የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የስኳር ፋብሪካዎች ከሸንኮራ አገዳ ምርት ጎን ለጎን በሳይንሳዊ መንገድ የስንዴ ምርት ማልማታቸው ተነገረ።
በወንጂ ሸዋ የስኳር ፋብሪካ ከሸንኮራ አገዳ ምርት ጎን ለጎን በሳይንሳዊ መንገድ ስንዴ፣ ቦሎቄ፣ ማሾና ሌሎች ምርቶች መመረታቸውን በየኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወዮ ሮባ ተናግረዋል።
ማንኛውም ውኃ ገብ መሬት ጾም እንዳያድር በሚል በተለያዩ የስኳር ኢንዱስትሪዎች የተለያዩ ምርቶችን እያለማ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ከ500 ሄክታር በላይ የሚሆን መሬት ላይ የስንዴ፣ ማሾና ቦሎቄ ምርቶች መልማታቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይ የአገርን የምርት እጥረትን በመቅረፍ እጥፍ የሆነ ትርፍ ለማግኘት መታቀዱን በምርቱ ጉብኝት ወቅት የተነገረ ሲሆን፣ የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጀማል አማን በበኩላቸው፣ ድርጅቱ የሸንኮራ አገዳ በማምረት ከፍተኛ ልምድ አለው ብለዋል።
350 ሄክታር መሬት ላይ የስንዴ ምርት በማልማት 10 ሺሕ ኩንታል በመሰብሰብ 40 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ታስቧል የተባለ ሲሆን፣ በዚህም የተጣራ ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በተመሳሳይ 128 ሄክታር መሬት ላይ ቦሎቄ በመዝራት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ይገኛል ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ በ30 ሄክታር ላይ የማሾ ምርትን በማልማት ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ እንደሚገኝ አሳውቀዋል።
አለ ስለሚባለው ስለሸንኮራ አገዳ እጥረትም ሆነ ምን ያህል መሬት ላይ አገዳው እየለማ እንደሆነ ግን አልተጠቀሰም።
ቅጽ 4 ቁጥር 203 መስከረም 14 2015


