የአልኮል ጎጂነት ከሚጠጣበት እድሜና ቦታ አኳያ

0
1497

አልኮል የሚጠጣበት እድሜና ቦታ ጎጂነቱን ይወስነዋል የሚል ጥናት ከሰሞኑ ይፋ ሆኗል። የሰው ልጅ እህልን አምቆና አብላልቶ አልኮል መጠጥን ጠምቆ መጠጣት ከጀመረ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ሰክሮበት ሲያፍርበት እንዲሁም ደስታውንም ሲያደምቅበት ቆይቷል።

በዘመናዊ መልክ መጠመቅ ከመጀመሩ አስቀድሞ የተለያዩ ዓይነት መጠጦች በየአገሩ ሲጠጡም ነበር። የአገራችንን ብናነሳ እንኳን ወይነጠጅን በእድሜ የሚደርስበት እንደሌለ ድርሳናት ይጠቁማሉ። ይህ መጠጥ ግን እንደ አሁኑ ከወይን ወይም ከጌሾና ማር ለየብቻ የሚጠመቁትን ሥሙን ከፍለው ይዘው የቀሩት የመጠጥ ዓይነቶች ጋር አንድ አልነበረም ይባላል።

የጥንቱ የወይን ዘለላና ማርን በአንድ ላይ በማዋሐድ ታሽቶ ለአንድ ወር ያህል ታሽጎ እንዲብላላ ከተደረገ በኋላ ይጠጣ ነበር። በእንዲህ ዓይነት መንገድ የተጠመቀውን አልኮል ነበር በሀይማኖት መጻሕፍት ላይ ተጠቅሰው የሚገኙት እነ’ኖህ በየወሩ ጠምቀው ይጠጡ የነበረው ተብሎም ይነገራል።

አልኮል በሰው ሠራሽ መንገድ ብቻ የሚገኝ አስካሪ መጠጥ አይደለም። በተፈጥሮ ሂደት እንደሰው ሠራሾቹ የሚያሰክሩ እጽዋት አሉ። ከእነሱ መካከል የማሩላ ፍሬ (Marula friut) የሚባል አፍሪካ ውስጥ የሚበቅል ዛፍ ፍሬው ሲበስል በመበስበስ ፋንታ ስለሚታፈን አልኮል ፈጥሮ መሬት ላይ ይወድቃል። ይህን ጣፋጭ አስካሪ ፍሬ ከስጋ በሎች በስተቀር ያገኘው እንስሳ ሁሉ ስለሚበላው እለቱን ሰክሮ ሲወላገድ ይታያል።
ይህን የተመለከቱ ተመራማሪዎች የእንስሳቱን ተግባርና ምርጫቸውን ሲያጠኑ፣ ሰው ብቻ ሳይሆን አራዊቱም የመስከር ፍላጎትና ዝንባሌ እንዳላቸው ለማወቅ ችለው ነበር።

አልኮል መጠጣት ጎጂ ነው ብለው በሀይማኖታቸውም ሆነ በባህላቸው የሚከለክሉ ማኅበረሰቦች ቢኖሩም፣ በአብዛኛው ኅብረተሰብ ዘንድ ግን እስከ አሁን ተቀባይነቱ ከፍተኛ እንደሆነ ቀጥሏል። አልኮል ለጤና ተስማሚ ነው ብለው ካልበዛ የምግብ መፈጨት ሂደትን ያቀላጥፋል የሚሉ የመኖራቸውን ያህል፣ ሲበዛ ጉበትን ይጎዳል፣ ሱስ ሲሆንም ማኅበራዊ ሕይወትን ያበላሻል በሚል ብዙዎች ሲነቅፉት ይሰማል።

ይህ ቢሆንም ግን፣ የመጠጡን ዓይነትና ብዛት እያስቀመጡ ጎጂነቱንና ጠቃሚነቱን ለማሳየት ከመሞከር ውጪ የሚጎዳው የማኅበረሰብ ክፍል የትኛው ነው፣ አልያም የት አካባቢ እየኖሩ የሚጠጡ ሰዎች ላይ ምን የተለየ ተፅእኖ ያሳድራል በሚል የተለየ ጥናት ሲደረግ ተሰምቶ አይታወቅም ነበር።

ስለአልኮል ይህን ያህል ያልናችሁ ከሰሞኑ ይፋ የሆነና መነጋገሪያ የሆነ ጥናት ስለአልኮል ከዚህ ቀደም ይታመን የነበረን አመለካከት የሚቀይር የግኝት ውጤትን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ነው። ‹ዘ ላንሰንት› ላይ የወጣው ይህ የሰሞኑ ጥናት ውጤት እንደሚያትተው፣ አልኮል የሚጠጡ ሰዎች ጉዳታቸው እንደእድሜ ልዩነታቸው እንደሚለያይ ነው።

በወጣትነታቸው ከሚጠጡት ይልቅ እድሜያቸው ሲገፋ የሚጠጡ ተጎጂነታቸው ይቀንሳል በማለት፣ እድሜ ማነስ ለተጎጂነት ያጋልጣል ሲል ድምዳሜውን ተናግሯል። ይህ ግኝትም በተለምዶ እድሜው የገፋ ሰው አልኮል መጠጣት የለበትም የሚለውን አመለካከት የሚቃረን እንደመሆኑ፣ ወጣቶች ላይ የሚስተዋለውን አዘውትሮ የመጠጣት ባህል ይቀንሳል ተብሎለታል።

በጥናቱ መሠረት መጠጥ የሚጠጡ ከ40 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች የበለጠ ጤናቸው ተጎጂ ሊሆን ይችላል የተባለ ሲሆን፣ ግኝቱን የበለጠ አጨቃጫቂ ያደረገው ጠጪዎቹ ወንዶች ሲሆኑ ደግሞ ይበልጡኑ ተጎጂ ይሆናሉ መባሉ ነው። አልኮሉ መጠጣት ያለበት ከእድሜ ፆታና ከሚኖሩበት ቦታ አኳያ እየታየ ነው መመከር ያለበት የሚለው ጥናቱ፣ ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች የተጎጂነታቸው መጠን የቀነሰ ይሆናሉ ብለዋል።

ከ15 እስከ 39 ዓመት ውስጥ ያሉ አልኮል የሚጠጡ ወንዶች በዓለም ዙሪያ ይበልጥ ጤናቸው ተጎጂ እንደሆነ ተመራማሪዎቹ በጥናት አረጋግጠናል ማለታቸው በሌሎች ሳይንቲስቶች ዘንድ እንዲነቀፉም አድርጓቸዋል።

ምንም ዓይነት የጤና እክል የሌለባቸው ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ሳያበዙ አነስተኛ መጠን ያለው አልኮል የሚጎነጩ ከሆነ በመጎዳት ፋንታ ይልቁንም ለጤናቸው ይጠቅማቸዋል ተብሏል። በተለምዶ አንድና ኹለት እየተባለ የሚነገረውን መጠን ያህል የሚጠጡ ሰዎች፣ በልብ በሽታና በስኳር በሽታ የመጠቃታቸውን እድል ስለሚቀንስላቸው ተጠቃሚ ይሆናሉ ሲሉ ሳይንቲስቶቹ አብራርተዋል።

204 አገሮች ውስጥ ያለውን የአልኮል አጠቃቀም መረጃ ካሰባሰቡ በኋላ አገናዝበው መረዳት እንደቻሉት፣ በፈረንጆቹ 2020 ብቻ ከዓለማችን ሰዎች 1 ነጥብ 34 ቢሊዮን የሚሆኑት አልኮልን በጎጂ መጠንነት ወስደውት እንደነበር ነው። በየትኛውም አልኮል በሚዘወተርባቸው ክፍለ ዓለሞች ጤናቸውን በሚጎዳ መጠን አልኮልን የሚጠጡት እድሜያቸው ከ15 እስከ 39 ዓመት ያሉት መሆናቸውንም ማወቅ ችለዋል።

በወጣትነት እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎች አነስተኛ መጠን ያለው አልኮል በመጠጣታቸው ከሚያገኙት ጥቅም ይልቅ የሚጎዱት መጠን ከፍተኛ እንደሆነ ተመዝግቧል። በዚህ እድሜ ውስጥ ሆነው ብዛት ያለው አልኮል ከመጎንጨታቸው በላይ 60 በመቶ የሚሆነው ጉዳት በእነሱ አማካኝነት የሚከሰት ነው ተብሏል። የመኪና አደጋ፣ ራስን ማጥፋትና ግድያን የመሳሰሉ ወንጀሎችን ከሚፈፅሙ መካከል አብዛኞቹ ወጣት ጠጪዎች መሆናቸውን መረጃዎች እንደሚያመለክቱም ተጠቅሷል።

ወጣቶችን አትጠጡ ብሎ መከልከል ከባድ እንደሆነ የተናገሩት ተመራማሪዎቹ፣ እንደትልልቆች ቢያንስ አነስተኛ መጠንን እንዲወስዱ ማድረግ ቢቻል መልካም ነው ይላሉ። ይህ ካልተሳካም ቢያንስ በጤናቸውና በማኅበረሰቡ ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን ጉዳት አውቀውት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መምከሩ ተገቢ እንደሆነ አመላክተዋል። እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆናቸው ሊጎዱ የሚችሉት ከተለመደው ሦስት መጠን በላይ የሚጎነጩ ከሆነ እንደሆነም ተናግረዋል።

ከእድሜ አኳያ የጥናቱ ግኝት የጠቆመውን ምልከታ ብዙዎች ቢቀበሉትም፣ ከቦታ አኳያ ጎጂነቱ ይለያያል መባሉን ግን ብዙዎች ተችተዉታል። በተለይ የእንግሊዝ ተመራማሪዎች ከአገር አገርና በየክፍለ አኅጉሩ ይለያያል ብሎ ዝርዝሩን ለሕዝብ ይፋ ማድረጉ በራሱ ሊጎዳ ይችላል ባይ ናቸው። አገራቱን ሳያማክሩ እንዲህ ዓይነት ውጤት ላይ ተመርኩዞ ድምዳሜ ላይ መድረሱ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚሻ ጉዳይ ነው ማለታቸውን ኢመርጂንግ ሪስክስ አስነብቧል።

የተለመደ አንድ መጠጥ እየተባለ ጥናቱ ላይ የተመላከተው የአልኮል መጠን ከአገር አገር እንደሚለያይ ተጠቁሟል። በምዕራቡ ዓለም ያለ የአልኮል የተለመደ መጠን በእስያና በምሥራቅ አውሮፓ ካለው እንደሚለያይ የተነገረ ሲሆን፣ የምዕራባውያኑ ያነሰ እንደሆነም ተመላክቷል። ይህን ሁኔታ በአገራችን ኢትዮጵያ እንኳን ከተመለከትነው እንደማኅበረሰቡና እንደአካባቢው ብርዳማነት የአልኮል ተጠቃሚው ቁጥርና የሚጠቀመው መጠን እንደሚለያይ ግልፅ ነው።

የጥናቱ ዋና ዓላማ የአልኮል አጠቃቀም እንደ እድሜ ልዩነት ጎጂነቱም ይለያያል የሚል ሲሆን፣ አወሳሰዱም ሆነ መጠኑ እንደ እድሜው ይለያያል መባሉ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሏል። ነገር ግን ይህ የሰሞኑ ጥናት ከዚህ ቀደም በዓለም ደረጃ የነበረውን ምልከታ የሚያጠናክር አይደለም ሲሉም ገልፀውታል።

በፈረንጆቹ 2016 በተወሰደ ጥናት በዓለም ዙሪያ ከአልኮል መጠጥ ጋር በተገናኘ ከሞቱ ሰዎች መካከል 150 ሺሕ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ15 እስከ 29 የሚሆኑ ናቸው። አልኮልን በማብዛታቸው ከሞቱት 900 ሺሕ የሚሆኑት ደግሞ እድሜያቸው 60 እስከ 74 የሚሆኑ መሆናቸው ተመላክቷል። ይህ ቢሆንም፣ ምን ያህል መጠንን ወስደው ምን ያህሉ በጤናቸው ላይ ጉዳት አምጥተዋል ወይም ለአደጋ ተጋልጠዋል የሚለውን የአሁኑ ጥናት በዝርዝር አልጠቆመም።

ይህ የአሁን ግኝት ለወደፊት በዘርፉ ለሚደረጉ ጥናቶች በር የሚከፍትና ለተጨማሪ ምርምር ግብዓት እንደመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው ቢባልም፣ ትችት የሰነዘሩበት በበኩላቸው የአንዳንድ አገራትን ምሳሌ በማቅረብ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ውጤቱ ተቀባይነት እንዳይኖረው የሚያደርግ ማስረጃን ለማቅረብ ሞክረዋል።

የጥናቱ ውጤት የአልኮል አጠቃቀም ገደብና መጠን እንዲኖረው ስለሚያደርግ መጠኑ በዛም አነሰ፣ በየትኛውም የእድሜ ክልል ውስጥ ያለ ሰው አብዝቶ መጠጣት እንደሌለበት ይመክራል። አዛውንቶች በመጠኑ መውሰዳቸው ለጤናቸው ይጠቅማቸዋል ማለትና አይጎዳቸውም ማለቱ ስለሚለያይ፣ የጥናት ውጤቱን ሙሉ በሙሉ መቀበል ሳይሆን ይበልጥ መመርመር ያስፈልጋል ሲሉ ይፋ የሆነው ግኝት ላይ ተመርኩዘው አስተያየት የሰጡ ባለሙያዎች ምክራቸውን ለግሠዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 195 ሐምሌ 23 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here