ማክሰኞ ነሐሴ 10 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአዲሱ ረቂቅ የትምህርት እና ጥናት ፖሊሲ ከቅድመ አንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል የሚሰጥ ትምህርት ነፃ እና አስገዳጅ እንደሚሆን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ግኝት መሰረት ዜጎች ከቅድመ አንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል በግዴታ እንዲማሩ ለማስቻልና የትምህርት አሰጣጥ ሂደቱን የተሳለጠ ለማድረግ አጠቃላይ የትምህርት ረቂቅ አዋጅ ተግባራዊ እንደሚደረግ፤ በሚኒስቴሩ የሥርዓተ ትምህርት ማበልፀጊያ ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ቴዎድሮስ ሸዋረገድ ለኢቢሲ ገልጸዋል።
ፍኖተ ካርታውን ለማዘጋጀት ሲሞከር የትምህርት ዘርፉ ያለበትን ሁኔታ ሊያሳይ የሚያስችል ጥናት መደረጉን የተናገሩት ኃላፊው፤ መንግስት ለትምህርት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና ጥራት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በአዲስ መልክ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መግባቱን ገልፀዋል።
በጥናቱ ሂደት ላይ ከዚህ በፊት ከነበረው አሰራር በተለየ ከውጭ በመጡ ባለሙያዎች ጥናቱን ከማሰራት ይልቅ፤ በአገር ውስጥ ባሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ጥናቱ እንዲከናወን መደረጉን ተናግረዋል።
በስድስት ዘርፎች ተከፋፍሎ በተካሄደው በዚህ ሰፊ ጥናት፤ በመሰረታዊነት ቅድመ መደበኛና የአንደኛ ደረጃ፣ ኹለተኛ ደረጃ፣ የመምህራን ሥልጠና፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት፣ የከፍተኛ ትምህርት እንዲሁም የፖሊሲ ጉዳዮችን የሚያካትተው የትምህርት ሥርዓት በተለያየ ቡድን እንዲጠና መደረጉን ኃላፊው ገልፀዋል።
በጥናቱ መሰረት በነባሩ የትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ የጥራት ችግር፣ የሰው ሀብት ስብዕና ግንባታ ጉድለቶች፣ ከገበያው ፍላጎት ጋር አለመጣጣም፣ የመምህራን ብቃት ማነስ፣ በቴክኖሎጂ አለመደገፍ እና ፍትሃዊ የትምህርት ተደራሽነት የዘርፉ ቁልፍ ችግሮች ሆነው መለየታቸውን አስረድተዋል።
በአዲሱ የትምህርት ፍኖታ ካርታ አንድ አካል በሆነው ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ የተዘጋጀውን የአሰራር ማዕቀፍ መሰረት በማድረግ፤ ከ2014 ጀምሮ በትምህርት ሚኒስቴርና በክልል የትምህርት ቢሮዎች ትብብር የመማሪያ ማስተማሪያ መፀሃፍት በማዘጋጀት ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል የሙከራ ትግበራ መካሄዱንም ኃላፊው ተናግረዋል።
በዚህ መነሻነት የሙከራ ተግባሩን መሰረት በማድረግ በ2015 ወደ ሙሉ ትግበራ ለመሻገር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ዶ/ር ቴዎድሮስ ጠቁመዋል።



