166 ድርጅቶች በታክስ ስወራና ሕገ-ወጥ ደረሰኞችን ሲጠቀሙ ተያዙ

0
584

በገቢዎች ሚኒስቴር ክትትል ሲደረግባቸው የቆዩ ታክስን ለመሰወርና ሕገ-ወጥ ተመላሽ ለመጠየቅ ሲሞክሩ የተያዙና ሀሰተኛ ማንነት ያላቸው 166 ድርጅቶች ይፋ ተደረጉ።

በገቢዎች ሚኒስትሯ አዳነች አቤቤ እና በሕግ ተገዢነት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ በሆኑት ዘመዴ ተፈራ በተሰጠው መግለጫ በነፍስ ወከፍ ከ51 ሚሊዮን ብር በላይ ግብይት የነበራቸው ነገር ግን ባዶ፣ ኪሳራና ተመላሽ ከሚጠይቁ ደርጅቶች መካከል 16 ድርጅቶች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸዉ እንደሆነ ተገልጿል።
ከ166 ድርጅቶች መካከል 136 ያህሉ ከ 6 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር ማድርጋቸውን በመረጃ ቋት ውስጥ መገኘቱን ተናግሯል። ድርጅቶቹም ምንም ዓይነት የሚሸጡት ዕቃም ሆነ የሚሰጡት አገልግሎት የሌላቸው ሲሆን በሀሰተኛ መታውቂያ፣ በሀሰተኛ አድራሻ ፈቃድ ሳይኖራቸው ደረሰኝ ያሳትሙ የነበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሚኒስትሯ አክለዉም እነዚህ ሕገወጥ ድርጅቶች በዋናነት ሀሰተኛ ደረሰኝን የሚያቀርቡ በመሆኑ ግብር ከፋዩ ማንነታቸዉን አውቆ ምንም አይነት ደረሰኝ ከነሱ እንዳይቀበልና ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም እንዲያቀርብ አሳስበዋል።

የተወሰኑ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ያለደረሰኝ ሲሠሩ ተገኝተዉ ማስተካከያ እንዲያደርጉ የተደረገ ሲሆን ከእነዚህም ዉስጥ ኢት ፍሩት እና የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ድርጅት መሆናቸዉን ገቢዎች ሚኒስቴር አስታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 50 ጥቅምት 8 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here