መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናከጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት 181 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተሰብስቧል

ከጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት 181 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተሰብስቧል

• ገቢው ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ20 በመቶ ብልጫ አለው ተብሏል

ኢትዮጵያ በ2014 በጀት ዓመት ከጨርቃጨርቅ ምርቶች ገበያ 181 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መሰብሰቧን የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

በ2014 በጀት ዓመት ከተለያዩ የጨርቃጨርቅ ምርቶች ገበያ 204 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ፤ 181 ነጥብ አምስት ዶላር መሰብሰብ መቻሉን የኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮምዩኒሼሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ባንቲሁን ገሰሰ አዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ባንቲሁን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ ከጨርቃጨርቅ ምርቶች በ2014 በጀት ዓመት 200 ሚሊዮን 21 ሺሕ ዶላር ለማሰባሰብ አቅዶ እንደነበር ጠቅሰው፤ የተገኘው አፈጻጸምም ከዚህ በፊት ከነበሩት የበጀት ዓመቶች ጋር ሲነጻጸር የተሻለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በ2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከጨርቃጨርቅ ምርቶች ገበያ የተገኘው ገቢ 151 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፤ በ2014 የተሰበሰበው ግን የ30 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ እንዳለውም ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።

ዓመታዊ ገቢው በዋነኝነት የተሰበሰበው ኢንስቲትዩቱ ለገበያ ከሚያቀርባቸው ታዋቂ ምርቶች ማለትም ከክር፣ ከጨርቅ፣ ከልብስ እና ከባህላዊ አልባሳት መሆኑን የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በሌላ በኩል ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ እንዳሳወቁት ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ዓመቱን ሙሉ ያስተናገደችው ውጣውረድ ቀላል ባለመሆኑ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ቢከሰቱም፣ ዘንድሮ የተሰበሰበው ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ20 በመቶ ብልጫ እንዳለው ነው።

ምንም እንኳ በ2014 ከጨርቃጨርቅ ምርቶች የተገኘው ገቢ ከ2013 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ብልጫ ቢያሳይም፣ ኢንስቲትዩቱ በርካታ ችግሮች ተጋርጠውበት ማለፋቸውን ግን ባንቲሁን አስረድተዋል።

የመብራት መቆራረጥ እና የግብዓት እጥረት ተቋሙን በይበልጥ የሚፈታተኑት መሰናክሎች መሆናቸውም ለአብነት ጠቅሰዋል።

ባንቲሁን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በተለይም ግብዓቶቹን ከታለመላቸው የመጨረሻ ውጤት ለማድረስ መብራት ትልቁን ድርሻ መያዙ የሚታወቅ መሆኑን አንስተው፤ ይሁን እንጂ በየወቅቱ የሚከሰተው የመብራት መቆራረጥ በሥራቸው ላይ መሰናክል ሳይሆን እንዳልቀረ አብራርተዋል።

በጦርነቱ ምክንያት የቆዳን ጨምሮ 11 የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች መውደማቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከዚህ በፊት መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፤ ክስተቱ በተለያዩ የጨርቃጨርቅ ምርቶች ላይ የግብዓት እጥረት ሳያስከትል እንዳልቀረም ተጠቁሟል።

በመሆኑም፣ በጦርነት ቀጠና ውስጥ በነበሩ እና በሚገኙ ሥፍራዎች የተፈጠረው አለመረጋጋትም ኢንስቲትዩቱ ከሰበሰበው ገቢ ተጨማሪ እንዳያገኝ ከገደቡት መሰናክሎች ተጠቃሽ መሆኑ ተመላክቷል።

በተቋሙ የሚገኙ የውጭ መሠረት ያላቸው አምራቾች በአብዛኛው የአገዋ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ የኢንቨስትመንት ዓላማ ይዘው መምጣታቸው፣ መፍትሄ በማጣታቸው እናቋርጣለን የሚሉ ድርጅቶች መብዛታቸውም እንደ ችግር ተነስቷል።

በተጨማሪም፤ የአገዋ የገበያ መቋረጥ ያስከተለው አሉታዊ ተጽዕኖ በርካታ መሆኑ የኤክስፖርት ገበያ ትዕዛዝ እንዲቋረጥና ገዢዎች የገበያ ትዕዛዝ መጠን እንዲቀንሱ ማድረጉ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በአይካ አዲስ ጨርቃጨርቅ፤ በኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ፤ በአዳማ ጨርቃጨርቅ፣ በባህር ዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ እንዲሁም በሌሎች በርካታ ቅርንጫፎች በጨርቃጨርቅ ምርቶች ሥራ የተሰማራ ተቋም ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 194 ሐምሌ 16 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች