መነሻ ገጽርዕስ አንቀፅስህተትን አትድገሙ!

ስህተትን አትድገሙ!

በኢትዮጵያ ለበርካታ ሺሕ ዓመታት ሕዝቡ ተቻችሎም ሆነ ተገፋፍቶ እስካሁን ባለበት እንዲቆይ ካስቻሉት ምክንያቶች መካከል ቀዳሚው የሥርዓተ መንግሥቱ አስተዳደር እንደሆነ ይታመናል። በሌላው ዓለም አንዱ በሌላው እየተዋጠና እየተገዛ ሲኖር፣ የራስ ማንነት በአንፃራዊነት ጠፍቶ ወጥ የሆነ ባሕልና ማኅበረሰብ ለአገረ መንግሥት ምሥረታ መነሻ መሆኑን መመልከት ይቻላል።

የኢትዮጵያን የቀደመ ታሪክ በተለያዩ ዘመናዊ አስተሳሰብ መስፈርቶች መዝነው የሚኮንኑም ሆነ የሚተቹ የመኖራቸውን ያህል፣ አስተያየታቸውን እዚህ ዘመን ላይ ደርሰው እንዲሰጡ ላስቻሏቸው ለቀደሙት ትውልዶች ምስጋና ማቅረብ እንደሚያስፈለግ የሚናገሩ አሉ።

ያለፈ ታሪክ ሁሉ በጎ ብቻ አልያም መጥፎ ብቻ ሊሆን እንደማይችል ሁሉ፣ በየዘመኑ ፈተናና ተፈታኝ እንደማይጠፋው ጥሩም መጥፎም የሠራ እንዳለ ይታወቃል። የታሪክ ትምህርት የሚሰጠውና አስፈላጊ ነው የሚባለውም ሰው ካለፈ ስህተት ተምሮ እንዳይደግመውና መልካም ተሞክሮንም ወስዶ እንዲማርና እንዲያስፋፋው መሆኑ ግልፅ ነው።

የቀደመ ታሪክ ይቅርና የቅርቡ በሕይወት ዘመናችን የተፈፀመ ስህተት እንዳይደገም መሥራት፣ ሲፈፀምም ካየን የማስጠንቀቅ ኃላፊነት የኹላችንም እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች።  የቀደመውም ሆነ የአሁኑ ሥራችን ለትውልድ ተጽፎ የሚያልፍበት ሌላ ምክንያትም እንደሌለው አውቀን ከሰው ስህተት ብንማር ለኹላችንም መልካም ነው።

ያለፈ ስህተትን ከሠራ አካል ሌላው ዐይቶ መማር ወሳኝ ነው። የኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ መሪዎች፣ እንደቀደሙት በልጅነታቸው ያለፉ መሪዎቻቸውን ታሪክ ከክብረ ነገሥትም ሆነ ከፍትሃ ነገሥት ላይ የመማራቸው እድል በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ፣ የቆየን ቀርቶ የዘመናቸውን ስህተት ራሳቸው የሠሩትንም ጭምር ሲደግሙት ይስተዋላል።

ይህን ያስባለን ከሠሞኑ ከክልል አደረጃጀት ጋር በተገናኘ በኢሕአዴግ ዘመንም ሆነ በብልፅግና አጭር እድሜ የተሠሩ ስህተቶች ሊደገሙ ጫፍ ተደርሶ እየተመለከትን ስለሆነ ነው። ለሺሕ ዘመናት የቆየው የአስተዳደር ወሰን ዓላማው ሰው በፈለገበት እየኖረ ለአቤቱታም ሆነ ለግብር አከፋፈል የቅርብ አስተዳዳሪ እንዲያገኝ ነበር።

አንድ ሰው በሆነ ግዛት ሲተዳደር ግፍ በቅርብ ሹመኞች ቢፈፀምበት ለግዛቱ አስተዳዳሪ አቤት ለማለት በአማካይ ቦታ የግዛቱ መሪ መቀመጫ እንዲሆን ይደረግ ነበር። ቢርቅ ቢርቅ፣ አቤት ባዩ ማደር ሳይኖርበት በፈረስ ግልቢያ ደርሶ መመለስ በሚችልበት አማካይ ቦታ ከተማ እንዲቆረቆርም ይደረግ ነበር። ይህ ተገልጋይን ማእከል ያደረገ የመሬት አከፋፈል የነዋሪውን ማንነት መሠረት ያደረገ ሳይሆን ተፈጥሮንና ቅርበትን ያማከለ ነበር።

ይሁን እንጂ ይህ ለዘመናት ሲያገለግል የነበረና ኅብረተሰቡን አስተሳስሮ ከሌላው ዓለም ነዋሪ የተለየ ቅልቅል ሕዝብ ያስባለው የአስተዳደር አከፋፈል፣ ከቅርብ ዐስርት ዓመታት ወዲህ ዓላማውን ባላወቁ ቡድኖች ከጥቅም ውጭ ሆኖ እንዲቆይ መደረጉ አይዘነጋም። ይህን ተከትሎ ማንነትና ዘር ላይ መሠረት ያደረገ ብሔር የተባለ ሥም ተሠጥቶት ቦታንና ሕዝብን ለመከፋፈል ምክንያት መሆኑ የሚታወቅ ነው።

ይህ የዘር ፌዴራሊዝም እንደታሰበው ተግባራዊ ሊደረግ ስላልተቻለ ከ50 በላይ የሚሆኑ ጎሳና ነገዶችን በአንድ ጨፍልቆ በየአቅጣጫ ሥም ተሰይመው እንዲኖሩ ተደርጎም ነበር። ይህ የቅርብ ጊዜ ስህተት እየታወቀ ሳይስተካከል ለዓመታት ደም እያፋሰሰ ቆይቶ አሁንም መዘዙ መቀጠሉን አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።

የክልል ወይም የዞን እንሁን ጥያቄ መነሳት የጀመረው አከላለሉ ከጀመረበት ወቅት ጀምሮ ቢሆንም፣ እስከ አሁን ወደነበርንበት እንመለስ፤ ክልልም እንሁንና ወደዞን እንደግ የሚሉ ጥያቄዎች መነሳታቸውን አላቆሙም።

ለውጥ መጣ ተብሎ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት እርስ በእርሳቸው ተከፋፍለው ሥም ለውጥ ካደረጉ በኋላ በአስተዳደር ዙሪያ የተነሱ ጥያቄዎች እንደ አዲስ አገር ሽተዋል። ከሁሉም በቀዳሚነት የሚነሳው የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ ሲሆን፣ ፍላጎቱ በቀረበበት ወቅት በተገቢው ፍጥነትና ሕጋዊ መስመር ምላሽ ባለማግኘቱ ያስከተለው ሞትና የንብረት ውድመት እስካሁን የሚረሳ አልነበረም።

ከሲዳማው ችግር ያልተማረው መንግሥት በቀጣይነት እንደአፈል የበዙበትን ጥያቄዎች በጊዜ መመለስ ሳይችል አሁንም ለሌላ ዙር እልቂትና ውጥረት ሕዝቡን ዳርጓል። እንደአዲስ ማለዳ እምነት ሕዝብ ፍላጎቱን በሕጋዊ መንገድ ማቅረብ እንደሚጠበቅበት ሁሉ መንግሥትም ማስፈራሪያ ሳይሆን ተገቢውን ምላሽ ሊሰጥ ይገባዋል።

ለአንዱ ተፈቅዶ ለሌላው መከልከል የለበትም በሚል እሳቤም ይሁን በሌላ ይገባኛል ብሎ ትክክለኛውን የማቅረቢያ መንገድ እስካልጣሰ ድረስ ጫና በመፍጠርና እኔ አውቅልሃለሁ በሚል የዜጎች ፍላጎትን መጫን እንደማይገባ ግልፅ ነው።

ኢሕአዴግ ደቡብ ብሎ ሳይጠይቁ እንደጨፈለቃቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ አሁንም የተወሰኑ ማኅበረሰቦችን ከፍሎ ክላስተር በሚል ለፈንጂ የተለመደ ሥምን ሰጥቶ በአንድ ላይ መጠርነፉ ቢሳካ እንኳን፣ የጊዜ ጉዳይ እንጂ እንደአሁኑ ለወደፊትም ቢሆን መፈንዳቱ እንደማይቀር ሊታወቅ ይገባል።

ወለጋ ክልል ይሁን ተብሎ በተነሳ ጥያቄ “የኦሮሞ ሕዝብ አይከፋፈልም” በሚል አስተሳሰብ የመጣው እልቂትም አሁን ድረስ ካለመቆሙ መንግሥት ተምሮ አስፈላጊውን ውሳኔ በጊዜ ማድረግ ይጠበቅበታል።

“የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም” እንደሚባለው፣ መንግሥት ሌላ ላይ ሳይሆን ራሱ ላይ ያለውን የመቀመጫውን ያልደረቀ ቁስል ተመልክቶ እንዳያመረቅዝ ሊንከባከበውና ሌላ እንዳያቃጥለው ሊጠነቀቅ ግድ ይላል። እንዲህ ዓይነት የክልል ጥያቄዎች በጉራጌ ሕዝብና በሌሎችም ከ10 በላይ በሚሆኑ ማኅበረሰቦች እንደቀረበ የሚታወስ ቢሆንም፣ የተወሰኑት በክላስተር ሆነው ክልል ለመሆን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ ማቅረባቸው ተነግሯል።

- ይከተሉን -Social Media

ይህ የመብት ጥየቃ ሂደት በሥርዓቱና በሕገ መንግሥት መሠረት ያለምንም ደም መፋሰስ ተግባራዊ ቢደረግ መልካም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን፣ ለሁሉም ሊሰጥ የማይቻል ነው የሚል አመለካከት ካለ፣ በዘፈቀደ ለአንዱ ሰጥቶ ሌላን ከመከልከል ለዚህ መዘዝ የዳረገውን ሕገ መንግሥት ማገድ አልያም ማሻሻል አማራጭ መሆኑ ሊታሰብበት ይገባል።


ቅጽ 4 ቁጥር 196 ሐምሌ 30 2014

 

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች