ሬድፎክስ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የግል ዳታ ሴንተር ወደ ሥራ ገባ

0
625

ሬድፎክስ ሶሉሽንስ ያስገነባው በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል ዳታ ሴንተር ባሳለፍነው መስከረም 9/2015 በሀያት ሬጀንሲ ሆቴል በይፋ ሥራውን ጀምሯል።

ሬድፎክስ ሞጁላር ዳታ ሴንተር 1 ተብሎ የሚጠራው የዳታ ማእከል የአገሪቷ መዲና በሆነችው በአዲስ አበባ በሚገኘው አይሲቲ ፓርክ ውስጥ ነው ተገብቶ ሥራውን የጀመረው።

የሬድፎክስ ሶሉሽንስ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አዳነ ካሳዬ ባደረጉት ንግግር፤ ግባችን በክፍለ አኅጉሩ ቀዳሚ የዳታ ማእከል መሆን ነው ብለዋል። ሬድ ፎክስ ዳታ ሴንተሮቹን ደረጃ በደረጃ ነው የሚገነባው ያሉት አዳነ፣ ሥራ የጀመረው የመጀመሪያው ሞጁላር ዳታ ማእከል እና ቀጣዩ ሰርቨር ማኖሪያዎች በአይሲቲ ፓርክ የሚገኙ መሆኑንም አስታውቀዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ከአደጋ ጊዜ ማገገሚያ ጣቢያዎች (ዲዛስተር ሪከቨሪ ሳይትስ) እና ቀጣዮቹ ሦስት ሞጁላር ዳታ ማእከሎች የሚገነቡበትን ቦታ በተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ይፋ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ሬድፎክስ ሶሉሽንስ አራት ዋና ዋና አገልግሎቶችን (Edge Preserve Cloud, Modular Data Center, and Build to Suite) ያቀርባል ተብሏል። በፍላጎት ላይ የተመሠረተ የመሠረተ ልማት አገልግሎቶችንም ከሳይት ውጪ እንደሚያቀርብና ደኅንነታቸው የተረጋገጠ የዳታ ማእከላት ዲዛይኖችን እንደሚሠራም አስታውቋል።

ፋየርፎክስ ሶሉሽንስ ሥራ መጀመሩን ይፋ ባደረገበት እለት ለጋዜጠኞች በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ይህ አዲስ እና የመጀመሪያው የግል የዳታ ማእከል ተገንብቶ በይፋ ሥራ መጀመሩ ባለሀብቶች በዘርፉ ላይ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚጋብዝ እና ዘርፈ ብዙ የቴክኖሎጂ እድገቶችም እንዲኖሩ የሚያደርግ ነው ብሏል።

ሬድፎክስ በቴሌኮም እና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የበርካታ ዓመታት ልምድ እና ከፍተኛ እውቀት ባላቸው እንዲሁም በተለያዩ የቢዝነስ ተቋማት በርካታ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ሥራዎችንና ፕሮጀክቶችን በመሩ ዐስር ትውልደ ኢትዮጵያዊ ባለሙያዎች የተቋቋመ ተቋም ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 203 መስከረም 14 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here