በ2015 በጀት ዓመት ከ450 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱ ተገለጸ

0
1063

ማክሰኞ ነሐሴ 10 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የገቢዎች ሚኒስቴር በ2015 በጀት ዓመት ከ450 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ እቅድ መያዙን የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው ገለጹ፡፡

በ2015 በጀት ዓመት ለመሰብሰብ በእቅድ የተያዘው ገቢ 266 ነጥብ 95 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ ታክስ እንዲሁም 183 ነጥብ 34 ቢሊዮን ብር ከወጪ ንግድ፣ ቀረጥና ታክስ ለመሰብሰብ መታቀዱን ያሳወቁት ሚኒስትሩ፤ እቅዱ ከባለፈው በጀት ዓመት አንጻር ሲታይ የ70 ነጥብ 4 ቢሊዮን ወይም የ36 ነጥብ 3 በመቶ እድገት እንዳለው ተናግረዋል፡፡

እቅዱን ለማሳካት የግንዛቤ ሥራዎችን ማጠናከር፣ በተጨማሪ እሴታ ታክስ ላይ የሚደረጉ ኦፕሬሽኖችን ቁጥር መጨመር፣ ያላሳወቁ ግብር ከፋዮች ላይ የሚደረጉ ክትትሎችን ማጠናከር፣ ዕዳ ክትትል የሚደረግባቸውን ግብር ከፋዮች ቁጥር መጨመር፣ የኦዲት ሽፋንና ጥራትን ማሻሻል፣ ደረሰኝ ላይ የሚደረጉ ክትትሎችን ማጠናከር እንዲሁም በፈቃደኝነት ታክሳቸውን አሳውቀው የሚከፍሉ ግብር ከፋዮችን ቁጥር ማሳደግ ዕቅዱን ለማሳካት የሚሰሩ መሆናቸውን ተናግረው ኦዲት፣ ታክስ ማሳወቅ፣ ቅሬታ አፈታት፣ ዕዳ ክትትል እና ሌሎች በተቋሙ በተለዩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

ተቋሙ የ2014 በጀት ዓመት አፈጻጸምን እንደመነሻ በመውሰድ እና መሻሻል የሚገባቸውን ተግባራት ከማሻሻል አንስቶ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን እንዲደረጉ እስከማድረግ ጥረት እንደሚደርግ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ግብር ከፋዮች፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመራሮች እና ሰራተኞች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ለእቅዱ ተግባራዊነት እንደሁልጊዜው ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ሚኒስቴሩ የ2014 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸሙን እንዲሁም የ2015 በጀት ዓመት እቅዱን በተመለከተ በቢሾፍቱ (ደብረዘይት) ከተማ እያካሄደ ያለው መድረክ ዛሬ እንደሚጠናቀቅ ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

የገቢዎች ሚኒስትሩ ላቀ አያሌው በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ2014 በጀት ዓመት ሊሰበስብ ካቀደው 360 ቢሊዮን ብር ውስጥ 336 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 93 ነጥብ 53 በመቶ ማሳካት መቻሉን መግለጻቸው ይታወሳል። ገቢውም ከ2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የ20 ነጥብ 7 በመቶ ወይም የ57 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here