ባለብሩሽ: ኢትዮጵያዊ ጥበብን ከዘመናዊው ያዋሐደ

0
1105

ስዕል ከልጅነታቸው ጀምሮ አብሯቸው የቆየ የማንነታቸው ክፋይ ነው። ከኢትዮጵያ ተሻግረው በባሕር ማዶ ይልቁን በሩስያ የአሳሳል ጥበብን በትምህርት የቀሰሙ ቢሆንም ኢትዮጵያዊ የሆነውን አሳሳል እንዳልነጠቃቸውና እንዳልጋረደባቸው በልበ ሙሉነት ይናገራሉ። ኢትዮጵያዊ የሆነውን የአሳሳል ጥበብ በዘመናዊ መንገድ ያቀርባሉ ከሚባሉ ቀደምት ጥቂት ሰዓልያን መካከልም ሥማቸው ይገኛል፤ ሰዓሊ ልዑልሰገድ ረታ።

ልጅነታቸውንና ተማሪነታቸውን ሲያስታውሱ፤ እንደማንኛውም ተማሪ ፀሐይ አቃጥሎን፣ ዝናብ ቀጥቅጦን፣ ፓስቲ እየበላን በእግራችን እየሔድን ነው ይላሉ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን መስፍን ሐረር እና ወይዘሮ ቀለመወርቅ ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል። ኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ኹለት ዓመት ተፈሪ መኮንን፣ ከዛ ካቴድራል ትምህርት ቤት የማታ ተምረዋል። ይህ የሆነው በ1962 ሲሆን ያኔ አርት ስኩል ገብተው ስለነበር ነው የማታ ትምህርትን እንዲከታተሉ የሆነው።

ባለትዳርና የአንዲት ሴት ልጅ አባት የሆኑት ሰዓሊ ልዑልሰገድ፣ ለደረሱበት ደረጃ የብዙዎች ድርሻ እንዳለበት ከመናገር አይቆጠቡም። ከምስጋናቸውና ከአክብሮታቸው አንድም እንዳይጎድል ሲሉ አዲስ ማለዳን ማሳሰባቸው አልቀረም። በዚህም ሰዓሊ ታደሰ መስፍንን ደጋግመው ይጠራሉ ያመሰግናሉም። ያስተማሯቸውን ታደሰ መመጫን እና ወርቁ ማሞንም ባለውለታዎቼ ናቸው ይሏቸዋል።

ሰዓሊ ልዑልሰገድ ትውልድና እድገታቸው አዲስ አበባ ይሁን እንጂ፤ ብዙ ዘመድና ጓደኛ ያላቸው በመሆኑ ከአዲስ አበባ በተለይ በክረምት የእረፍቱ ጊዜ ድሬዳዋ እና አስመራ እንዲሁም ዘመድና ጓደኛ እንሒድ ባለበት ሁሉ ይሔዱ ነበር። “እኔ ዕድለኛ ነኝ፤ ብዙ ጓደኞች አሉኝ” ይላሉ። ሰፊ የሆነ ማኅበራዊ ትስስራቸውም ብዙ ነገር ማወቅ እንዳስቻላቸው ያምናሉ።

በልጅነት በዓይናቸው ገብቶ የቀረው የአብያተ ክርስትያናት የሥዕል ጥበብ በተፈጥሮ ከታደሉት ጸጋ ጋር ተደምሮና በልጅነት ባለው ጨዋታና ማኅበራዊ መስተጋብር ዳብሮ፤ የስዕል ችሎታቸው ዛሬ ላይ አንቱታን አትርፎላቸዋል። ኢትዮጵያም የራሷ የሆነውን የአሳሳል ጥበብ ሳይጥል ከዘመን ያዋሐደ ብሩሽ ባለቤት ከሆኑ ሰዓልያን መካከል ሰዓሊ ልዑልሰገድን አግኝታለች።

የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ሰዓሊው ቦሌ መድኃኒዓለም አካባቢ በሚገኘው ወልድ ፍቅር ሕንጻ፤ አዲስ ፋይን አርት ጋለሪ “መክሊት” የተሰኘ የስዕል ዓውደ ርዕያቸውን ፈረንጆቹ “ከፈረሱ አፍ” እንደሚሉት በራሳቸው በልዑልሰገድ ረታ ገለጻ ከጎበኘች በኋላ ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።

አዲስ ማለዳ፤ በስዕል ሥራዎችዎ ብዙ ጊዜ የሴት ገጽ ይጠቀማሉ፤ ይህ ከምን የመጣ ይሆን?
ሰዓሊ ልዑልሰገድ ረታ፤ መሠረት አለኝ፤ አመጣጤም ከእናቴ ነው። ስለዚህ እናት ምን እንደሆነች፣ እህት ምን እንደሆነች፣ ጓደኛ ምን እንደሆነች፣ ሚስት ምን እንደሆነች፣ ልጅ ምን እንደሆነች የተረዳሁበት ዘመን ስለሆነ ሰለሴት ሙሉ ቀን ማውራት እችላለሁ። ቁምነገሩ የእናቶችን ልፋት፣ ብልሃትና ዘዴ እንዲሁም ውበት በተቻለኝ መጠን ለረጅም ጊዜ አብረውኝ ካደጉት፣ ጊዜዬን ካሳለፍኩበት ከአካባቢዬ፤ ኢትዮጵያውያንን የተረዳሁበት መንገድና ግንዛቤ ያገኘሁበት፤ ከጓደኞቼም በትምህርት ቤት የተረዳሁት ነው። አሁን ዘመን ላይ ያለነው ከድሮ ጋር በማዋሐድ ለሴት ከፍተኛ ግምት ስላለኝ፣ በእነርሱ ላይ ብዙ ትኩረት ማድረጌ እውነት ነው።
ግን አንድ ነገር ስንሠራ ማወቅ ያለብን የተረዳነውን ነገር በአግባቡ ለተመልካችም ለራስም በተገቢው መልክ ማድረስ እንዳለብን ነው። ያም እንዲሆን ሆነ ብዬ የተጠቀምኩባቸው የአሳሳል ዘዴዎች አሉ፤ በአብዛኛውም ሴቶች ናቸው። ይኼ ማለት ወንድ አይገባበትም ማለት አይደለም። ይህ የሆነበትን ምክንያት በእርግጥ እኔም አላውቀውም፤ አብሬ የኖርኩበት ስለሆነ። አቀማመጥ፣ እንቅስቃሴና መሰል ሁኔታዎችን የምረዳበት መንገድ በእነርሱ [በሴቶች] ላይ ያይላል።

የኢትዮጵያ የአሳሳል ጥበብ ከቀሪው ዓለምም ሆነ ከአፍሪካ እንዴት ይነጻጸራል?
ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ያላት አገር ናት። ይህ በአበው በትልልቅ ሰዎች ተጽፎ ተነግሮ ያላለቀ ነው። እንደውም በደንብ አልተጻፈም በደንብም አልተነገረም። ወደፊት ምናልባት አቅምና ጊዜ ሲኖር፤ ወይም ኢትዮጵያዊነት የገባን ቀን ስለ ኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ዕድገት ከየት ተጀምሮ የት እንደደረሰ መናገር ይቻላል። ነገር ግን ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራትም በስዕል ጥበብ ትለያለች።

በቅብና በዘመናዊ በተለይ ደግሞ ‘ማጂክ ስክሮል’ የመሳሰሉ በሊቃውንት ወይም አዋቂዎች፤ ለፍቅርም ለጥላቻም የሚሠሩ የክታብ ሥራዎች አሉና ከዛም ጋር የሚያያዝ ነው። በአብያተ ክርስትያናት ያሉ ስዕላትም የሚያስረዱን፤ አንድ ነገር ብቻ እንዳናይ፣ እንድናግዝበት፣ እንድንማማርበት ነው።

እኔም ያንን መሠረት አድርጌ የሰማያዊውን ወደ ምድራዊ ዓለም በተጓዳኝ አምጥቼ በኢትዮጵያን ሥነ ጥበብ ትንሽ የተፈነጠቀ የሚመስል አካሔድ አለኝ። ይኸውም ትምህርቴን ጨርሼ ስመጣ በሥራ ዓለም በነበርኩበትና በኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ስሠራ የሠራኋቸው ባሕላዊ ዘመናዊ ፖስተሮች ነበሩ፤ ትልቅ ሥራ ነው። ታስቦበትና ተጨንቆ የተሠራ ነበር። አሁን ላለሁበት ዘመንም አሻራ ነው ብዬ ነው የማምነው።

ከኢትዮጵያዊ አሳሳል ጥበብ ወደ ዘመናዊነት በሚደረግ ለውጥ የፍልስፍና ለውጥም ያስፈልጋል የሚሉ አሉ፤ ይህን እንዴት ያዩታል?
ወደ ፍልስፍና መሔድ ከባድ ነው። እያንዳንዱ ሰው እየረቀቀ ሲሔድ ወደዛ መድረሱ አይቀርም። ነገር ግን ገና በአስተሳሰብ ለውጥ አልሠራንም። ፍልስፍና ባለው ላይ ብዙ መጠበብ፣ ባለው ላይ ተሞክሮ ታይቶ ‘በርታ’ ሲባል ነው የሚመጣው። ምንም በሌለበት ፍልስፍናውን ይዞ መቀመጥና ማውራት አይቻልም።

ያም ሆኖ እኛ መሠረት አለን። የሰለሞንም ሆነ የሳባ፣ የቴዎድሮስም ሆነ የቤተክህነቱ፣ መሠረት አለን። እንደዚህ የሆንበት ምክንያት አንደኛ ሃይማኖት አለን፤ ኹለተኛ ቋንቋ አለን፤ ሦስተኛ ደግሞ አገር አለን፤ መጨረሻ ባሕል አለን። ከመፈላሰፍ በላይም መሆን ይቻላል፤ ነገር ግን ባለው ላይ የበለጠ እውቀት ሰጥተን፣ ሕዝብን ሳናሳስስት ነው መሥራት ያለብን።

ምክንያቱም ሥነ ጥበብ የአንድ አገር ፊት ነው፣ የውስጥ ስሜት መገለጫ ነው። እግዚአብሔር የሰጠሽ የራስሽ ጥረት ያለበት፤ ዘመኑ የፈቀደልሽ፣ ያንቺ ብርታት ውስጡ ኖሮ አገርን ለተመልካች፣ ለዓለም ሕዝብ የሚያሳወቅ ሥራ መስጠት ማለት ነው። ለዚህ ፈቃደኝነት፣ ለጋስነት፣ ደግነት፣ ፍቅር ያስፈልጋል። እንጂ ዝም ብሎ አይመጣም። ጥበብ ለክፉ ነገር አይሆንም።

በዘመናዊ አሳሳል ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ነች ማለት ይቻላል?
በፊት የአብያተ ክህነት ሥራዎች መልክዓ ምድርን የሚገልጹና አገርን የሚወክሉ አንዳንድ ሥራዎች ናቸው። አሁን ዘመኑ ላይ ያለው ደግሞ እያንዳንዱ በተለይ በዘመነኛ ሥራ ላይ ልንጠቅስ የምንችላቸው ሰዓልያን አሉ። እንደ እስክንድር ቦጎሲያን፣ ገብረክርስቶስ ደስታ፣ ታደሰ መስፍን፣ መዝገቡ ተሰማ፣ ጌታሁን አሰፋ፣ እሸቱ ጥሩነህና እኔን ጨምሮ ወደ ዘመናዊ አሳሳል ጥበብ የገባን ነን።

አሁን ወጣቱ ደግሞ ትንሽ የራሱ አካሔድ አለው። ምን ያህል የታኘከ ነው፤ እሱን ተመልካችና ራሳቸው ማየት ይችላሉ። ትልቁ ቁም ነገር ግን አንድ ሰዓሊ ክህሎት ካለው፣ በዛ ላይ ከተማረ የአገሩን ጥበብ ሰፊ የማድረግ አቅም ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ።

ሰዓሊ ልዑልሰገድ ማንን ያደንቃሉ?
እኔ ብዙ ሰው አደንቃለሁ። በትምህርት ቤት ዘመኔ የመጀመሪያው ታደሰ መስፍን ነው። ታደሰ መስፍን የእኔ መካሪ (‘ሜንቶር’) ነው፤ ኹለተኛ የስዕል ትምህርት እንድጀምር ያደረገኝ ሰዓሊና ጓደኛዬም ነው። ከዛ አስተማሪዬን ገብረክርስቶስ ደስታን፣ ታደሰ ማመጫን፣ ወርቁ ማሞን በስዕል ላይ በጣም አደንቃቸዋለሁ።
የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌም እንደዚሁ የእኔም ‹ኢቫሉዌተር› ነበሩ፤ በሥራቸውና ለስዕል ሥነ ጥበብ በሚሰጡት ክብር በጣም ነው የማደንቃቸው። ከዛ በተረፈ እንደ ወሰኔ ኮስረፍ፣ ተሾመ በቀለ፣ ጥበበ ተረፋ፣ ዘሪሁን የትምጌታ፣ አሁን ደግሞ ወጣትና ጎበዝ የሆኑ ልጆች እንደ ስዩም አያሌው፣ ታምራት ሱልጣን፣ በእኔ እኩያ ያሉም አሉ፤ ብቻ ቁጥራቸው ብዙ ነው።

ሁላችንም በየራሳችን ጥረታችንን ከፍ እያደረግን ከእነዚህ ሰዎች ጋር በመሥራትና አብሮ በማየት ራስን መፈተሸ ስላስፈለገና ዕድሉ ስላጋጠመኝ እኔ ዕድለኛ ነኝ። ለምን? አስተማሪዎች አስተምረውኝ፣ ጓደኞቼ ጋር አብረን ሠርተን፣ ውጪ አገር አብረን ተምረን ነው።

አሁን አገሬ ከተመለስኩ በኋላ የግድ ሰዓሊ ብቻ መኮን የለበትም። እንደነ ፀጋዬ ገብረመድኅን፣ ተስፋዬ ገሠሠ፣ ሳህሉ አሰፋ፣ መላኩ አሻግሬ፤ እነኚህ የጥበብ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ለኢትዮጵያ የሥነ ጥበብና ኪነ ጥበብ ዘርፍ ትልቅ አሻራ ያላቸው ሰዎች ናቸው። ከእነዚህ ሰዎች ጋር በቴአትር ቤት አብሬ ስለሠራሁም ዕድለኛ ነኝ። በዛም እንደነ ፍቃዱ ተክለማርያም፣ አሰለፈች አሽኔ፣ አብራር አብዶ፣ ሳራ ተክሌ፣ ወጋየሁ ንጋቱ፣ ዓለምፀሐይ ወዳጆ፣ ደበበ እሸቱ፤ ከእነዚህ ሰዎች ጋር አብረሽ ውለሽና አውርተሸ የራስሽን አንድ ነገር ማበርከት ካቃተሸ አንቺ የለሽም ማለት ነው።

አሁን ላይ ካሉ ከወጣት ሰዓልያን ምን ተመለከቱ?
የአሁኑ ወጣት ለምንም ነገር ይቸኩላል፤ ይሔ ግን አይችሉም ማለት አይደለም፤ በደንብ ከሠሩ ጥሩ ነው። በስዕል ጥበብ ላይ ያሉ ወጣቶች ጥረታቸውን አደንቃለሁ፤ ጊዜውም ያግዛቸዋል፤ በተለይ ዲጂታል ቴክኖሎጂ መኖሩ። ነገር ግን የግንዛቤ እጥረት አለ። የመረዳት፣ ሆኖ የመገኘት ጉድለት አለ፤ እናም እንዲህ ባሉት ነገሮች ላይ ትንሽ ትጥቅ ይፈልጋሉ።

ትጥቅ ስል አረዳድ ወሳኝ ነው። እኛ ያደግነው እንደ እነርሱ እድል አግኝተን አይደለም፤ ተረድተን ነው የምንሠራው። አሁን የተሰጣቸውን ነው የሚሠሩት። ያ የአመለካከት አድማስ ሰፊና አጭር የሚያደርግ ሁኔታ ነው። እኛ ያኔ ብዙ ነገር ነው የምንመኘው፤ አሁን ትንሽ ነገር ላይ ነው ትኩረት የሚያደርጉት። ለማግኘትና ለማጣት፤ አሁን ንግዱም ትንሽ ይበዛል። በእኛ ጊዜ መሥራትና መታወቅ እንጂ ገንዘብ አልነበረም።

በእርግጥ ወጣቱን በደፈናው መኮነን አይቻልም። ግን በታሪክ፣ በባሕል እንዲሞላ ያስፈልጋል፤ ወሳኝም ነው። ይህን ማወቅና መገንዘብ አለባቸው። እነርሱ በአጭር ጊዜ በአቋርጭ መክበርን ይፈልጋሉ። ይህ ግን በኋላ የሚጎዳው እነሱን ነው። ተርቦ ያልሠራ ሰው ጠግቦ ቢሠራ ዋጋ የለውምና ነው። እናም ትልቅ ስንቅ ያስፈልጋል።
ቴአትር ማየት፣ ማንበብ፣ ፊልም መመልከት፣ ከሰዎች ጋር ሰብሰብ ማለትና ታላላቆችን መጠየቅ ጠቃሚ ነው። እንዲሁም አገርን ማወቅና መጎብኘትም ያስፈልጋል። በዓላትን በደንብ መገንዘብም እንደዛው። ስለዚህ ይህን ትጥቅ የሚያሰፈታ ሰው ቢኖር እንኳን እየቀነሱ ነው እንጂ ሁሉም አይዘረገፍም፤ ብልሃትና እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል።

ትልቁ ነገር ደግሞ የማንነት ጉዳይ ነው። ማንኛውም ሙያ ልፋት አለው፤ ግንዛቤና መረዳት እንዲሁም ማወቅ ያስፈልጋል። ከመናገር ወይም ዝም ከማለት ማዳመጥ ጠቃሚ ነው። ስለዚህ ይህን ማዳበር አለባቸው። ተረቶቻችንን ማወቅም ጠቃሚ ነው። ብዙ ሊረዱ የሚገባቸው ነገሮች አሉ። ይህ የሚሆነው በልፋት ነው፤ ጥረት ያስፈልጋል።

ልጆቹ የተሰጣቸውን መሆን ይችላሉ፤ እንዴት የሚለውን ነገር በትምህርት ቤት የሚገኝ ነው። ትምህርት ሲሰጥም ልጅ ናቸው ብሎ መተውና በሰፊው መስጠት ሳይሆን ሁሉን ነገር በግንዛቤ እንዲያደርጉ፣ እንዲረዱትና እንዲያውቁት ከተደረገ የእኛ ልጆች ብልሃተኛ ናቸው። ስለዚህ መሠረት እንዲኖራቸው ከመጀመሪያው ነው ማስተማር ያለብን። ካልሆነ በኋላ አሁን ከምናዝነው የበለጠ ልናዝን እንችላን።

የአሁን ዘመን ከእኛ ዘመን የተሻለ ነው። ድካም ሳይኖር በአጭር ጊዜ ብዙ ነገር ለመረዳት ይቻላል። ይህም ልጆች እንዳያመልጣቸው ነው። ሌላው ደግሞ በሽታ እንኳን ቢሆን ታማሚው ነው ሃምሳ በመቶ ራሱን መጀመሪያ የሚያክመው። ለመድኀኒቱና ለሕክምናው ማገዝ የሚችለው ታማሚ ነው። እናም ብዙ ነገሮችን ስንሠራ መረዳት አለብን የምንለው ለዛ ነው።

‘አርት ኦፍ ኢትዮጵያ’ በሸራተን አዲስ ሆቴል በየዓመቱ የሚካሔድ የስዕል ዓውደ ርዕይ ነው፤ አሁን በየኹለት ዓመቱ ሆኗል፤ ሲጀመር ዓላማው ምን ነበር፤ ለምንስ በየኹለት ዓመቱ ሆነ?
የተጀመረው በስምንት ሰዓልያን በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2008 የተጀመረ ነው፤ ‘መርጅ’ በሚል መጠሪያ። በወቅቱ የሸራተን ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ሚስተር ዣንፔር ማኒንጎፍ (ነፍሳቸውን ይማር) ሞት ቀደማቸው እንጂ ለኢትዮጵያ ትልቅ ህልምና ብዙ ዓላማ ነበራቸው። በ2007 አንድ ቦታ ተቀምጠን እያወራን ነው ይህ ሐሳብ የተጠነሰሰው።

መጀመሪያ በሆቴሉ የእኔ ስዕሎች ይታዩ ነበር፤ ብዙ ስዕል ገዝተውኝም ነበር። እናም በዛ ቀን ሌሎች ሰዓልያን ጋር አብረን ብንሠራ ሲሉኝ በደስታ አልኳቸው፤ የሚያስፈልገንን ከቻላችሁ ሰዓሊው አለ አልኳቸው። በዚህ ተስማምተን ከእኔ ጋር የሦስት ትውልዱ ሰዓልያን ያሉበት የስምንት ሰዓልያንን ሥም ዝርዝር ሰጠኋቸው። ዮሐንስ ገዳሙ፣ ተሸመ በቀለ፣ ጥበበ ተርባ፣ ታደሰ መስፍን፣ መዝገቡ ተሰማ እና ሌሎች ኹለት ሰዓሊያን ጋር ሆነን ጀመርን። እንድናሳይ ፈቀዱ፤ በዛ መሠረት ቦታውም ተዘጋጀልን።

የስምንታችን ሥራ ሲታይ ደነገጡ፤ አልጠበቁም ነበር። እኛም ደስ አለን። ከዛ የመጀመሪያው ዓውደ ርዕይ ሊዘጋ አንድ ቀን ሲቀረው ጠርተውኝ ሕዝቡም እኛም ተደስተናል፤ ስለዚህ የሚቀጥለው ዓመት በዚሁ ቀን ሠላሳ ሰዓሊ አድርጌልሃለሁ አሉኝ፤ ደነገጥኩ። ይኼ ማለት ለእኛ ትልቅ ነው ብዬ አመሰገንኩ። አፈወርቅ ተክሌንም አካትታለሁ ስል፤ አፈወርቅ እኛ ለምነነው እንቢ ብሎናል፤ ስለዚህ እሱን አትቸገር አለኝ። እኔም አናግረዋለሁ አልኳቸው፤ አፈወርቅም በደስታ ፈቃደኝነቱን ገለጸልኝ፤ እሳተፋለሁ አለ። ከዛም በኋላ ኹለት ጊዜ ነው የተሳተፈው፤ ይህም ቀላል አይደለም።

‘አርት ኦፍ ኢትዮጵያ’ በዚህ መልክ ተጀምሮ በርካታ ሰዓልያን፣ አስተማሪዎቼን፣ ታላላቆቼን፣ ጓደኞቼን፣ ወጣቶችን በሙሉ አሳትፌ አሁን የደረሰበት ደረጃ ደርሷል። ልክ እንደ ቱሪዝም መስህብም ሆኗል። እግዚአብሔር ሲረዳን ተሳክቷል።

የተለያዩ ሰዓልያን ናቸው በዛ ያለፉት፤ አሁንም በዚህ ለመሳተፍና ለመግባት የማይጥር የለም። ይኼ ነው የሚፈለገው። አንዳንድ ሰዓልያን የተለየ አመለካከት ነበራቸው፤ የሸጡ ሰዓልያን አመስግነው ሲሔዱ ያልሸጡ እየተሳደቡ ነው የሚሔዱት። እኔ ግን እፈልግ የነበረው የምስል/ዕይታ ለውጥ ነው። የሰዓሊውን የአገራችንን ዕይታ ለመለወጥ እፈልግ ነበር፤ እግዚአብሔር ይመስገን እስከአሁን ጥሩ ነው።

በየዓመቱ የነበረው በየኹለት ዓመቱ የሆነው፤ ሸራተንን ብዙ ሰው ያስቸግራል። ለስዕል ብቻ ይህ ሁሉ ተሰጠ የሚሉና በጎን ሔደው ከስዕሉ ጋር በተገዳኝ ሌላ ሥራ እንዲሠራ የሚፈልጉም ነበሩ። እኔ ግን አይሆንም ብያለሁ፤ ከፈለጋችሁ በራሳችሁ አድርጉ ነው የምለው። ከዛም የፎቶግራፍ ፌስቲቫል ተብሎ ተጀመረ። አንድ ቀን የተካሔደ ቢሆንም ይህ የፎቶ ፌስቲቫል ተዘጋጀ። እኔም ይሁን ሲሉኝ የማደርገው ነገር አልነበረም፤ መቀያየም እንዳይመጣም ቀረና በየኹለት ዓመቱ ሆነ።

መናገር የምፈልገው ሆቴሉ የሚያደርገው ነገር ቀላል እንዳልሆነ ነው። አዳራሹን ሲሰጡን፤ አዳርሽ ውስጥ ከመግባታችን በፊት ስድስት ቀን ስዕል ለመስቀል የሚያልፍ፣ ከተሰቀለ በኋላ አራት ቀን፤ ከዛ ደግሞ ለመውሰድና ለመቀበል የሚወሰዱ ቀናት አሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን እነዚህ ለሆቴሉ ወጪ ናቸው። ይህን ሁሉ እያደረጉ፤ በቀን ብዙ ገንዘብ የሚያገኙበትን እየተዉ መናገር ልክ አይሆንም። በፊትም ሆነ አሁን ያሉትም ጥሩ ሥራ እየሠሩ ነው። ዘንድሮም ከኹለት ወር በኋላ ይኸው ዓውደ ርዕይ የሚኖር ይሆናል።

ወደ ኋላ ልመልስዎ ነው፤ በሩስያ የሥነ ጥበብ ትምህርት ተከታትለዋል። ቆይታዎ እንዴት ነበር?
እንደ ማንኛውም ዕድለኛ ኢትዮጵያዊ ዕድል አግኝቼ ወደ ሶቭየት ኅብረት የሔድኩት በ1979 ነው፤ በአውሮፓውያን አቆጣጠር። እናም ዐሥር ወር ሙሉ በቅድመ ዝግጅት ኡዝቤኪስታን የሚባል ከተማ ነው ቆይታ ያደረኩት። ከዛ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ቤት (አካዳሚክ) ለመግባት እዛው ፈተና ነበርና እሱን አለፍኩና ቀጥታ ወደ ሌኒንግራድ የሥነ ጥበብ ትምህርት አካዳሚ ለመግባት ችያለሁ።

እዛ ስሔድ ቀደም ብዬ አማካሪዬ ነው ብዬ የጠቀስኩት ታደሰ መስፍን በዛ ጊዜ እዛው ሦስተኛ ዓመት ነበር። እርሱ ቋንቋውንም ባሕሉንም ስለሚያውቅ “እባክህን መስመሬንም ስለምታውቅ የትኛው የትምህርት ክፍል ለእኔ ይሆናል?” ብዬ ሳማክረው፤ “አንተ ግራፊክ ላይ ብትገባ ጥሩ ነው፤ ቅብ ላይ የምታውቀው ስለሆነ በግራፊክሱ ቀጥል” አለኝ።

የመጀመሪያ ቀን ስዕላችንን ስናቀርብ የግራፊክስ ትምህርት ክፍል ዲን የእኔን ሥራ አይተው ‹ይኼ የእኔ ልጅ ነው› ብለውኝ ነበር። እስክጨርስ ድረስም ከእርሳቸው ጋር ሠራን፤ በማዕረግ ነው የተመረቅኩትም። በዛ ቆይታዬም ማኅበራዊ ግንኙነቴም ጠንካራ ነበር። ለአምስት ዓመታት የተማሪዎች ፕሬዝዳንት ነበርኩ። ይህም ብዙ ንግግር እንዳደርግና ከሰዎች ጋር እንድግባባ አስችሎኛል። እናም በ1986 ትምህርቴን አጠናቅቄ ወደ አገሬ ተመለስኩ።

እዚህ ስመጣ መጀመሪያ የገባሁት የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ነው። በዛም ኮሜርሻል አርቲስት ሆኜ፣ የሥነ ጥበባት ክፍል ኀላፊ ከዛም ባለሙያ ሆኜ ዘጠኝ ዓመት አገልግያለሁ። የውጪ ትምህርት ዕድል ከማግኘቴ ቀደም ብሎ ደግሞ ለኹለት ዓመታት ብሔራዊ ቴአትር አገልግያለሁ። ከ1996 ጀምሮ እስከአሁን የስቱድዩ አርቲስት ነኝ።

በዚህ ሁሉ መካከል ብዙ ውጣውረዶች አሉ። አሁን ያለሁበት ደረጃ ለመድረስ ብዙ አልፏል። መግለጽ የማልፈልገው ብዙ መጠላለፎች ነበሩ። ሥራ ላይ ማተኮር ግን አስፈላጊ ነው። ያኔ እግዚአብሔርም ይረዳል።

ወደ ስዕል ግን ምን ነበር ያመለከትዎ?
ወደ ስዕል አንድገባ የገፋፋኝ አንዱ የቤተክርስትያን ስዕላትን በማየቴ ነው። እሱን በማየት ብቻ ሳይሆን ፊልም ያኔ ስናይ በሃማሳ ሳንቲም ሦስት አራት ፊልም ነበር የምናየው። በጊዜው የነበሩት የሚታዩ ፊልሞች የሚተዋወቁበት ሬክላም የሚባል አለ፤ የፊልሙ ማስታወቂያ የሚለጠፍበት ቦርድ ነው። ያንን ማየት በጣም ይማርከኝ ነበር። ከዛም ታላቅ ወንድሜም ስዕል ይሞክር ስለነበር ከእርሱ ጋር እንወደደር ነበር። በትምህርት ቤት በወላጆች ቀን የስዕል ውድድርም ሁሌ አንደኛ ነበር የምወጣው። ብዙ እገዛ ስዕልን እንድማር፣ እንድረዳ አድርጎኛል።

ከዛ በተፈረ አስተማሪዬ እና ጎረቤቴ የነበረው ገብረክርስቶስ ደስታ ነው። ከእርሱ ጋር ብዙ ግንኙነቶች ነበሩን፤ ዕድለኛም ነኝ። አንድ ጊዜ የእናት አገር ጥሪ ተብሎ በወይዘሮ ቀለመወርቅ ትምህርት ቤት የስዕል ዓውደ ርዕይ ቀርቦ ነበርና፣ እኔ ገብረክርስቶስ እና ፋሲካ የሚባል ሰው ነበርን አብረን ያቀረብነው። ይህ ሁሉ እልህ ውስጥ እንድገባ፣ ጥረት እንዳደርግ አግዞኛል። ጋሽ ገብረክርስቶስ እና በሕይወቴ የማልረሳው መምህር ታደሰ ማመጫ ናቸው። ወርቁ ማሞም እንዲሁ፤ ሁሉም ባለውለታዎቼ ናቸው።

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here