መነሻ ገጽዜናወፍ በረር ዜና‹መድኃኒቴ› የተሰኘ መተግበሪያ ይፋ ተደርጓል

‹መድኃኒቴ› የተሰኘ መተግበሪያ ይፋ ተደርጓል

በኢትዮጵያ በስፋት የሚስተዋለውን ጤና ነክ የመረጃ ክፍተቶች እና የታዘዘን መድኃኒት የት እና እንዴት ይገኛል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ያስችላል የተባለለት ‹መድኃኒቴ› የተባለ መተግበሪያ ይፋ ሆኗል።

ባሳለፍነው ሐምሌ 13/2014 በሸራተን አዲስ ሆቴል በተካሄደ መርሀ ግብር ይፋ የተደረገው ይህ መተግበሪያ፤ የጥሪ ማእከል አገልግሎት ፣ ለደንበኞቹ የትኛው መድኃኒት የት ፋርማሲ ይገኛል የሚለውን ሙሉ መረጃ በመስጠት በመረጃ እጦት ምክንያት መድኃኒት ለመግዛት የተቸገሩ ሰዎችን ልፋት ያስቀራል ተብሏል።

መተግበሪያውን ያበለጸገው የግሬት ካቮድ ድርጅት መሥራች ሰይፈገብርኤል ስዩም በመድረኩ እንደተናገሩት፣ ይህንን መተግበሪያ እውን ለማድረግ ከኹለት ዓመታት በላይ ጊዜ ፈጅቷል።

መድኃኒቴ በአፕ ስቶር እና ፕሌይ ስቶር አማካኝነት በእጅ ስልክ ላይ ሊገኝ የሚችል መተግበሪያ ሲሆን፣ ድረ ገጽ እንዲሁም በ9922 የጥሪ ማእከል አማካኝነት የሕክምና መረጃዎችንና የመድኃኒት ስም ዝርዝሮችን ከእነ መገኛ አድራሻዎቻቸው ለደንበኞቹ እንደሚያቀርብም ሰይፈገብርኤል አስረድተዋል። ለዚህም በዘርፉ ምሩቃን የሆኑ ባለሙያዎች ብቻ መመደባቸውን ነው ያመላከቱት።

ይህ አሠራር በመረጃ እጦት ምክንያት በሕገ ወጥ የደላሎች ሰንሰለት የሚወድቁ ሰዎችን ከኪሳራ እና መጭበርበር ይታደጋል ያሉት ሰይፈገብርኤል፣ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከ160 በላይ ፋርማሲዎች ጋር በትብብር ለመሥራት ስምምነት ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል።
በቀጣይ ጊዚያት የህብረተሰቡ ግንዛቤና ተጠቃሚነት እየተጠናከረ ሲመጣ ወደ ክፍለ አገራትም በመሄድ አገልግሎታቸውን እንደሚያስፋፉ አስታውቀዋል።

የመድኃኒት ነገር በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ስር የሰደደ ማኅበረሰባዊ ቀውስ መሆኑ በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች ይስተዋላል። ሐኪም ያዘዘውን መድኃኒት በቀላሉ ማግኘት አለመቻል፣ የሚገኘውም መድኃኒት ዋጋ ከፍተኛ መሆን፣ የሐኪም ማዘዣ ወረቀቶች በአግባቡ ተነብበው ትዕዛዙ አለመፈፀም፣ መድሃኒቶች የትኛው ፋርማሲ እንዳሉ አለማወቅ እና ፍለጋ መውጣት የብዙዎች የምሬት መንስኤም ሆኖ እንደሚስተዋል በእለቱ በመድረኩ ተነስቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 194 ሐምሌ 16 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች