መነሻ ገጽዜናወቅታዊክረምት የፈተናቸው ተፈናቃዮች

ክረምት የፈተናቸው ተፈናቃዮች

ባሉበት አካባቢ በወቅቱ ዶፍ ዝናብ እየወረደ ነበር። ባለታሪኳ ከአዲስ ማለዳ ጋር በሚነጋገሩበት ወቅት በሥፍራው የተፈናቃይ መጠለያ ባለመኖሩ በክረምቱ ቁር ከልጆቻቸው ጋር በረንዳ ላይ ኩርምት ብለው እንደተቀመጡ እየገለጹ በየመሃሉ ሲማረሩ ይሰማሉ። ሰዓዳ ይማም የሀሮ ሊሙ ወረዳ አርቁምቢ መንደር አንድ ነዋሪ ናቸው።

ራሱን ‹የኦሮሞ ነፃ አውጭ› ብሎ የሚጠራው ኦነግ ሸኔ በነዋሪዎች ላይ ከሚያደረሰው የግድያ ጥቃት ሕይወታቸውን ለማዳን አንጻራዊ ሰላም ወዳለባት አንገር ጉትን ከተማ ከተፈናቀሉ ድፍን ኹለት ዓመታን አስቆጥረዋል። ታዲያ ታጣቂ ቡድኑ ከሚሰነዝረው ጥቃት ነፍሳቸውን ለማትረፍ መፈናቀል ግዴታ የሆነባቸው በርካታ ሰዎች የመጠለያ ጣቢያ እንኳ ባለማግኘታቸው የ2014 የክረምት ወቅት ድርብርብ ችግር እንደሆነባቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሰዓዳ ከኹለት ዓመት በፊት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ አንገር ጉትን ከተማ ያቀኑት፣ ታጣቂ ቡድኑ በአንድ ወቅት በሀሮ ሊሙ ወረዳ ነዋሪዎች ላይ የግድያ ጥቃት ሲሰነዝር ነበር ይላሉ። በወቅቱ እሳቸውና ቤተሰቦቻቸው ብቻ ሳይሆኑ ቁጥራቸውን በትክክል ባያውቁትም በርካታ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ትተው ወደ አንገር ጉትን ከተማ ሲተሙ ማየታቸው ግን አይረሴ ሆኖባቸዋል።

‹የሚሸሽ ሰው ኮሽ ባለ ቁጥር ልቡ ፍስስ፤ ጉልበቱ ብርክርክ ይላል› ያሉት ባለታሪኳ፤ በተለይም ልጅና አዛውንት ይዞ ሽሽትን ‹እንደ ሬት የሚመር የጉዞ አስከፊ ገጽታ ነው› ሲሉ ገልጸዉታል።

መራር የተባለው ጉዞ ተጠናቀቀ ሲባል የተፈናቃዮች ማረፊያ አለማግኘት ደግሞ ሌላኛው ለተፈናቃዮቹ እስከዛሬ ድረስ ‹ከእሾህ ሸሽቶ ከጋሬጣ› ይሉት ዓይነት ችግር ሆኖ ቀርቷል። ሰዓዳ እንደሚሉት፣ ተፈናቅለው ከቤታቸው ሲወጡ ያንጠለጠሉት ንብረት አልነበረም። የእለት ጉርስ እንኳ ማግኘት ከባድ ነበር። ይባስ ብሎ በአንገር ጉትን ከተማ ደግሞ አንድም የሚያውቁት የቅርብ ዘመድ አልነበራቸውም። ታዲያ በእለቱ ማረፊያ ማግኘት ቸግሯቸው ከመስጊድ ተጠልለው ስለማደራቸውና ለምነው ስለመመገባቸው ባለታሪኳ አልደበቁም።

ባለቤታቸው የቀን ሥራ እየሠሩ የጎዳና ኑሮ ያፈራውን እየተመገቡ ቀናቶች አልፈው ዓመታት ተቆጠሩ። ‹ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል› ይላሉ ሰዓዳ፣ በእንደዚህ ሁኔታ በነበሩበት ወቅት ሌላ ችግር አፍጥጦ መጣባቸው። በቀን ሥራ ተሰማርቶ ሲመግቧቸው የነበሩ ባለቤታቸው ‹ሥራ ጠፋ፣ ጥቃቱም አሁን ትንሽ ተረጋግቷል አሉ። ትንሽ የምንመገበው ላምጣ› ብለው ወደ መኖሪያ ሥፍራቸው አርቁምቢ መንድር አንድ ጊዜ ሄደው ነበር።

ባለቤታቸው እመለሳለሁ ባሉበት ቀን ሳይመለሱ የቀሩባቸውና ስልካቸውም አልሠራ ያላቸው ሰዓዳ ጭንቀት እየተነባበረባቸው ቀናት ተቆጠሩ። በመጨረሻ የሰሙት ግን አስደጋጭ ዜና እንደነበር ባለታሪኳ ሳግ እየተናነቃቸው ይናገራሉ። ባለቤታቸው በታጣቂዎች ተገድለዋል። እናም አሁን በሕይወት ከተለዩዋቸው ድፍን ስምንት ወራት ተቆጥረዋል።

ታዲያ የክረምቱ ብርድና ርሀብ ከመፈናቀልና ከሀዘን ላይ ተጨምሮ ‹ከእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ› እንደሆነባቸው ነው ሰዓዳ የገለጹት። ‹እኔስ አጥንቴ ጠንካራ ነው ግፍ ይችላል፣ በለጋ እድሜያቸው ከዚህ በፊት ፀሐዩ አሁን ደግሞ ብርድና ዝናብ የሚፈራረቅባቸው ልጆቼ ግን ምን እንደማደርጋቸው ግራ ገብቶኛል› ሲሉ በማዘን ይናገራሉ።

እስከ አሁን የሚኖሩት ከቤታቸው በረንዳ እንዲያድሩ በፈቀዱላቸው ቀና ሰዎች ግቢ ውስጥ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ግን ሌላ ተፈናቃይ ዘመድ በመምጣቱ ሲያድሩበት ከነበረው በረንዳ ወጥተው መንገድ ዳር አዳሪ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

በመፈናቀል ላይ ሀዘን፤ ርሃብ የተጋረጠባቸው እንዲሁም በክረምት ወቅት ከመጠለያ ውጪ የሆኑት ሰዓዳ፤ ማኅበረሰቡ እያደረገላቸው ላለው ትብብር አመስግነው፣ መንግሥትም ሆነ ሌሎች እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ቢቻል ወደየቀያቸው እንዲመልሷቸው፣ ካልሆነ ደግሞ ክረምቱ እስከሚያልፍ እንኳ መጠለያ እንዲያዘጋጁላቸው ተስፋ አድርገዋል።

ተፈናቃዮች ከዚህም ከዛም
ሕይወታቸው የአፈሙዝ እራት እንዳይሆን ከቀያቸው በመሸሽ ‹ነገ የተሻለ ይሆናል› የሚል ሙሉ ተስፋን የሰነቁ በርካታ ተፈናቃዮች በኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዘን ከተበታተኑ ውለው አድረዋል።

በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የዜጎች ሞት፤ የአካል ጉዳት፤ መፈናቀል፤ የንብረት ውድመት እንዲሁም ዝርፊያ መቋጫ ያጣ ሰው ሠራሽ ክስተት ሆኗል።

ሰዎች እትብታቸው ከተቀበረበት፤ ወልደው ከሳሙበት፤ ድረው ከኳሉበት፤ የልጅ ልጅ ካዩበት በአጠቃላይ ከልጅነት እስከ አረጋዊነት ከኖሩበት ቀያቸው በማንነታቸው ምክንያት ሲገደሉ፤ ሲፈናቀሉ ይስተዋላል።

በአፋር፤ በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው የነበሩ ሰዎች ወደየቦታቸው ቢመለሱም፤ ገና በስጋት ቀጠና ውስጥ ባሉ አንዳንድ ስፍራዎች ያሉ ተፈናቃዮች በክረምት ወቅት ከመጠለያ ውጪ መሆናቸውና የድጋፍ እጥረት እንዳለባቸው እየተገለጸ ነው።

በተያዘው ክረምት በርካታ ተፈናቃዮች ከመጠለያ ካምፕ ውጪ በመሆናቸው ‹በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ› እንዲሉ፣ ዘርፈ ብዙ ክስተቶች ጠፍረው እንደያዟቸው ችግሩን በመጋፈጥ ላይ ያሉት ሰዎች ይገልጻሉ።

በአማራ ክልል ዋግኸምራ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙና ከዚህ በፊት ቁጥራቸው 72 ሺሕ ለነበሩ ተፈናቃዮች 400 የመጠለያ ድንኳን ቢያስፈልግም፣ ማግኘት የተቻለው 30 ብቻ በመሆኑ የ2014 የክረምት ወቅት ፈታኝ ሊሆንባቸው እንደሚችል ሲገልጹ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።

- ይከተሉን -Social Media

ይሁን እንጂ፣ ስጋታቸው መፍትሄ ባለማግኘቱ የተፈናቃዮች ቁጥር ወደ 90 ሺሕ ከፍ እንዳለና ከእነዚህም መካከል 74 ሺሕ የሚሆኑት በተያዘው ክረምት ከመጠለያ ጣቢያ ውጭ መሆናቸውን ከዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መምሪያ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

የዋግኸምራ ብሔረሰብ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መምሪያ ኃላፊ ሰለሞን ንጉሥ ከኹለት ሳምንት በፊት ለአዲስ ማለዳ በገለጹት መሠረት፤ ከ90 ሺሕ ተፈናቃዮች መካከል በመጠለያ ካምፕ ውስጥ የሚገኙት 16 ሺሕ ሰዎች ብቻ ናቸው።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በዝቋላ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች በበኩላቸው፣ መጠለያ ባለማግኘታቸው በየበረንዳውና ጎዳና ላይ ወድቀው በዝናብ እየበሰበሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከዋግኸምራ ተፈናቃዮች በተጨማሪ፣ በተያዘው የክረምት ወቅት ከመጠለያ ውጪ ሆነው በዝናብ እንዲበሰብሱ የታጣቂዎች ጥቃት መንስኤ የሆናቸው ከወለጋ የተለያዩ ሥፍራዎች ተፈናቅለውና በአንገር ጉትን ከተማ ተበታትነው የሚገኙት ሰዎች ተጠቃሽ ናቸው።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት በአንገር ጉትን ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች እንዳሉት ከሆነ፤ በከተማዋ በግምት በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ቢኖሩም፤ እስከ አሁን ግን አንድም የተዘጋጀ መጠለያ የለም።

ከጊዳ አያና ወረዳ ተፈናቅለው በጉትን ከተማ ከሚገኙት ሰዎች መካከል አንዱ መሆናቸውን የጠቀሱት ሰይድ አደም፤ ከተፈናቀሉ አንድ ዓመት ማስቆጠራቸውን ገልጸው እስከ አሁን ግን አንድም የተፈናቃይ መጠለያ የለም ብለዋል።

ከሀሮ ሊሙ፤ ከጊዳ አያና የተለያዩ ቀበሌዎች ወደ አንገር ጉትን ከተማ ካቀኑ ከኹለት እና ከዛም በላይ ዓመታትን ያስቆጠሩ አረጋዊያን፤ ጨቅላ ሕፃናትን ያቀፉ እናቶች እንዲሁም በርካታ ወጣቶች በመጠለያ እጥረት ውሎና አዳራቸው በረንዳ ላይ ሆኗል ይላሉ ሰይድ።

በኢትዮጵያ በሚገኙ ሌሎች የመጠለያ ጣቢያዎች ይነስም ይብዛ መንግሥትና ሌሎች እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን ማድረጋቸው በተደጋጋሚ ይነገራል ያሉት ተፈናቃዩ፤ ጉትን ከተማ ግን አንድ ጊዜም እርዳታ አልተሰጠም ብለዋል።

- ይከተሉን -Social Media

ተፈናቃዮቹ እንደሚሉት ከሆነ፤ ከመጠለያው በላቀ መልኩ አስከፊ የሆነባቸው የምግብ ድጋፍ አለማግኘታቸው ነው። ሰይድ ከዚህ በፊት የእርዳታ ስንዴ የያዙ በርካታ መኪናዎች ሲራገፉ ማየታቸውን አስታውሰዋል። ነገር ግን ከተራገፈ በኋላ በስፍራው ያሉ ነጋዴዎች ተረከቡት እንጂ ለተፈናቃይ አልተሰጠም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በስፍራው የድጋፍ አገልግሎት ባለመዘርጋቱ አረጋዊያንና እናቶች ብቻ ሳይሆኑ ወጣቶችም በክረምት ወቅት በረንዳ አዳሪ ከመሆናቸውም ባሻገር፣ ሥራ ባለማግኘታቸው ለምኖ ተመጋቢ ሆነዋል።

ሌላው ቢቀር ወጣቶች ሠርተው ይበሉ ነበር ያሉት ሌላኛው ተፈናቃይ ጌትነት ይልማ፤ ሥራ አለመኖሩን ተከትሎ ባሳለፍነው ሐምሌ 19/2014 በአንገር ጉትን ከተማ በሚገኘው የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከአዛውንቶች ጋር ተሰልፈው የሚለምኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን እንዳዩ ተናግረዋል።

በርካታ ሕፃናት፤ እናቶች፤ አዛውንቶች፤ ወጣቶች እንዲሁም አካል ጉዳተኞች በየበረንዳውና በየመንገዱ በዝናብ እየበሰበሱ እንደሚገኙም ጌትነት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

‹‹ተፈናቃዮችን ወደየቀያቸው የማስመለስ ሥራ እየተሠራ ነው ይባላል፣ ነገር ግን በሊሙ ወረዳ እንኳ እስካሁን የተመለሱት የኹለት መንደር ነዋሪዎች ናቸው። ከስድስት በላይ በሚሆኑ መንደሮች የሚኖሩ ሰዎች ግን አልተመለሱም›› ብለዋል። ለአብነትም የመንደር አምስት እና ሰባት ተፈናቃዮች ተመልሰዋል የተባለ ሲሆን፤ ሌሎች ግን አልተመለሱም ብለዋል ጌትነት።

ከመጠለያ እጥረት በተጨማሪ ተፈናቃዮችን እየፈተነ ያለው ሌላኛው ችግር ርሃብ ነው። ርሃብ ከተጋረጠባቸው ተፈናቃዮች መካከል በአማሮ ልዩ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች ተጠቃሽ ናቸው።

በአማሮ ልዩ ወረዳ አጠቃላይ በግጭትና በድርቅ ምክንያት ከ140 ሺሕ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች በረሀብ አደጋ ውስጥ መግባታቸውን የአማሮ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት አደጋ ስጋት አመራር ተቋም አመላክቷል።

በምዕራብ ጉጂ ዞንና በአማሮ ልዩ ወረዳ መካከል በተፈጠው ግጭት አካባቢያቸውን ለቀው የተፈናቀሉት በአጠቃላይ 44 ሺሕ 202 እንደሆኑና እስከ አሁን 10 ሺሕ 962 የሚሆን ሰው በሸራ ውስጥ ከመኖራቸውም በተጨማሪ፣ ከ33 ሺሕ 240 በላይ ሰዎች አቅም ያጣው ተከራይቶ፤ ሰው ተጠግቶ አልያም ቀን ሥራ እየሠሩ መኖራቸውን የልዩ ወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት አደጋ ሥራ አመራር መረጃ ያሳያል።

- ይከተሉን -Social Media

በሰዎች ሕይወት ላይ ፈተና የሆነው ድርቅ ሲሆን፤ በዚሁ ሳቢያ በልዩ ወረዳው 96 ሺሕ 440 ሰዎች ለርሃብ መዳረጋቸው ተመላክቷል። የጃሎ ቀበሌ ሊቀ መንበር ሰብሰቤ ቸርነትና ሌሎች የቀበሌ አርሶ አደሮች የሆኑት ታደለች ተስፋዬ እና ርብቃ አርጓዴ በጋራ በሰጡት አስተያየት፤ በምዕራብ ጉጂ ዞንና በአማሮ ልዩ ወረዳ መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት አካባቢያቸውን ለቀው ከተፈናቀሉና ሸራ ውስጥ መኖር ከጀመሩ ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል።

ከግጭቱም በተጨማሪ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ምርት ወቅቶች ድርቅ፣ የአንበጣ መንጋ እና የተምች ክስተት በመኖሩ አብዛኛው የቀበሌ ነዋሪዎች ቀያቸውን ለቀው እስከ መሰደድ ደርሰዋል ነው የተባለው።

ነዋሪዎቹ በበኩላቸው፣ ያሉበትን የከፋ ሁኔታ በተደጋጋሚ ይናገራሉ። ድርቁ በዚሁ ከቀጠለ በግጭቱ ሳቢያ ከቀበሌያቸው ከሞተው ሕዝብ በላይ በአንድ ጀምበር በርካታ ሰው ሊሞት እንደሚችል የተናገሩት ነዋሪዎቹ፤ አሁን አሁን የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው የሕፃናት፤ አረጋዊያን እና ሴቶች ቁጥር በየጊዜ እየጨመረ መጥቷል ይላሉ።

በመሆኑም፤ መንግሥት እያደረገ ያለው ድጋፍ በቂ ካለመሆኑም በተጨማሪ፣ በግጭቱ ሳቢያ መንገድ ከመዘጋት ጋር ተያይዞ በየጊዜው መቆራረጦች እንዳለ እና በአካባቢው ያለውን የፀጥታ ችግር በመፍታት መንግሥት ወደ ቀያቸው በዘላቂነት እንዲመልሳቸው፤ በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

በ2013/14 ምርት ዘመን የዝናብ ሁኔታ ወጣ ገባ ያለ፤ ነፋስ የተቀላቀለና የተቆራረጠ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ተምች በመከሰቱ ምርቱ ሙሉ በሙሉ መጥፋቱን ተከትሎ ወረዳው በተለይ በቆላማ ቀበሌያት ያሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሕፃናት፤ አረጋዊያንና ነፍሰጡር ሴቶች በከፍተኛ ሁኔታ ለምግብ እጥረት እንደተዳረጉ ነው የተመላከተው።

አሁን ወቅቱ ክረምት መሆኑን ተከትሎ ከመጠለያ ውጭ ላሉት ይቅርና ሸራን እንደ መጠለያ በሚጠቀሙ ተፈናቃዮች ላይም ቅዝቃዜውና ርሃቡ አስከፊ ሆኗል።

ከጊምቢ ቶሌ ተፈናቅለው በመተከል ዞን፤ ከወለጋ የተለያዩ ወረዳዎች ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ከተማ እና በሌሎች ስፍራዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች በበኩላቸው፣ የድጋፍ አቅርቦት ችግር እንዳለባቸውና መፈናቀሉ ከክረምቱ ጋር ተዳምሮ ሕይወታቸውን እንደፈተነው ሲያወሱ ይደመጣሉ።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የብሔራዊ አደጋና ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ደበበ ዘውዴ የቻሉትን እየረዱ መሆኑን ገልጸው፤ ሚዲያዎች ግን ይህን ያህል ተፈናቀለ፤ ይህን ያህል ተራበ የሚለውን ወሬ ከማናፈስ ውጭ ሌሎች አካላት መንግሥትን እንዲረዱ ምንም የሠሩት ሥራ የለም ብለዋል። ኃላፊው ተፈናቃዮች የሚያነሷቸው የእርዳታ ጥያቄዎችን በተመለከተ ምላሽ መስጠትን በተመለከተ ፈቃደኛ አልሆኑም።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢያሱ መስፍን በበኩላቸው፣ በክልሉ 36 የመጠለያ ጣቢያዎች እንዳሉ ገልጸው፤ ድጋፉን በተመለከተ ግን ገና ከፌደራል የሚሰጣቸውን መመሪያ እየተጠባበቁ በመሆኑ ዝርዝር ሐሳብ እንደማይሰጡ ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።


ቅጽ 4 ቁጥር 195 ሐምሌ 23 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች