መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛየደንብ ነው ወይስ የዳንስ ልብስ?

የደንብ ነው ወይስ የዳንስ ልብስ?

ከሠሞኑ በማኅበራዊ ሚዲያ እየተዘዋወረ የብዙዎችን ትኩረት የሳበ አንድ ምስል አለ። አንዲት የመጠጥ ቤት አስተናጋጅ ትሪ ሙሉ መጠጥ ይዛ በዝናብ ውጪ ላሉ ተስተናጋጆች ስታደርስ የሚያሳይ ምስል ነው። ምስሉ የተነሳበት ወቅት ክረምት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ዝናብም በከባዱ እየወረደ የነበረበት ጊዜ ነበር።

በዚህ ብርዳም ወቅት ውጪ ላለ ደንበኛ መጠጥ እንድታደርስ በባለቤቶቹ ተገዳ ይሁን ወይም መታገስ ያልቻሉ ተስተናጋጆች አዋክበዋት ይሁን ባይታወቅም፣ ልጅቱ ዝናብ እየወረደባት ስታደርስ በአንድ ደንበኛ ፎቶግራፍ ልትነሳ ችላለች። ብዙዎች ይህንን ምስል ሲያዩ በሀዘኔታ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን፣ በዝናብ ማን አስገድዷት ነው የሚለው ሳይሆን የብዙዎች ጥያቄ አለባበሷ ላይ ነበር።

በወጣትነት እድሜ ክልል ላይ የምትገኘው ይህች ሠርቶ አደር እንድትለብስ የተደረገው በጣም አጭር የሚባል ጉርድ ቀሚስ ነበር። ልጅቱ በፍላጎቷ ያንን ቀሚስ በዚህ ክረምትና በብርድ ለብሳ እንደማትወጣ ለማንም ግልጽ ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንዲህ ዓይነት ቤቶች ሠራተኞቻቸውን “የደንብ ልብስ” ብለው በግድ ማልበስ እንደጀመሩ ይታወቃል። የሚያለብሷቸው ዓይነት እንደንግድ ተቋሙ የሚለያይ ይሁን እንጂ፣ የመጠጥ መስተንግዶ የሚሰጡት አጭር ቀሚስ በማስለበስ ይታወቃሉ።

ከዚህ ቀደምም እንዲህ የሚያደርጉ ባለቤቶች ላይ በዘመቻ መልክ ተቃውሞ ተደርጎ የሚያውቅ ቢሆንም፣ ለውጥ ባለማምጣቱ ብሶበት ምሽት ላይ ይዘወተር የነበረው አሁን አሁን እንደልጅቷ በቀኑም ያስለብሷቸው ጀምረዋል። ይህን ሰውነትን እንደሸቀጥ አድርጎ ማሻሻጫ ማድረግን የሴቶች መብት ላይ የሚሠሩ ተቋማትም ሆኑ ታዋቂ ግለሰቦች እንደ አሁኑ ቢተቹትም፣ እስከ አሁን ሊቀር አልቻለም።

እንደአንዳንዶች አስተያየት አስገዳጅ ሕግ ማውጣትና አማራጭ አጥተው አካላቸው መነገጃ የሚደረግባቸውን መከላከል እንደሚገባ ነው። በሌላ በኩል፣ ሕግ ብቻውን ውጤታማ ስለማይሆን ኅብረተሰቡ እንዲህ ዓይነት ተግባር በሚፈፅሙ ተቋማት ገብቶ እንዳይጠቀም ቅስቀሳ ማድረግና አድማ እንዲደረግባቸው ማስተባበር ያስፈልጋል የሚሉ አሉ።

የእንዲህ ዓይነት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለቤቶች፣ ዝቅተኛ የሚባለውን ክፍያ እያገኙ ሕይወታቸውን ለመምራት የሚጥሩ እንዲህ ዓይነት ወጣት ሴቶች ደንበኞቻቸውን ለማማለያ እንዳይጠቀሙ የሚያደርግ  ተመሳሳይ ውሳኔም በራሳቸው በማሕኅበራቸው በኩል ቢወስኑም መልካም እንደሆነ የተናገሩ አሉ።

በብርድ እየተንዘፈዘፉ ዝናብ እየወረደባቸው አጭር ቀሚስና ብጫቂ ጨርቅ ከላይ አድርገው ሕይወታቸውን እንዲገፉ የሚደረጉ ሴቶች ጉዳይ የሚገባውን ትኩረት እንዳላገኘ ብዙዎች ጽፈዋል። በየጎዳናው አካላቸውን ሸጠው የሚያድሩ እንኳን በብርድ የማያደርጉትን  አለባበስ፣ እንዲህ ሥራ ሠርተው የሚያድሩ ሴቶች ላይ ማድረጉ፣ ከነውርም በላይ ግፍ በመሆኑ ባለቤቶቹ ብቻ ሳይሆኑ እዛም ሄደው የሚገለገሉ ሊወገዙ እንደሚገባ የብዙዎች አስተያየት ነበር።


ቅጽ 4 ቁጥር 196 ሐምሌ 30 2014

 

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች