የከተማ አስተዳደሩ በመሃል ከተማ የ500 ሺሕ መኖሪያ ቤቶችን ግንባታ ልጀምር ነው አለ

0
758

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ትላንት መስከረም 30/ 2012 ባወጣው መግለጫ በተያዘው ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ አስሩም ክፍለ ከተሞች 500 ሺሕ መኖሪያ ቤቶችን ግንባታ ለመጀመር ዝግጅቴን አጠናቅቄአለሁ ብሏል።

የከተማ አስተዳደሩ የቢሮው ኃላፊ ሰናይት ዳምጠው፣ በ2012 የሚገነቡት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ቀደም ሲል ከነበሩ ዲዛይኖች ላይ መጠነኛ ማሻሻያ እንደሚደረግባቸው በመግለጫቸው አስታውቀዋል። 500 ሺሕ መኖሪያ ቤቶችን በከተማው ለማስገንባት የተለያዩ የግንባታ አማራጮችን ይዞ ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም ገልፀዋል።

እንደኃላፊዋ ገለጻ፣ በመንግሥት የሚገነቡ 150 ሺሕ ቤቶችን በ20/80 እና 40/60 ፕሮግራም ተመዝግበው ለሚገኙ የሚገነቡ ሲሆን፣ በ75 ሄክታር መሬት ላይ 25 ሺሕ ኪራይ ቤቶች ግንባታ፤ ለዚህኛው በተለየ መልኩ በ10ሩም ክፍለ ከተሞች መታደስ እና መቀየር የሚገባቸውን የቀበሌ ቤቶች የሚገኙበትን ይዞታ በመጠቀም የሚገነባ ይሆናል።

በዚህም መሠረት የፓይለት ሥራው በኹለት ክፍለ ከተሞች መጀመሩንና የከተማዋ ኪስ ቦታዎችን በመጠቀም የ175 ሺሕ የማህበር ቤቶች ግንባታ በማካሔድ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ፣ ባለሃብቶችን በማሳተፍ አቅም ላላቸው ነዋሪዎች የአፓርታማዎችን ግንባታ ለማከናወን ዝግጅቱ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ከተለያዩ የሃገር ውስጥ እና የውጪ ሃገር ባለሃብቶች ጋር በመሆን በተያዘው ዓመት 25 ሺሕ ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ የተያዘ ሲሆን፣ ከሪል ስቴት አልሚዎች ጋር በመሆን 75 ሺሕ ቤቶች ግንባታ እንደሚጀመርና የተጠቀሱት የግንባታ አማራጮችን በ2012 በመጀመር በዓመቱ መጨረሻ የግንባታዎቹን 30 በመቶ ለማጠናቀቅ ይሠራል ብለዋል።

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሩ የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ከጀመረ 1996 ጀምሮ መገንባት የቻለው ከ200 ሺሕ ያልበለጡ ቤቶችን መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here