የባለአደራ ምክር ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ማንነታቸው ባልታወቀ ግለሰቦች በመረበሹ ተቋረጠ

0
761

በጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ የሚመራው የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት ጥቅምት 2/2012 በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ ስለሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ እውቅና ለመስጠት፣ እንዲሁም ደግሞ ሰልፉን በተመለከተ ለሚመለከታቸው አካለት ጥሪ ለማድረግ ትላንትና መስከረም 30/2012 በሰጠው መግለጫ ላይ ማንነታቸው ባልታወቀ ወጣቶች ጩኽት እና ግርግር መቋረጡ ተነገረ።

ሰልፉን ለማካሔድ ሕጉ በሚፈቅደው መልኩ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጥያቄ ቢቀርብም መግለጫው እስከተሰጠበት ቀን ድረስ መልስ አለማግኘታቸውን፣ ነገር ግን በሕጉ መሰረት ሰልፉን ለማካሔድ የሚያግዳቸው ነገር አለመኖሩን እና ከመጀመሪያውም መግለጫውን እንዳይሰጥ ፖሊሶች የመከልከል ሙከራ አድርገው እንደነበር እስክንድር ተናግሯል።

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ እስክንድር በመግለጫው ላይ ‹‹አዲስ አበባ የኦሮምያ ሳትሆን ራሷን የቻለች ከተማ ነች›› ብሎ ተናግሮ ነበር። በዚህም ሰዓት ጥቂት ወጣቶች የኢፌዴሪን ሰንደቃ ዓላማ በመያዝ ‹‹ባንዲራው ይሄ ነው›› የሚል ድምፅ በማሰማት ግርግር የተፈጠረ ሲሆን መግለጫውም በዚህ ምክንያት መቋረጡ ታውቋል።
ይሁን እንጂ አሐዱ ሬዲዮ ስለ ሰልፉ እውቅና የጠየቀው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ጥያቄው ለአስተዳደሩ እንደ ደረሰና ለፌዴራልና ለከተማው የደኅነትና የፀጥታ መዋቅር እንዳሳወቀ ገልጿል።

በመስቀል አደባባይ ይደረጋል በተባለው ሰልፍም የዴሞክራሲና የሰላም መልዕክቶች ይተላለፋሉ ሲል የባለ አደራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ እስክንድር ነጋ ተናግሯል። በሰልፉ የሚሳተፉ የመዲናዋ ነዋሪዎችም ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ የፖለቲካ፣ ምጣኔ ሃብትና ማኅበራዊ ጥያቄዎቻቸውን እንዲያቀረቡ ባልደራሱ ጥሪ አቅርቧል።

ባልደራሱ ከሚያነሳቸው ጥያቄዎች መካከል የአዲስ አበባ ምክር ቤትና የካቢኔ ሥልጣን ዘመን አልቋል፣ ስለዚህም የባለ አደራ አስተዳደር መመስረት አለበት የሚለው ይገኝበታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here