የጤና ሚኒስቴር ለባህል መድኀኒት ጥናትና ምርምር 90 ሚሊዮን ብር መደበ

0
738

የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የባህል መድኀኒት ጥናትና ምርምር ፍኖተ ካርታ ይፋ አደረገ። ለፍኖተ ካርታው ተግባራዊነትም ጤና ሚኒስቴር 90 ሚሊዮን ብር መመደቡን የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ በላከው ጽሑፍ አስታውቋል።

የፍኖተ-ካርታው ዋና ዓላማ ሃገር በቀል ዕዉቀትን በመሰነድና በመጠበቅ የተጠናከረ ጥናትና ምርምር ማከናወን፣ የባህል መድኀኒት ባለሙያዎችን ማደራጀት፤ የባህል መድኀኒቶች በፋብሪካ እንዲመረቱ ማስቻል፤ ጠንካራ የምርምር -ዩኒቨርሲቲ እና የፋብሪካ ትስስር መፍጠር፤ የቤተ ሙከራዎችን አቅም ማሳደግ፣ ደረጃውን የጠበቀ የፍቱንነት፣ የደኅንነትና የጥራት የፍተሻ አገልግሎት መስጠት እና ከጤና ሚኒስቴርና ከተቆጣጣሪ አካላት ጋር በመተባበር ደረጃውን የጠበቀ የባህል ህክምና አገልግሎት በአገሪቱ እንዲሰጥ ለማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ጽሑፉ አመላክቷል።

ፍኖተ-ካርታው ይፋ በሆነበት ወቅት የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ ያላት መልክዓ ምድር እና አየር ንብረት ከ6 ሺሕ 500 በላይ የሚሆኑ የመድኀኒት እጽዋት፣ በርካታ እንስሳት እና ማዕድናት መገኛ መሆኗ፣ ከ 80 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝቧ ሲታመም መጀመሪያ የሚጠቀመው የባህል መድኀኒት መሆኑ እና ረጅም ዓመት የካበተ እውቀት አለ። ነገር ግን መጠቀም አልተቻለም። በመሆኑም የሃገራችን ሕዝብ ተፈላጊውን ጥቅም እንዲያገኝ ለማስቻል የባህል መድኀኒት ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት ትልቁ ጉዳይ በመሆኑ ተዘጋጅቶ ቀርቧል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በፍኖተ ካርታው መክፈቻ ሥነ-ስርዓት ወቅት እንደገለጹት የተለያዩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአገራችን በአማካይ ወደ 80 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የባህል መድኀኒት ተጠቃሚ ቢሆንም ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ግን ብዙም እንዳልሆነና በመንግሥት ደረጃም እውቅና ያገኘው በ1942 መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ በባህል መድኀኒቶች ላይ የተለያዩ ጥናትና ምርምር በጋራ ለማድረግ ኢንስቲትዩቱ ከሁሉም የሃገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎችና ከምርምር ተቋማት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሟል።

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here