ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኖቤል የሰላም ሽልማትን አሸነፉ

0
712

100ኛው የኖቤል የሰላም ተሸላሚ ሆነዋል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) 223 ግለሰቦችና 78 ድርጅቶች በአጠቃላይ 301 እጩዎች የተሳተፉበትን የኖቤል የሰላም ሽልማት በትላንትናው ዕለት ዓርብ፣ መስከረም 30/2012 አሸንፈዋል። የኖቤል የሰላም ሽልማትን የሚያሸንፉ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች 900 ሺሕ ዶላር (ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ) የሚሰጣቸው ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመጪው ታኅሣሥ 2012 በኦስሎ ሽልማታቸውን ይወስዳሉ ተብሏል ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከ20 ዓመት በፊት ደም አፋሳሽ የነበረውንና የርካታ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈውን የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት መቋጫ እንዲያገኝ አድርገው ሰላም በማውረዳቸውና ምሥራቅ አፍሪካ የትብብር ቀጠና እንዲሆን ያደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የኖቤል ሽልማቱን እንዲያሸንፉ ጉልህ ሚና ተጫውቷል ተብሏል።
በተለይም ወደ ደም መፋሰስ እየገባች የነበረችው የሱዳን የፖለቲካ ኀይሎች ተደራድረው የሥልጣን ክፍፍል በማድረግ ወደ ሰላም መመለሳቸውም ትልቅ ዋጋ የሚያሰጥ ስኬት ተደርጎም ተወስዶላቸዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ መሸለም በርካታ የአገራት መሪዎችን ፖለቲከኞችንና ምሁራንንም በአንድ ድምፅ ያስማማ መሆኑን አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸውና መልዕክታቸውን ካስተላለፉት የአገራት መሪዎች ለማወቅ ችላለች።

የአገራት መሪዎች
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኖቤል የሰላም ሽልማት ማሸነፍን ተከትሎ ባስተላለፉት መልዕክት “ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የ2019 የኖበል ሰላም ሽልማትን ስላገኙ እንኳን ደስ አለዎት፣ እንኳን ደስ አለሽ እናት አገር ኢትዮጵያ፣ በአገራችን አራቱ ማዕዘን፣ በዓለም ዙርያ የምትኖሩ የዚህች የተባረከች አገር ልጆች ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል።

የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ በበኩላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኖቤል የሰላም ሽልማት ማሸነፋቸውን ተከትሎ ባስተላለፉት የደስታ መልዕክት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማቱ የሚገባቸው መሆኑን ገልጸው፣ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ የሠሩት ሥራ ምሳሌ ሊሆን የሚችል እውነተኛ መሪ ናቸው ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቀጠናው ሰላም እንዲኖር ያደረጉት አስተዋጽዖ ከፍተኛ መሆኑንም አስታውሰዋል።

የግብጹ ፕሬዝዳንት አብደልፈታህ አል ሲሲም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደስታቸውን ገልጸው በመልዕክታቸው በአፍሪካ ግጭት እና ውዝግብን ለማስቆም ለሚደረጉ ጥረቶች ሁሉ ስኬትን ተመኝተውላቸዋል።

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሽልማቱ ይገባቸዋል፣ የቀጠናውን ትስስር ለመፍጠር ከእሳቸው ጋር በመሥራቴ ደስተኛ ነኝ ብለዋል።

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ዛይድ በበኩላቸው በአማርኛ ቋንቋ “ጓደኛዬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኖቤል የሰላም ሽልማትን በማሸነፉ የተሰማኝን ደስታና ጥልቅ ስሜት ለመግለፅ እወዳለሁ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቀጠናው ላመጣው ሰላምና ተስፋ ሽልማቱ ይገባዋል” ሲሉ ደስታቸውን አጋርተዋል።

የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማ፣ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሓፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝን ጨምሮ የተለያዩ አገራት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ መሸለም የተሰማቸውን ደስታ ከገለጹት መካከል ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ 100ኛው የኖቤል ተሸላሚ መሆናቸውን አስመልከቶ ባስተላለፈው መልዕክት፣ “ሰላም እና ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲኖር ለማስቻል ላደረጉት ጥረት እና ከጎረቤት ኤርትራ ጋር የነበረው ግጭት እንዲፈታ ለወሰዱት እርምጃ” የኖቤል ሽልማት ማግኘታቸው ተገቢ እንደሆነ አስታውቋል። ኤምባሲው አያይዞም ይህ የክብር ሽልማት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አመራር በአገሪቱ ውስጥ አመርቂ እመርታ ለመምጣቱ ማሳያ ነው መሆኑን ጠቅሷል።

ስለጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ሽልማት

ታዋቂ ሰዎችና ፖለቲከኞች ምን አሉ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የጠቅላይ ሚኒስትሩ መሸለም በእጅጉ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል። ለረጅም ጊዜ የቆየውን የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት እና አለመግባባት በመፍታት፣ እንዲሁም ሰላምና ዴሞክራሲ የሚመጣው በፍቅር፣ ሰዎችን በማክበር፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመፍጠር እንጂ በማሰር፣ በመግረፍ በማንገላታት እና በጉልበት ሰላም እንደማይገኝ አምነው የጀመሩት የለውጥ ሒደት ነው ሲሉ ሽልማቱ ለእሳቸው ተገቢ መሆኑን ያወሳሉ። ሽልማቱ መሰጠቱ ለውጡን በጀመሩበት መንፈስ እንዲቀጥሉ ያበረታታቸዋል ብዬ አስባለሁ ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማቱን ያገኛሉ የሚል እምነት እንደነበራቸው ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥን ሕይወት መምህርና የመድረክ ምክትል ሊቀ መንበር በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር) ለኹለት ዐሥርት ዓመታት ደም አፋሳሽ የነበረውንና በርካታ ሰዎች ያለቁበትን የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት መቋጫ እንዲያገኝ ማድረጋቸውና ሰላሟ የደፈረሰን አገር በድፍረት ተረክቦ ሰላም ለማምጣት መጣራቸው ስኬታማ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) ሊቀመንበር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በቀጠናው ሰላም ለመፍጠር ደፋ ቀና እያሉ ላሳዩት ጥረትና ስኬት ትክክለኛ ክፍያ ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል። ኢትዮጵያም እንደ አገር፣ ሕዝቦቿም እንደ ሕዝብ በስኬቱ ድል ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል የሰላም ሽልማት ማግኘት ለኢትዮጵያ ትልቅ እሴትና ዕውቅና መሆኑን የገለጹት እሌኒ ገብረ መድህን (ዶ/ር)፣ የእሳቸው ለዚህ ስኬት መብቃት ለኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ የድል ደወል መሆኑንና ሌሎችም ትልቅ ትምህርት ነው ብለዋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀ መንበር ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጠናው ባሉ አገራት እና በኢትዮ ኤርትራ ዙሪያ ለፈጸሙት ገድል፣ ለድካማቸው የሚመጥን ሽልማት አግኝተዋል፤ በትክክልም ሽልማቱ ይመጥናቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።

የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ሊቀ መንበር አብዱልቃድር አደም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ20 ዓመት በኋላ የኢትዮ ኤርትራ ደም አፋሳሽ ታሪክ መቋጫ እንዲያገኝ አድርገው ሰላም በማውረዳቸውና ምሥራቅ አፍሪካ የትብብር ቀጠና እንዲሆን ያደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በዓለም ዐቀፍ ማኅበረሰቡ እውቅና እንዲቸረውና ለኖቤል ሽልማት እንዳበቃቸው ያምናሉ።

የሽልማቱ ቀጣይ ተጽዕኖ
ሽልማቱ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአገሪቱ ፖለቲካ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው የሚገልፁት ብርሃኑ ነጋ፣ ምንም እንኳን ፖለቲካችን ትልቅ ግፊት ያለበት ቢሆንም፣ ቅን ልቦና ያላቸው ፖለቲከኞች እንዲበረታቱ ያደርጋቸዋል ብዬ አምናለሁ ሲሉ አክለዋል። ኢትዮጵያ ይኼንን ክብር ስታገኝ የመጀመሪያዋ እንደ መሆኑ ለአገርም ክብር ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ የመሪዎች ጥንካሬ የሚለካው ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ በሆነ ሁኔታ ምን አደረጉ በሚለው ሳይሆን፣ እነዛን ችግሮች ለማለፍ መቻላቸው የአመራር ጥንካሬ ምልክት ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ አስቸጋሪ ሁኔታዎች መኖራቸውን ያነሱት ብርሃኑ፣ እነዚህን አስቸጋሪ ነገሮች በጥበብ ለማለፍ በመሞከራቸውና ይኼንንም ዓለም ዓቀፉ ተቋም ዕውቅና መስጠቱ እኛ በምንፈልገው መልኩ አልሠሩም በማለት ከተወሰነ የማኅበረሰብ ጥቅም አንጻር ብቻ የሚያዩ ኃይሎች አገርን አንድ ማድረግ፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ማምጣት ትልቅ ጥበብ መሆኑን እንዲረዱ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል። የዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ለዚህ ዕውቅና ከሰጠው ምናልባት እየሠሩት ያለው ነገር ያለውን አስቸጋሪ መሆኑን በመረዳት አገር ውስጥም ያሉት ፖለቲከኞች ከዚህ ትንሽ ተምረው፣ ተረድተው ለውጡ ወደ ታለመለት ቦታ እንዲደርስ ይረዳሉ ብለው ተስፋ ያደርጋሉ። አገሪቱን ለማረጋጋትም የፖለቲካውን አቅጣጫ ወደ ታለመለት ቦታ ለመውሰድም ይጠቅማል ብለው ያስባሉ፤ ብርሃኑ።

ደሳለኝ ጫኔ በፕሮፌሰሩ ሐሳብ አይስማሙም። በቀጠናው ሰላም በማምጣት በተሸለሙበት ነገር ቢስማሙም በአገር ውስጥ ግን ውጤታማ አለመሆናቸውን ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የሰላም እጦት መኖሩን የሚያወሱት ደሳለኝ፣ ምናልባትም ይኼ ሽልማት ጠቅላይ ሚኒስትሩን በአገሪቱ ላይ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ብርታት እንደሚሆናቸው አመላክተዋል።

በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገር ቤት በርካታ ችግሮችን አስቀምጠው የጎረቤት አገራትን ችግር እልባት ለመስጠት ሲሯሯጡ እንደነበር ባይካድም፣ ለዛ ተግባራቸው የተበረከተላቸው ገጸ በረከት ግን ምናልባትም ለአገራቸው ሰላም እንዲሠሩ ሊያነሳሳቸው እንደሚችል ተስፋ አለኝ ሲሉ ገልጸዋል።

አረጋዊ በርሄ ግን በዳሰለኝም በበየነም ሐሳብ አይስማሙም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአገሪቱ ሰላም መሥራት ያለባቸውን ያህል እየሠሩ ነው፤ በዛም በነጻነት ሐሳብን የመግለጽ መብት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት የመንቀሳቀስና ሌሎችንም መብቶች እንዲከበሩ አድርገዋል። ሽልማቱ ጥረታቸውን እንዲያጠናክሩ ብርታት ይሆናቸዋል በሚለው ሐሳብ እስማማለሁ፤ ሽልማቱ ይበልጥ ለፖለቲከኞቹ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑንም አውስተዋል።

ስለኖቤል ሰላም ሽልማት
ኖቤል የሚለው ሥያሜ የተወሰደው ከሲውዲናዊ ነጋዴ እና የድማሚት ፈጣሪ አልፍሬድ ኖቤል መሆኑን የታሪክ መዛግብት ያወሳሉ። ለመጀመሪያ ጊዜ ሽልማቱ መሰጠት የጀመረው በ1901 (እ.ኤ.አ.) ግለሰቡ በለገሰው ገንዘብ እንደሆነም ይነገራል።

በተለያዩ መስኮች አኩሪ ተግባራትን ያከናወኑ ግለሰቦችንና ተቋማትን በየዓመቱ የሚሸለሙበት የኖቤል ሽልማት በዓለማችን ከሚሰጡ ዕውቅናዎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳል። አልፍሬድ ኖቤል ኅዳር 18/1888 ባስቀመጠው ኑዛዜ ያለውን አብዛኛውን ሀብቱን የኖቤል ሽልማት ተብለው ለሚሰጡ ሽልማቶች እንዲውል ተናዟል። በዚህም ኑዛዜው “በመንግሥታት መካከል ወንድማማችነት እንዲሰፍን አብዝተው ወይም የተሻለ ሥራን ላከናወኑ፣ የጦር ሠራዊቶች ቅነሳና ለሠላም መስፋፋት አስተዋጽዖ ላበረከቱ ይሰጥ” ሲል አሳስቧል።

እንደተቋሙ ገለጻ ከሆነ 67 የሚሆኑ የኖቤል የሠላም ሽልማቶች በተናጠል ላሸነፉ ግለሰቦች ተሰጥተዋል። 30ዎቹን ደግሞ ኹለት ግለሰቦች በጋራ የተሸለሟቸው ናቸው። ኹለት የሠላም ሽልማቶችን ሦስት ሦስት ሰዎች በቡድን አሸንፈዋል።

ለሦስት ሰዎች የተሰጡት ሽልማቶች በአውሮፓዊያኑ 1994 እና በ2011 ሲሆን የመጀመሪያውን የፍልስጥኤሙ መሪ ያሲር አራፋት እንዲሁም እስራኤላዊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሺሞን ፔሬዝና ይዛክ ራቢን በጋራ ወስደዋል።

ኹለተኛውን ደግሞ አፍሪካዊቷ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ኤለን ሰርሊፍ ጆንሰን፣ ላይቤሪያዊቷ የመብቶች ተሟጋች ሌይማህ ቦዊና የመናዊቷ ጋዜጠኛና የመብት ተከራካሪ ታዋኮል ካርማን ሽልማቱን ተጋርተውታል።

ሽልማቱ ከአንድ በላይ ለሆነ አሸናፊ የሚሰጥ ከሆነ የገንዘቡም መጠን ለአሸናፊዎቹ ይከፋፈላል። ሸላሚው ድርጅት ለአንድ ሽልማት ከሦስት በላይ አሸናፊዎች እንዳይኖሩ ይገድባል።

የኖቤል የሠላም ሽልማት ለ133 ግለሰቦችና ተቋማት ተሰጥቷል። ከእነዚህ ውስጥም 106 ግለሰቦች ሲሆኑ 27ቱ ድርጅቶች ናቸው። ከተቋማቱ ውስጥ ዓለም ዐቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ሦስት ጊዜ ሽልማቱን የወሰደ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ደግሞ የኖቤል ሠላም ሽልማትን ሁለት ጊዜ ለማግኘት ችሏል።

ዘንድሮ ለዘርፉ ከቀረቡ እጩዎች መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና የ16 ዓመቷ ስዊድናዊት የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋች ግሪታ ተንበርግ በሰፊው ያሸንፋሉ የሚል ግምት ተሰጥቷቸው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአንድ ቀን 350 ሚሊዮን ችግኝ ማስተከላቸውና በእርሳቸው አመራር የካቢኔያቸውን ግማሹ በሴቶች እንዲያዝ ማድረጋቸውም ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ እንዲቸራቸው ያደረገ መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ሲናገሩ ይደመጣል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት 1938 (እ.ኤ.አ.) ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ለኖቤል ሽልማት ታጭተው ነበር።

የኖቤል ሽልማት በፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ሕክምና፣ ሥነ ጽሑፍና ሰላም ዘርፎች በየዓመቱ ይሰጣል። ሽልማቱ የሚሰጠው ባለፉት 12 ወራት “ለሰው ልጅ የበለጠ አበርክቶ” የሚያደርጉ ነገሮችን ላከናወኑ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሰላም ሽልማቱን አግኝተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here