ሕብረት ኢንሹራንስ በዛፉ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ስም ቅርንጫፍ ሰየመ

0
735

ሕብረት ኢንሹራንስ አክሲዮን ማህበር በዋናው መሥሪያ ቤት ውስጥ የሚገኘውን ዐብይ ቅርንጫፍ በኢንሹራንሱ መሥራች እና የአክሲዮን ባለድርሻ ዛፉ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ስም ለመቀየር መወሰኑን ገለፀ። በኢንሹራንሱ ዋና መሥሪያ ቤት ወስጥ የሚገኘውን እና ዐቢይ ቅርንጫፍ ተብሎ የሚጠራውን ለኢንሹራንሱ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ባበረከቱት የኢንሹራንሱ መሥራች እና የቀድሞ የቦርድ ሊቀመንበር ስም በቀጣዩ ወር መጀመሪያ እንደሚለወጥ ተገልጿል።

የስም ለውጡ ከተወዳዳሪነት አንፃር የሚያበረክተው ጥቅም በኢንሹራንሱ የቦርድ አመራር በማፅደቅ በዛፉ ስም እንዲሆን መወሰኑን የኢንሹራንሱ የሽያጭ ክፍል ኃላፊ መስፍን ኢያሱ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። አክለውም በአዲሱ ስያሜ መሰረት ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ዐቢይ ቅርንጫፍ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ሰነዶችን እና መረጃዎችን በአዲሱ ስያሜ የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በቀጣይም ለባንኩ እንዲሁም ለኢንሹራንሱ እና ለሀገር እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ባበረከቱ ሰዎች የቀድሞ አመራሮች፣ የረዥም ጊዜ ደንበኞች እና የአክሲዮን ባለድርሻዎች ስም ቅርንጫፎችን የመክፈት ሃሳብ እንዳለው እና ኢንሹራንሱ የገበያ ዘዴ አድርጎ እንደሚጠቀምበት ተገልጿል። በአሁኑ ወቅት ኢንሹራንሱ በመላ ሀገሪቱ 50 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 38ቱ መደበኛ ቅርንጫፎች ሲሆኑ 12 ደግሞ በሳተላይት ቅርንጫፍነት አገልግሎት ይሰጣሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 50 ጥቅምት 8 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here