ፖለቲካ እናድርገው!

0
577

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ከታሪክ መዝገብ ላይ መኖር አለመኖሩ፣ የእውነት ተፈጽሟል ወይስ አልተፈጸመም የሚለው ይቆየን። በምናውቀው ግን “የቀደመው” ኢሕአዴግ በሚመራው መንግሥት ብዙ ወጪ የወጣበት “አኖሌ” የሚባል ሃውልት ተገንብቷል። ይህም ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ጡት ቆርጠዋል ከሚል “ትርክት” መነሻ እንደሆነም በተለያየ ጊዜ ሰምተናል።

ታድያ ለእናቶቻቸውና ለእህቶቻቸው “ተቆርቋሪ” የሆኑ ሰዎች ያንን እያነሱ ዛሬም ድረስ ቂም ይዘው የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ወገን ናቸው ያሉትን እንዲሁም ራሳቸው ዳግማዊ አጼ ምኒልክን አምርረው ይጠላሉ። ከ“መቆርቆራቸው” የተነሳ ቂም ይዘው ዛሬ ድረስ ሕመሙ ይሰማቸዋል፣ ዛሬ ድረስ ይቆጫሉ። እንዳልኳችሁ ነው! ያውም እውነት የተደረገ ስለመሆኑ የተረጋገጠ ማስረጃ በማይሰጥበት ሁኔታ ማለት ነው።

እነዚህ የዛሬ “ሰዎች” ለቀደሙት እናቶቻቸው “እናስባለን! ወገኖቻችን ናቸው! እነሱ ተነኩ ማለት እኛም ተነካን ነው!” ብለው ራሳቸውን የ‘ታሪኩ’ አካል አድርገው ይናገራሉ። ይህ ግን የፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ነው። “ተቆርቋሪነቱ” የፖለቲካ ማገዶ መሆኑ እንዴት ይታወቃል? ዛሬ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ግፍና በደል ያላስጨነቀው፣ “በቃ!” እንዲል ያላስገደደው፣ ያላሳዘነውና ለሴቶች መብት ያልቆመ፤ ጭራሹን ደፋሪና አጥፊ የሆነ ሰው በምን ተዓምር ነው ለቀደሙት ሴቶች እንዲህ ሊቆረቆር የሚችለው?

እህቶቼ እመኑኝ! የእውነት የሆነ ታሪክም ይሁን የተፈጠረ፤ ዓላማው የፖለቲካ መቆመሪያ እንጂ ተቆርቋሪነት አይደለም። አዲስ አበባ ገና ለገና “የእኛ ናት!” ባዮች ድንጋይ መወራወሪያ ሜዳ እንዳትሆን ብሎ ባለአደራ ምክር ቤት በግለሰቦች ተነሳሽነት ተፈጥሮ መሪዎችን ሲፈትን አይተናል፣ አገር ሆነውና ብዙ ኀይል ይዘው አንዳች ያልሠሩ ሁሉ በድንገት እየተነሱ ክልል እንሁን ጥያቄን በጉልበት ሲያቀርቡ ተመልክተናል፤ ሴቶች ስብዕናቸውና ሰውነታቸው ተደፍሮ የሰው ያለ ሲሉ ግን ማንም ምንም አይልም። “ለምን?” ቢሉ ይኼ ፖለቲካ አይደለማ!

በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ዛሬም አሉ። ሰሞኑን በተለያዩ ማኅበራዊ ገጾች ላይ አነጋጋሪ ከሆኑ ክስተቶች መካከል አንዱ ይኸው ነበር። በትግራይ ክልል ሃምሳ ሴቶች ላይ አስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈጽሞ የተከሰሰ ሰው በዋስ ተፈታ፤ ያውም የሕግ አስከባሪ ነው የተባለ ፖሊስ። ነገሩ ፖለቲካ ቢሆንስ ኖሮ? አገር ምድሩ ሲጮኽ እንሰማ ነበር። ግን አልሆነም፤ ለምን? ፖለቲካ ስላልሆነ።

እርግጥ ነው በመጮኽ ብቻ ለውጥ የሚመጣ ላይመስል ይችላል፤ ግን እንደምናየው በአገራችን ለሚታየው የፖለቲካ ነፋስ ለውጥ እንዲህ ዋጋ የሌላቸው የሚመስሉ ትንንሽ የተባሉ ጩኸቶች አበርክቶ ነበራቸው። ጥቂት የሚመስሉ የግጥም ስንኞች፣ ቀላል የሚመስሉ መልዕክቶች፣ ጠብ የሚሉ የማይመስሉ ሐሳቦች ተደራርበው ነው ዛሬ የምንተነፍሰውን የፖለቲካ አየር ያመጡት።

ይመስለኛል እንደውም ፖለቲካ አንድም ኀይል የሆነው እያንዳንዱን ድምጽ ማክበሩ ነው። አንድ ግለሰብ በድንገት ተነስቶ ‘አክቲቪስት’ ነኝ ብሎ፣ አገር ልትፈርስ ትችላለች ሲል እንኳን ድምጹ ዜና ይሆናል። ፖለቲካ ሐሳብና ሰው አይንቅም። በዚህ በኩል ስለሰብኣዊ መብት ሲነሳና የሴቶች ጉዳይ ላይ ግን ከከንፈር መጠጣ ያለፈ ድምጽ አንሰማም። “አያሳዝንም?!” ነው መልሱ፤ ጩኸቱ በየሳምንቱ ሌላ ነው።

መገናኛ ብዙኀን ለሴቶች ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮችን ትተው “ወይዘሮ እና ወይዘሪት” መባልን ርዕሰ ጉዳይ ያደርጉታል። በሴቶች ጉዳዮች ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ ማኅበራትና ተቋማት ከተማ ላይ የታጠሩ እስኪመስሉ ድረስ ተጽዕኖ መፍጠር አልቻሉም፤ እንቅስቃሴያቸውም የቅንጦት መሰለ፤ ነገሩ ስለ ሰብኣዊ መብት መሆኑ ተዘነጋ። ይመስለኛል ትኩረት ማግኛ መንገዱ አንድና አንድ ነው፤ የሴቶች ሰብኣዊ መብት ጉዳይን ፖለቲካ እናድርገው!

ሊድያ ተስፋዬ

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here