ከ70 ሰዎች በላይ የቀጠፈው ግርግር

0
909

ሥልጣን ላይ የሚገኘው እና ራሱን “የለውጥ ኀይል” ብሎ የሚጠራው በዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው መንግሥት በትረ ሥልጣኑን ከጨበጠ አመት ከመንፈቅ አለፈው። በ2010 እና ከዛ በፊት ባሉት ጥቂት ዓመታት ከጫፍ ጫፍ የለውጥ ያለህ በማለት ብሶቱን በየአደባባዩ ሲገልጽ የነበረው ህዝብ፤ በፍትሕ፣ መልካም አስተዳደርና የስራ ዕድል ዕጦት የተማረረው ወጣት በመላ አገሪቱ ከዳር ዳር በመነሳት ብሶቱን በመግለፅ በጊዜው ከፌደራል እስከ ወረዳ የተቀመጠውን አመራር እረፍት በመንሳቱ ኢትዮጵያ አሁን ለምትገኝበት ለውጥ ምክንያት እንደሆነው ብዙዎች ይስማማሉ።

በአገሪቱ ፖለቲካ እምብዛም የማይታወቁትን ዐቢይ አሕመድን ወደሚኒሊክ ቤተመንግስት ያመጣው ለውጥ በብዙ አፍ የሚያስከፍቱ ክስተቶች ታጅቦ ለሶስት ወራት ያህል ከቆየ በኋላ የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም በቅጡ አጣጥማ ሳትጨርስ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ግጭቶችና የዜጎች መፈናቀል መከሰት ጀመረ፤ ተባብሶም ቀጠሉ፡፡
የሰላም መደፍረሱ ዋነኛ ምክንያት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ዳተኝነት የሚስተዋልበት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር አሁንም የተረጋጋ እና ሰላም የሞላባትን ኢትዮጵያን እውን ማድረግ እንዳልቻለ ከሰሞኑ የተፈጠሩትና በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች እና የተወሰኑ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የሰላም አየር እንዳይተነፍሱ የተገደዱበትን ምክንያት ማንሳት ይቻላል።

ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እየኖሩ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚፈጽማቸውን በደሎች ነቅሰው በማውጣት የማይናቅ ሚና ሲጫወቱ የነበሩ እና በፖለቲካውም ጎራ ተሰልፈው ገዢውን መንግሥት በዓለም መድረክ ሲሞግቱ የነበሩ አካላት ለውጡን ተከትሎ አገር ቤት ከትመዋል።

መንግሥትም ወደ አገር ቤት ለሚገቡ ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮችና አክቲቪስቶች የግል ጥበቃ በመመደብ በሚሔዱበትና በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ከለላ እንዲያገኙ ሲያደርግ ቆይቷል። የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦኤምኤን) የቴሌቪዥን ጣቢያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጃዋር መሐመድ የጥበቃ አገልግሎት ከሚደረግላቸው ግለሰቦች አንዱ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ጥቅምት 12 ዕኩለ ሌሊት ላይ አካባቢ የፌደራል ፖሊስ ጥበቃዎቹን በድንገት ጃዋር ሳያውቁ ለማንሳት ሙከራ ባደረገበት ወቅት ሁኔታውን አንዱ ጥበቃ ከእንቅልፍ ቀስቅሰው እንዳሳወቋቸው ሁኔታውን በተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ይፋ አደረጉ፡፡ የጠባቂዎቻቸውን መነሳት ተከትሎ ለሚመጣ ማንኛውም አይነት አደጋ ጠባቂዎቹን ያስነሳው አካል ኀላፊነቱን ይወስዳል የሚል መልዕክት ጃዋር በማስተላለፋቸው በርካታ ደጋፊዎቻቸው በመኖሪያ ቤታቸው ተሰብስበው ነበር።

ጃዋር ለእንግሊዘኛ ተናጋሪዎች በሚል ስለሁኔታው በፌስ ቡክ የገለፁት ቃል በቃል ሲተረጎም፤ “እኩለ ሌሊት ላይ ኹለት መኪኖች በመኖሪያ ቤቴ አቅራቢያ በመምጣት ጠባቂዎቼን እቃቸውን ሸክፈው ጊቢውን ለቀው እንዲወጡ እና ለእኔ እንዳያሳውቁ ነገሯቸው።” ሲል ይፋ አደረጉ። ከዚህ በኋላ ነበር በመቶዎች የሚቆጠሩ ቄሮ፣ ቀሬ እና ፎሌዎች የጃዋርን ቤት በመክበብ ለደኅንነታቸው ጥበቃ ለማድረግ የተሰበሰቡት፡፡ ጉዳዩን በማሕበራዊ የትስስት ገፆች የሰሙ ደጋፊዎቻቸው በቁጣ ገንፍለው በመውጣት በወለቴ፣ አየር ጤና፣ ማካኒሳ፣ ጀሞ፣ በኦሮሚያ ደግሞ ዓለም ገና እንዲሁም ሰበታ አካባቢ የሚገኙ ወጣቶች መንገዶችን ዘጉ። የወጣቶቹ ቁጣ እንደሰደድ እሳት በጥቂት ሰዓታት ውስጥ በመስፋፋት የመንገድ መዝጋትና የተቃውሞ ሰልፎች በቢሾፍቱ፣ አዳማ፣ አምቦ፣ አርሲ ነገሌ፣ ሻሸመኔ፣ ዶዶላ፣ ሐረርና ሐማሬሳ ከተሞች ለበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ምክንያት የሆነ ግጭት ተፈጠረ።

አዲስ አበባ
ረቡዕ ማለዳ፣ ጥቅምት 12/2012 የአዲስ አበባ የተወሰኑ አካባቢዎች ንጋታቸው መልካም አልነበረም። ምክንያቱ ደግሞ ጃዋር መሐመድ በማሕበራዊ የትስስር ገፃቸው መንግስት የመደቡላቸው ጠባቂዎች የማንሳት ሙከራን አስመልክቶ የለቀቁት መረጃ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ በርካታ ወጣቶች ከጀሞ ቁጥር ኹለት እስከ መሐል አዲስ አበባ ድረስ ያለውን መንገድ ዝግ እንዲሆን አድርጉ፡፡ በዚህ ሳያበቃ መካኒሳ ሚካኤል አካባቢም መንገዱ በጸጥታ ኀይሎች በመዘጋቱ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ተስተጓጉለው፣ ንግዶች ተቀዛቅዘው፣ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ለመሔድም ያልደፈሩበት ቀን እንደነበር አዲስ ማለዳ ከአካባቢው ነዋሪዎች ሰምታለች።

በሌሎችም የአዲስ አበባ አካባቢዎች ግጭቶች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ በኮየፈጨ እና በቂሊንጦ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢም ተደጋጋሚ የጥይት ድምፆች የተሰሙ ሲሆን ያለ ዕረፍት የሚመላለሱ አምቡላንሶችም ተስተውለዋል። የዓይን እማኞች ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት በግርግሩ ወደ ዐሥር የሚጠጉ ሰዎች የመፈንከት አደጋ ገጥሟቸዋል፤ አራት መኪኖች ላይም ጉዳት ደርሷል። እንደ አዲስ ማለዳ ምንጮች ገለፃ ከተሸከርካሪዎች ባለፈም በአካባቢው በሚገኝ አንድ ካፌ እና ግሮሰሪ ላይ ጉዳት ደርሷል።

ቢሾፍቱ
ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው ቢሾፍቱ ሰላሟ በከፊል ተመለሰ እንጂ አሁንም ድረስ ከድንጋጤ አልወጣችም። ከዓይን እማኞች አዲስ ማለዳ እንደሰማችው ከሆነ በግጭቱ አራት ሰዎች ህይዎታቸውን አጥተዋል። ከዚህም የተነሳ በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች አድማ በመምታታቸው ምክንያት የከተማዋ ነዋሪ ዕንቅስቃሴ ተገድቦ ነበር።

አዳማ
በአዳማ በነበረው ግጭት በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ የከፋ ጉዳት ደርሷል። በዚህም ምክንያት 16 ሰዎች መሞታቸውን የአማርኛው በበሲ የአዳማ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና ስፔሺያሊስት የሆኑትን ዶ/ር ደሳለኝ ፍቃዱን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡ በአጠቃላይ በግጭቱ ከቀላል እስከ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው በሆስፒታሉ ህክምና እየተደረገላቸው የሚገኙ ታካሚዎች ቁጥር ከመቶ በላይ እንደሆነ የዜና አውታሩ ዘግቧል፡፡ ከሰው ህይወት በዘለለ 15 የምስራቅ አፍሪካ ዱቄት ፋብሪካ መኪኖች ተቃጥለዋል፡፡ በከተማው ፍራንኮ በሚባል አካባቢ ከ30 በላይ አነስተኛ ሱቆች መቃጠላቸውም ታውቋል። የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንዳስታወቁት በከተማው በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች በኹለት ጎራ ተከፋፍለው ወደ ግጭት የገቡ ሲሆን መከላከያ ሠራዊት በስፍራው ተገኝቶ ውጥረቱን ባያረግበው ግጭቱ ወደ ከፋ አደጋ የሚያመራበት ሁኔታ እንደነበር ገልፀዋል። ትናንት ዓርብ ከማለዳ ጀምሮ አንጻራዊ ሰላም በከተማዋ ቢሰፍንም አሁንም የግጭት ሥጋት እንዳንዣበበ አዲስ ማለዳ በስልክ ያነጋገረቻቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

አምቦ
ከአዲስ አበባ ቦሌ ከጃዋር መኖሪያ ቤት የወጣው መረጃ ከአዲስ አበባ 125 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አምቦ ከተማ ላይም ኹከት ቀስቅሷል። በዚህ ኹከትም ሰዎች ቆስለዋል፤ ሕይወታቸውንም እንዲያጡ ሆነዋል። ቢቢሲ የአማርኛው ክንፍ የአምቦ ከተማ ሪፈራል ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅን ዋቢ አድርጎ እንዳስነበበው 14 ሰዎች ከፀጥታ አካላት በተተኮሰ ጥይት የተጎዱ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አምስት ያህሉ ሕይወታቸው እንዳለፈ አስታውቋል። ቢቢሲ እንደዘገበው ከሆነ አንድ የ80 ዓመት አዛውንት ከፀጥታ ኀይሎች በተተኮሰ ጥይት ተመትተው መሞታቸው ታውቋል።
በሰው ሕይወትና አካል ላይ ጉዳት ከመድረሱም ባሻገር በርካታ የንግድ ተቋማትም ላይ ጥቃት መድረሱን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአይን እማኞች ተናግረዋል።

ድሬዳዋ
ድሬዳዋ ባለፉት ቀናት በሰላም እጦት ውሎ እና አዳሯ ጭንቅ ነበር። አዲስ ማለዳ ወደ ኅትመት እስከገባችበት ሰዓት ድረስ ከተማዋ አሁንም በአለመረጋጋት ውስጥ ትገኛለች። በድሬዳዋ፣ ሐረር እና አካባቢው የሚገኙ የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንዳስታወቁት ባለፉት ቀናት ከድሬዳዋ ወደ ሐረር እና ከአዲስ አበባ ወደ ሐረር የሚያገናኙ መንገዶች በተለያዩ ቦታዎች ላይ ዝግ ሆነው ሰንብተዋል። በከተማዋ የኦሮሚያ ሰሌዳ የለጠፉ ተሸከርካሪዎች ብቻ ማለፍ ይችሉ እንደነበርም ከነዋሪዎች ለማወቅ ተችሏል።

በአካባቢው የሚገኙ የአዲስ ማለዳ ምንጮች የተፈጠረውን ሲገልፁ በከተማዋ በርካታ የንግድ ቤቶች የወደሙ ሲሆን በሰዎች ላይም የአካል ጉዳትና የሕይወት መጥፋት ጉዳት አጋጥሟል። በበርካታ የዜና አውታሮች እየተዘገበ የሚገኘው የሟቾች ቁጥር ያነሰ ነው ሲሉ ያስታወቁት ምንጮች አምስት ሰዎች ሞተዋል የተባለው በድሬዳዋ ከተማ ከዛ በላይ እንደሆነና በየቀኑ ሰዎች ተገድለው እንደሚገኙ አስታውቀዋል። በሐረር ከተማ ብቻ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን አዲስ ማለዳ ሰምታለች።
ከአወዳይ ጀምሮ ሐረር ከተማ ድረስ መንገዶች በተቃጠሉ ጎማዎች እና በትላልቅ ድንጋዮች ተሞልተው መመልከታቸውን እና ግጭቱ አሁንም ድረስ አለመብረዱን የዓይን እማኞች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከሰሞኑ የተቀሰቀሰውን ግጭት እና አለመረጋጋት በሚመለከት የሰላምና ደኅንነት ጥናት ከፍተኛ ባለሙያው ሰኢድ ነጋሽ ሙያዊ ትንታኔያቸውን ለአዲስ ማለዳ ሰጥተዋል። “በመጀመሪያ ደረጃ መንግሥት በማኅበራዊ ትስስር ገፆች በሚለቀቁ ጽሑፎችና መልዕክቶች ዙሪያ ጠንከር ያለ ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል” ሲሉ ይጀምራሉ። አያይዘውም ግለሰቦች በማን አለብኝት ለሚለቁት እና ብዙኀኑን ሰላም ለሚነሱት ጉዳይም መንግሥት ተጠያቂ የሚያደርግበት አካሔድ ዝቅተኛ መሆን አገሪቱ አሁን ላለችበት አዙሪት እና ትርምስ ዋነኛ ተጠቃሽ ነው ሲሉ ያክላሉ። “ግለሰቦቹ አይታወቁም እንዳይባል በሕዝብ ዘንድ በደምብ የሚታወቁ ናቸው” የሚሉት ሰኢድ አሁንም መንግሥት ጠንካራ ዕርምጃ መውሰድ ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋም ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በመሥራት ላይ የሚገኙት ሙሉቀን ሀብቱ ሲናገሩ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሕግ አስከባሪው በኩል የሚታየው የመለሳለስና ሕግን ለማስከበር ቁርጠኝነት ማነስ አሁን ላለንበት ችግር ዋናው ምክንያት ነው ሲሉ ይደመጣሉ። “አሁንም ቢሆን መንግሥት ይህ አገራዊ ችግር ከመባባሱ በፊት ፈጥኖ እልባት መስጠትና የአገሪቱ ሰላም ወደ ነበረበት መመለስ ይኖርበታል” ሲሉ ይናገራሉ። ከሰላም ማጣት ጋር ተያይዘው ዘርፈ ብዙ ችግሮች በኢትዮጵያ ላይ እንደሚከሰቱ የሚተነብዩት ሙሉቀን ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውረው መሥራትና መኖር አለመቻላቸው አንደኛው ማሳያ ነው ይላሉ። ሙሉቀን በዚህ ብቻ አያበቁም፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቡድን ማሰብ እና በፉክክር መኖር በስፋት ከመታየቱ ጋር ተከትሎ ሕግ በይፋ የሚጣስበትና ስርዓት አልበኝነቱም እየተስፋፋ በመምጣቱ የዜጎችን ሰላም ማስጠበቅ ከማይቻልበት ደረጃ ላይ እየተደረሰ እንደሆን ይናገራሉ።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here