መነሻ ገጽዜናወቅታዊደም ልገሳ እና እጥረቱ

ደም ልገሳ እና እጥረቱ

ከወለዱ ከትንሽ ቆይታ በኋላ ከአልጋቸው ወድቀው ወለሉ ላይ ተዘርረው ነበር። በሞትና በሕይወት መካከል ሆነው ‹ልጄስ? ወልጃለሁ አይደል?› ይላሉ። ግን ደግሞ በሰመመን ውስጥ ሆነው ግራ ቀኝ ጎናቸውን ሲያስሱም አጠገባቸው ማንም የለም። በዚህ ሁኔታ እያሉ እንደህልም መሰላቸው እና ‹ምን ሆኜ ነው? የት ነው ያለሁት?…› አቅም ስላነሳቸውና ራሳቸውን ስለሳቱ በወቅቱ ምላሽ ያላገኙለት ለራሳቸው የጠየቁት የራሳቸው ጥያቄ ነበር።

ያለምእሸት ውቡ ይባላሉ። በወሊድ ወቅት ብዛት ያለው ደም ስለፈሰሳቸው ከሞት አፋፍ ደርሰው ተመልሰዋል። ባለታሪኳ ቤተሰቦቻቸው እንኳ ደም ለመለገስ ፈቃደኛ መሆን ተስኗቸው እንደነበር አስታውሰው፣ ማን እንደለገሳቸው እና እንዴት ሕይወታቸው እንደተረፈ ለአዲስ ማለዳ ኹነቱን በዝርዝር ተናግረው ምክራቸውን ለግሰዋል።

ያለምእሸት ከእለታት በአንደኛው ቀን ከሚኖሩበት የገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል ወደ ናዝሬት አዳማ ከተማ ለማቅናት ተገደው ነበር። ለጉዟቸው አስገዳጁ ጉዳይ ወሊድ ነው። በመሆኑም፤ ከሚኖሩበት አካባቢ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ጤና ጣቢያ የወሊድ አገልግሎት ለማግኘት አቅንተው፤ በሰላም ቢገላገሉም ሌላ ችግር ገጠማቸው።

ችግሩ በወሊድ ጊዜ ብዙ ደም መፍሰስ ነው። ከዛም ብሶ ለጋሽ አለማግኘት ፈተና መሆኑን ከሰመመን ከነቁ በኋላ የነበሩበትን ኹነት ዶክተራቸው እንዳጫወቷቸው እያስታወሱ ነው ያለምእሸት ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።

ነገሩ እንዲህ ነው የሆነው። ያለምእሸት ልጃቸውን ከወለዱ በኋላ ከማዋለጃ ክፍሉ በሚገኘው አልጋ ጋደም ብለው ነበር። ያዋለዷቸው ዶክተር ወደ ሌላኛው ክፍል አመሩ። አብረው ወደ ጤና ጣቢያው ያቀኑት ቤተሰቦቻቸውም በሰላም መገላገላቸውን ተበስረው የምሥራቹን ለሌሎች ሰዎች እየደዋወሉ በመግለጽ ላይ ስለነበሩ ባለታሪኳ ከተገኙበት ክፍል ማንም ሰው እንዳልነበረ ያወሳሉ።

ከገጠሩ አካባቢ ወደ ጤና ጣቢያው ካቀኑት ሰዎች መካከል ከግቢው ውጭ ወጣ በማለታቸው የምሥራቹን ያልሰሙ አንዲት እህታቸው ያለምእሸት ወደተኙበት አልጋ በገቡበት ወቅት አስደንጋጭ ነገርን ተመለከቱ። ያለምእሸት ከተኙበት አልጋ ተንሸራተው ወለል ላይ ተዘርረው አገኟቸው። ጠጋ ብለው ሲመለከቷቸው ትንፋሻቸው ብን እያለ የነበረ ሲሆን፤ ከዚህም በላይ በደም ተለውሰው መገኘታቸው በወቅቱ የተፈጠረ ይበልጥ አስደንጋጭ ክስተት ነበር።

ያለምሸትን ወድቀው ያገኟቸው እህታቸው ‹ኧረ ድረሱልን›  የሚል ጥሪ አሰሙ። የእርዳታ ጥሪ የሰሙ ሁሉ ወደ ክፍሉ ተዥጎድጉደው መግባታቸውን ተከትሎ፣ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ክፍሉ በዋይታ ጩኸት እየተናጠ መቆየቱን ቤተሰቦቻቸው እንደነገሯቸው ይገልጻሉ።

ይሁን እንጂ በመካከላቸው ያለው ዶክተር ጩኸቱ መቆም እንዳለበትና ሰዎቹ ከክፍሉ እንዲወጡ አዘው የሕክምና እርዳታ ተጀመረ። ታዲያ ያለምእሸት ከፍተኛ ደም ፈሷቸው ነበር የተገኙት። ይህን የተረዱት ዶክተር የአራሷን ሕይወት ለማትረፍ ደም የሚለግስ አካል እንደሚያስፈልግ በማመን ለቤተሰቦቻቸው ጥሪ አቀረቡ።

ይባስ ብሎ ግን ደም ለመለገስ ፈቃደኛ የሆነ ሰው አልነበረም። በመጨረሻም ዶክተሩ አንድ ዩኒት ደም ለግሰው ያለምእሸትን በደም እጥረት ሊያልፍ የነበረ ሕይወታቸውን ሊታደጉ ቻሉ። ይህ በመሆኑ ከሞት ተርፈው ዘጠኝ ወር በማኅጸናቸው የተሸከሙትን ልጃቸውን ለማቀፍ በቅተዋል።

ኹነቱን ከላይ በተዘረዘረው መልኩ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት ያለምእሸት፣ ደም መለገስ መታደግ የሚያስችለው የእናቶችን ሕይወት ብቻ ሳይሆን የሕጻናቱንም ጭምር ነው። በመሆኑም ማኅበረሰቡ የመለገስ ልምዱ ሊዳብር ይገባል ነው ያሉት።

ደም መለገስ በማኅበረሰቡ ዘንድ እንደሚፈራው አይደለም ሲሉ የመሰከሩት ያለምእሸት፣ ‹‹ደም በሚለግሰው አካል ምንም የሚከተል ጉዳት የለም። ባለመለገስ ውስጥ ግን የሰዎች ሕይወት ያልፋል።›› ሲሉ ልዩነቱን አስረድተዋል። እናም ለመለገስ ብቁ የሆነ ሰው ሁሉ ወደኋላ ማለት እንደሌለበት ነው ምክር አዘል አስተያየታቸውን የሰጡት።

በርካታ ሰዎች ደም የሚለግሳቸው አጥተው ሕይወታቸው እንደሚያልፍ ይነገራል። ታዲያ ችግሩ የሚፈጠረው ደም በመለገስ ሕይወትን ማትረፍ እየተቻለ የሚለግስ አካል ወደኋላ በማፈግፈጉ እንደሆነም በተደጋጋሚ ይወሳል።

ስለሰሞንኛው ውዝግብ በጥቂቱ

የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት፣ በየክልሉ የሚገኙ ባንኮች እጥረት እንዳለባቸው ይገልጻል። ማኅበረሰቡ በበኩሉ ‹የሚለገሰውን ደም የት እያደረሱት ነው?› የሚል የጥርጣሬ መንፈስ ያዘለ ጥያቄ  ሲያነሳ ይስተዋላል።

በወሊድ ጊዜ በሚፈስ ደም ምክንያት የአንድ ሰው ሕይወት ማለፍ እንደሌለበት ያመኑና የበጎነት ምስጢር የገባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ደም ከመለገስ ወደኋላ ያሉበት ወቅት እንደሌለ በተደጋጋሚ በመግለጽ ላይ ናቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የማኅበረሰቡ ደም የመለገስ ባህል ደግሞ እምብዛም እንደሆነ ይነገራል። አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ደም መለገስ ሕይወቱን የሚያሳጣው እስኪመስለው ድረስ ለመለገስ ወደኋላ ሲያፈገፍግ ይስተዋላል። ይህን የማኅበረሰቡን አገም ጠቀም ኹነት ደግሞ ይበልጥ የሚያባብሱ ድርጊቶች ሰሞኑን መፈጠራቸውን የደም ለጋሾች ማኅበር ቅሬታ እያሳየ ነው።

- ይከተሉን -Social Media

ቅሬታ አቅራቢዎቹ የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ወደ ፖለቲካ እያመራ መሆኑን በመግለጽ ላይ ናቸው። አገልግሎቱ የደም ለጋሾች ቁጥር መቀነሱንና በደም ባንክ ያለው መጠን አነስተኛ መሆኑን ለተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ሰሞኑን እየገለጸ ሲሆን፤ በሌላ ጎን ደግሞ የበጎ አድራጎት ማኅበራት ደም ለመለገስ እገዳ ተደርጎብናል ሲሉ ተደምጠዋል።

የሙዚቀኛ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የልደት ቀን ምክንያት በማድረግ ‹ሺሕ ሆነን የሺዎችን ሕይወት እንታደግ› በሚል መሪ ቃል የደም ልገሳ ሊያደርጉ የነበሩ በጎ አድራጊዎች ዝግጅታቸውን ከጨረሱ በኋላ፣ ከበላይ አካል በደረሰ መልዕክት አላስፈላጊ ክልከላ ተደርጎባቸው ልገሳው በመቅረቱ ነው ማኅበሩ ቅሬታ የሚያቀርበው።

የማኅበሩ አካላት እንደገለጹት ከሆነ፤  የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት በደም ለጋሽ ማኅበሩ ላይ የፖለቲከኞችን ፍላጎት አስፈጽሟል በማለት ቅሬታቸውን እየሰነዘሩም ሰንብተዋል። ታዲያ እንዲህ ዓይነት ክልከላዎች እያሉ የደም እጥረት ተከስቷል ማለት ብዙኀኑን ያወዛገበ ኹነት ነው የሆነው።

‹እንኳንስ ዘንቦብሽ እንዳውም ጤዛ ነሽ› እንዲሉ፣ ይህን መነሻ ያደረጉ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች፤ ደም በመለገስ የሰዎችን የመኖር እድል ማስረዘም በራሱ ሰላምን የሚያጎናጽፍ ቅዱስ ተግባር መሆኑን ቢያምኑም፣ ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ በመንግሥት ላይ ያላቸውን እምነትና ተስፋ ያሟሸሸው ይመስላል። ‹የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ተግባር ወደ ፖለቲካ ይዘት ዞሯል› የሚሉ አንዳንዶች፣ ይህ ዓይነቱ ድርጊት ተቋሙ ለቆመለት ዓላማ መገለጫ እንዳልሆነ በመግለጽ፣ ወደ ፖለቲካው ከተገባ እንኳን ሌላ ደም ሊጠየቅ መንግሥት ራሱ በታጣቂዎች የሚፈሰውን የንጹሐን ደም የማስቆም ተቀዳሚ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ነው የሚሉት።

የአገርን ሰላም በማስፈን ፈንታ ደም የሚያፈሱ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ ይገባል እንጂ፣ ደም ሲፈስ ዝም ብሎ እያዩ እንደገና ደም መጠየቅ ምን ይሉት ተግባር ነው የሚለውን መልዕክትም ለደም ባንክ ባይሆን ለመንግሥት ይድረስ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት የደም አቅርቦትን 20 በመቶ ለመጨመር ማቀዱን ከዚህ በፊት መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፤ ይህም ሆኖ እጥረቱ አሁንም ከመከሰቱ እንዳልዘለለ እየተሰማ ነው።

ኅብረተሰቡ ስለ ደም ልገሳ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆን ለደም እጥረት መፈጠር ምክንያት መሆኑ ከዚህ በፊት በጤና ሚኒስቴር በኩል ሲነገር ነበር። ለአብነትም በ2012 ማኅበረሰቡ ስለ ደም ልገሳ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆኑን ተከትሎ የዓለም የጤና ድርጅት ለታዳጊ አገራት ካስቀመጠው ከአንድ በመቶ ያህሉ ሕዝብ ከአንዱ እንኳ ደም ማግኘት እንዳልተቻለ ተቋሙ መግለጹ አይዘነጋም።

አሁን ደግሞ ሕዝቡ ልለግስ እያለ ክልከላ ማድረግ ጉዳዩን ‹እንዳያማ ጥራው እንዳይበላ ግፋው› ይሉት አስመስሎታል እየተባለ ነው። ታዲያ ይህ ‹የማይረባ ውጥን› ድሮም በቋፍ ላይ ያለውን የማኅበረሰቡን የመለገስ ፍላጎት ይብሱን ሊያመናምነው እንደሚችል ከወዲሁ ስጋት የተዋሃደበትን ቅሬታ አሳድሯል።

- ይከተሉን -Social Media

ከአዳጊ አገራት ሕዝብ አንድ በመቶ የሚሆነው ደም መለገስ እንዳለበት የዓለም የጤና ድርጅት የሚገልጽ ሲሆን፤ በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ አንድ ሚሊዮን ሰው መለገስ እንደሚገባው የጤና ሚኒስቴር መረጃ ይጠቁማል። ይሁን እንጂ ከሦስት ዓመት በፊት ያለው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ በኢትዮጵያ ያለው የደም ለጋሾች ቁጥር ዜሮ ነጥብ ሰባት በመቶ መሆኑን ነው።

አሁን አሁን የሚሰሙት የፖለቲካ አሻጥሮችና የደም ለጋሽ ማኅበራት የመለገስ ክልከላ ደግሞ የደም እጥረቱን ከምን ደረጃ ያደርሰው ይሆን? ….የብዙኀኑ ጥያቄ ሆኗል።

ባሳለፍነው ሐምሌ መጀመሪያ ሳምንት ታስቦ የነበረው የቴዎድሮስ ካሳሁንን የልደት ቀን ምክንያት በማድረግ ማኅበሩ ያዘጋጀው ልገሳ መቋረጡ ቅሬታ ማስነሳቱን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት በበኩሉ ክልከላ እንዳላደረገ ለተለያዩ የሚዲያ ተቋማት እየገለጸ ነው።

ከማኅበሩ ውጪ ያሉት ሌሎች አካላት ደግሞ የአንድ ማኅበር ደም ስላልተለገሰ ሌላው ማኅበረሰብ ደም መለገሱን ማቆም የለበትም የሚል የግል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

እጥረት

በኢትዮጵያ በሚገኙ ክልሎች የደም እጥረት እንዳጋጠመ የሚመለከታቸው አካላት እየገለጹ ነው። ባለድርሻ አካላቱ እንደሚሉት ከሆነ፤ ከደም ባንክ የሚገኘው የደም ክምችት ከሚፈለገው መጠን ያነሰ መሆኑን ተከትሎ ከአንድና ከኹለት ሳምንታት በኋላ ደም ልገሳ የሚሻው ሕሙማንን ማስተናገድ አቀበት ሊሆን እንደሚችል በቅድሚያ ስጋት አሳድሯል።

እጥረቱ የተከሰተው በተለያዩ የክልል ከተሞችም ጭምር መሆኑ እየተሰማ ነው። የደም እጥረት የገጠመው የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የክልሎች ከተሞችም  ጭምር ነው። የደም እጥረት ከተጋረጠባቸው ደም ባንኮች መካካል ድሬዳዋ፤ አዳማ፣ በጎንደር እንዲሁም በተለይም በሰሜኑ ጦርነት ቀጠና ውስጥ የነበሩ ስፍራዎች ግንባር ቀደም ናቸው።

የአዳማ ደም ባንክ በበኩሉ፣ በባንኩ ቢያንስ 200 ከረጢት ደም መኖር ሲገባ ያለው ግን ከ70 ከረጢት የማይበልጥ መሆኑን ሰሞኑን ለተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ተናግሯል። የጎንደር ደም ባንክ በበኩሉ የደም እጥረት እንደተከሰተ እና ለማኅበረሰቡ 15 ሺሕ ዩኒት ደም እንደሚያስፈልገው መግለጹ አይዘነጋም።

- ይከተሉን -Social Media

በድሬዳዋ ከተማም እጥረቱ ተከስቷል ነው የተባለው። በሌሎች በጦርነት ቀጠና ውስጥ በነበሩና ባሉ አካባቢዎችም እጥረቱ እንደተባባሰ እየተነገረ ነው።

የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት በበኩሉ በባንኩ ያለው የደም መጠን ለአንድ ሳምንት ቢሆን እንጂ ከዚያ ሊበልጥ እንደማይችል እየገለጸ ይገኛል።

እንደ ተቋሙ ገለጻ ከሆነ፤ የደም ለጋሾች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየቀነሰ መምጣቱን ተከትሎ የደም እጥረት ያጋጠመ ሲሆን፤  የጉዳዩን እንገብጋቢነት በመረዳት ኹሉም ሰው የተለመደ በጎ ፈቃዱን እንዲቸር ጥሪ ሲያቀርብ ተስተውሏል።

የእጥረቱ ምክንያትና መፍትሄው

የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት እና ቀይ መስቀል ተቋም በአገር ዐቀፍ ደረጃ ለተከሰተው የደም እጥረት ዋነኛ ምክንያቶችን በዝርዝር እየገለጹ ነው። ከኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ከሆነ፤ ለእጥረቱ መከሰት ዋና ዋና ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው።

የመጀመሪያው ምክንያት የትምህርት ተቋማት መዘጋት ነው። በኢትዮጵያ የተለያዩ ስፍራዎች በሚገኙ የትምህርት ተቋማት ከተማሪዎችና ከመምህራን በርካታ ደም እንደሚሰበሰብ ይታወቃል። ይሁን እንጂ አሁን ላይ የትምህርት ተቋማት የተዘጉበት ወቅት በመሆኑ እጥረቱ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል።

የክረምቱ ወቅት ለለጋሾች መሰናክል መሆኑ ሌላኛውና ኹለተኛው ለእጥረቱ መከሰት መንስኤ ነው ተብሏል። ያለንበት ወቅት ክረምት መሆኑን ተከትሎ ደም ለመለገስ ይቅርና ከቤት ወደ ሥራ፣ ከሥራ ቦታ ወደ ቤት ለመንቀሳቀስ እንኳ ማኅበረሰቡ እየተቸገረ ይስተዋላል። ታዲያ ይህ ክስተትም ለእጥረቱ ምክንያት መሆኑ ተጠቅሷል።

በጦርነት ቀጠና ውስጥ ያሉ ስፍራዎች ደም ከመለገስ ይልቅ ደማቸው እየፈሰሰ መሆኑ ሌላኛው ሦስተኛው አንገብጋቢ ችግር መሆኑም ተመላክቷል። በኦሮሚያ ክልል ወለጋ የተለያዩ ወረዳዎች፤ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን የተለያዩ ሥፍራዎች፤ በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ ወረዳ ልዩ ልዩ ቀበሌዎች በሱዳን ደንበር በሁመራ በኩል በሚገኙ ስፍራዎች እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች የጸጥታ መደፍረስ ደም ለመለገስ መሰናክል የሆነ ክስተት መሆኑም ተነስቷል።

ሌላኛውና በአራተኛ ደርጃ የተነሳው የእጥረቱ መንስኤ በማኅበረሰቡ በኩል የሚስተዋለው የግንዛቤ እጥረት ነው። በተለይም በገጠራማው አካባቢ ያለው የማኅበረሰብ ክፍል ስለ ደም ልገሳ ያለው አመለካከት ዝቅተኛ መሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል። በመሆኑም ደም ለግሱ ከሚል ትዕዛዝ የሚመስል መልእክት ይልቅ የማኅበረሰቡን ሥነ አዕምሮ ሰርስሮ በሚገባ መልኩ የሥነ ልቦና ትምህርት ማስፋፋት ይገባል ይላሉ የዘርፉ ምሁራን።

ማኅበረሰቡ ደሜን አልሰጥም በሚል የተሳሳተ አመለካከት ስለተሰነካከለ መሠረታዊ የሥነ ልቦና ትምህርት ያስፈልገዋል የሚሉት የሥነልቦና ምሁርሩ ቃልኪዳን ዓለማየሁ ናቸው።

እንደ ቃልኪዳን ገለጻ ከሆነ፤ የሚለግሰውን ሳይሆን የማይለግሰውን ማኅበረሰብ ደም የመለገስ ጥቅም በአእምሮው ውስጥ እንዲሰርጽ ማድረግ ተገቢ ነው። አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ደም ቢለግስ በሕይወቱ ላይ አንዳች ችግር የሚፈጠር እንደሚመስለው ሲናገር ይሰማል። ታዲያ የሕክምና ባለሞያዎችም ቢሆኑ ይህንን የተሳሳተ አመለካከት እንዲቀርፍ ማኅበረሰቡን ማስተማር አለባቸው ነው ያሉት ቃልኪዳን።

የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ቲሹ በበኩሉ እጥረቱን በማስመልከት በተለያዩ ሥፍራዎች ድንኳን በመትከል ደም እያሰባሰበ ይገኛል።


ቅጽ 4 ቁጥር 196 ሐምሌ 30 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች