ዓለም አቀፍ የፎቶ ፌስቲቫል ከኅዳር 27 እስከ ታኅሣሥ 1 ድረስ በሸራተን አዲስ ሆቴል እንደሚካሔድ የአዲስ ፎቶ ፌስት አዘጋጆች ገለጹ።
ለስድስት ቀናት የሚቆየው ፌስቲቫሉ በአፍሪካ ትልቁ ነው ያሉት የፌስቲቫሉ መሥራችና እ.አ.አ. 2007 ዓለም ዐቀፍ የፎቶ አዋርድ ተሸላሚ አይዳ ሙሉነህ ለፎቶ አንሺዎች ከፍተኛ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከሚገኙ 61 አገራት የተውጣጡ 152 የፎቶ ግራፍ ጠበብት በፌስቲቫሉ ተሳትፈዋል።
ከመካከላቸው ከፊሎቹ ኢትዮጵያዊያን የፎቶ ግራፍ ባለሙያ ወጣቶች ናቸው። ጀማሪና ልምድ ያላቸው የኢትዮጵያና የአፍሪካ ፎቶ አንሺዎች ከሌላው ዓለም ጋር ማገናኘት የፌስቲቫሉ ዋና ዓላማ ሲሆን ጎን ለጎን ዐውደ ጥናቶች፣ ኮንፍረንስ፣ የልምድ ልውውጥ ይቀርቡበታል ተብሏል።
አዲስ ፎቶ ፌስት የተመሠረተው በ2003 በአይዳ አሸናፊ ነው። በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የፎቶግራፍ ፌስቲቫሎች ውስጥ አንዱ ሲሆን በዓይነቱና በይዘቱም ከቀዳሚዎቹ የአፍሪካና ዓለም አቀፍ ፌስቲቫሎች አንዱ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።