በጤንነት አጠባበቅ፣ አመጋገብ እና የአልኮል መጠጥ አጠቃቀም ላይ በርካታ መጽሐፍት ይጻፋሉ። በኢትዮጵያ በ1948 የታተመውን ‹ሀብትና ጤንነት› የሚል ርዕስ ያለው የመዓዛ ለማ መጽሐፍ በማንበብ እነሆ ቅምሻ የሚሉን ብርሃኑ ሰሙ ናቸው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ለተለያዩ ሕመሞች የሚሰቃዩ ዜጎችን ለማሳከም በየመንገዱ ዳርቻ፣ እንዲሁም በብዙኃን መገናኛዎች ሳይቀር፣ በግል እና በማኅበር መለመን እያደገ የመጣ ክስተት ሆኗል። የሕመሙ ዓይነትም እንዲሁ በርክቷል። ከዚህ እውነታ በመነሳት የጤንነት አጠባበቅ መጽሐፍት የጻፉ ሰዎች አሉ።
“ሀብትና ጤንነት” በሚል ርዕስ በደራሲ መዓዛ ለማ በ1941 ተዘጋጅቶ፣ ከ7 ዓመት በኋላ በሰኔ ወር 1948 ለአንባቢያን የቀረበው መጽሐፍ፥ አርቆ አስቦ፣ አደጋን ቀድሞ ለመከላከል ጥረት አድርጎ ነበር የሚያስብል ቁም ነገሮችን በውስጥ ይዟል። ከዛሬ 62 ዓመት በፊት በ180 ገጽ ተጠርዞ የቀረበው መጽሐፍ በተስፋ ገብረሥላሴ ማተሚያ ቤት የታተመ ሲሆን በዘመኑ የመሸጫ ዋጋው 2 ብር ከ50 ሣንቲም ነበር። ደራሲው በዘመኑ ይዘጋጁ እንደነበሩ ጥራዞች፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ በወሰዷቸው በርካታ ጥቅሶች በመታገዝ መልዕክታቸውን ለማስተላለፍ ጥረት አድርገዋል። ምግብና መጠጥን በመከልከል ወይም የሚመገቡትን በመምረጥ፤ አገርን፣ ሕዝብን፣ ሥልጣንን፣ ክብርን፣ የግል ጤንነትን መጠበቅ እንደሚቻል የሚያሳዩ የቀድሞ ዘመኑ ባሕልና ልምዶች ምን እንደሚመስሉ በርካታ ታሪኮችን አቅርበዋል።
በዐፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት የነበረው አገራዊ ሕግና ደንብ አንዱ ነው። በዚያ ዘመን ተራ ተርታ የሚባለው ሕዝብ በቤቱ ጠጅ እንዳይጥል፣ በግ፣ ፍየልም ሆነ ፍሪዳ አርዶ እንዳይበላ፣ በጠፍር አልጋ እንዳይተኛ፣ ማንኛውንም ዓይነት ጥላ እንዳይዝ፣ በተሸለመ ፈረስ እንዳይቀመጥ… የሚከለክል ሕግ ወጥቶ ነበር። ይህን ሕግ የተላለፈ ሰው “በወንጀል እየተከሰሰ ሀብቱን ይወረስ ነበር።ይህ የተደረገው ያገራችን ሰው ሥጋና ጠጅ የሚወድ ስለሆነ ተሾሜ፣ ተሸልሜ፣ ሥጋና ጠጅ እንደልቤ አገኛለሁ በማለት ንጉሡን እንዲያገለግልና ደጅ እንዲጠና ታስቦ የተደረገ” ነበር።
ለዚህ አዋጅ መሻር ምክንያት የሆነው ጌታሁን ግሤ የተባለና በእርሻ፣ በከብትና በንብ ማርባት የከበረ ገበሬ፤ ለማርያም ክብረ በዓል ድል ያለ ድግስ ደግሶ ካህናቱንና ምዕመናንን መጋበዙ እንደወንጀል ተቆጥሮበት፤ ከሳሾቹ ዐፄ ዮሐንስ ዘንድ ሔደው “ጌታሁን ግሤ የተባለ ጥጋበኛ ከንጉሥ ዘንድ ቀሚስ ይቅርና ለምድ በትከሻው ያላጠለቀ ከቤቱ ጠጅ ጥሎ፣ ፍሪዳ አርዶ፣ ባላገሩን ሰብስቦ እያበላና እያጠጣ ሲያዘፍንና ሲያሸልል ውሏል፤ የንጉሡን አዋጅ ጥሷልና ቀርቦ ይቀጣ” በሚል ክስ አቀረቡበት።
ጌታሁን ግሤ ከቀረበበት ክስ እራሱን ለማዳን በሚችለው አቅም ተከራከረ። ድግሱን ያዘጋጀበት ዋነኛ ምክንያት በደጁ ያለችው የማርያም ክብረ በዓልን ለማድመቅ መሆኑን ሲያስረዳ፥ በችሎቱ ላይ የሸዋ መኳንንት ንጉሥ ምኒልክ፣ የወሎ መኳንንት ንጉሥ ሚካኤል፣ የጎጃም መኳንንት ንጉሥ ተክለሃይማኖት ነበሩ። የግራ ቀኙን ክርክር የሰሙት ዐፄ ዮሐንስ የሚከተለውን ፍርድ በመስጠት ለዘመናት ሲሠራበት የነበረውን ሕግ ሻሩ “የሰው ገንዘብ ሲሰርቅ ወይም ከዱር ተቀምጦ ሲቀማ አልተገኘምና የሚያርስበት ካላጣ የገዛ በሬውን ቢያርድ ገንዘብ ካልቸገረው ማሩን ቢጠጣ አያስከስሰውም፤ ያውም ለማርያም ዝክር ያደረገው ነውና አያስቀጣውም፤ ወደፊትም ሕዝቡ እንደፈቀደ ይተዳደር” ብለው ፍርድ ሰጡ።
‹አቶ ሺሺጉ አሉ ወይ?›
መጽሐፉ የያዘው ሌላው ታሪክ ከልዑል ራስ እምሩ ጋር በተያያዘ የቀረበ ነው። ልዑሉ የሐረር ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ በነበሩበት ዘመን ሕዝቡ በመልካም ሁኔታ እንዲተዳደርና በሠላምና በፀጥታ እንዲሰፍር በማለት ካወጡት ሕግና ደንብ መካከል ሰክሮ የተገኘ ሰው ታስሮ ፍርድ ቤት በመሔድ 5 ብር መቅጫ ከፍሎ ይለቀቅ የሚል ትእዛዝ ሰጥተው ነበር። “ሹማምንቱ ይህን ትእዛዝ አክብረውና ተቀብለው ይፈፅሙ ነበር። የስካር ምንጩን ለመድፈን አስበው አረቄና ጠጅ በከተማው እንዳይሸጡ፣ ሲሸጥ የተገኘውም ሰው መቀጫ እንዲከፍል ትእዛዝ ሰጥተው ነበር። ትእዛዝ ተላላፊዎች የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ግን በስውር ይሸጡ ስለነበር የመጠጥ ፍቅር ያደረባቸው ‹አረቄ አለ ወይ?› በማለት ፈንታ ‹አቶ ሺሺጉ አሉወይ?› እያሉ፣ ‹ጠጅ አለ ወይ?› በማለት ፈንታ ‹አቶ ማሩ አሉ ወይ ?› እያሉ በፈሊጥ እየጠየቁ፣ እየገቡ በመጠን እየጠጡ፣ ተጠንቅቀው ጠብና ክርክር ሳይታይባቸው፣ መውደቅ መነሳት ሳይደርስባቸው ወደ የቤታቸው ስለሚሔዱ የሕዝቡ ፀጥታ ተጠብቆ ነበር።”
የደራሲ መዓዛ ለማ “ሀብትና ጤንነት” መጽሐፍ አገኘሁ ብሎ ምግብን ማግበስበስ፣ ለአመጋገብ ምርጫና ጥንቃቄ አለማድረግ… የሚያስከትለውን ፈርጀ ብዙ ጉዳት ለማሳየት ያቀረቧቸው ታሪኮች፤ የሚበዙት ከአልኮል መጠጦች ጋር የተያያዙ ናቸው። የልዑል ራስ እምሩን ትዕዛዝ ለማስፈፀም የተጉትና ከሐረር ማዘጋጃ ቤት ሹም ከነበሩት ከቀኛዝማች ጀማነህ ጋር በተያያዘ የቀረበው ታሪክ ሌላኛው ነው።
የሚያሰክሩ መጠጦች በሐረር ከተማ እንዳይሸጡ በተከለከለበት ወራት አንድ ሰው በመሸታ መጠጥ ሰክሮ፥ ስካሩ እንዳይታወቅበት ተጠንቅቆ ቀስ እያለ ሲጓዝ፣ የሐረር ማዘጋጃ ቤት ሹም የነበሩት ቀኛዝማች ጀማነህ በመንገድ አግኝተው “ለምን ሰከርህ?” ብለው ቢጠይቁ “አልሰከርሁም” አላቸው። “ጠጥተህ የለምን” ቢሉት “አቶ እገሌ ቤት 9 ብርሌ ጠጅ፣ ከሙሴያኒ ቤት 7 መለኪያ አረቄ ጠጥቻለሁ የሆነ ሆኖ አልሰከርሁም” አለ። ቀኛዝማች ጀማነህም “ሰክረህ ባትወድቅም አብዝተህ መጠጣትም ጥፋት ነው፤ ይልቁንም የትም አድረህ አውሬ ከሚበላህ ወይም በሽታ ከሚያድርብህ ከዘብጥያው አድረህ ጧት ትሄዳለህ” ብለው ለዘበኞች ሰጥተውት ታስሮ አደረ ።
የጸሐፊ ተውኔቱ መንግሥቱ ለማ አባት ከሆኑት ከአለቃ ለማ ኃይሉ ጋር በተያያዘ መጽሐፉ ያሰፈረው ታሪክም አለ። ታሪኩ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “የክህደት ቁልቁለት”የሚል ርዕስ ባለው መጽሐፋቸው“የማይጠራጠር ሰው ከእውነት ላይ አይደርስም”ያሉትን ኃይለ ቃል የሚያስታውስ ነው።
አንድ ታላቅ መኮንን ከቤቱ ግብዣ አድርጎ ጠላውን፣ ጠጁንና አረቄውን በየዓይነቱ አዘጋጅቶ መኳንንቱንና ወይዛዝርቱን ጠርቶ ሲጋብዝ ከመብል በፊት የአረቄ መጠጥ (አፕሬቲፍ) ቢያቀርብ ከተጋባዦቹ አንዱ አለቃ ለማ ኃይሉ አረቄ ሊጠጡ አለመፍቀዳቸውን አስታወቁ። መኮንኑም “ይህ ኮኛክ አረቄ ከዚህ አገር የተሠራ አይደለም፣ ከባሕር ማዶ እንደተዘጋጀ የመጣ ነውና ይጠጡ” አላቸው።
አለቃ ለማም “እኔስ ይህን አረቄ አልጠጣም ያልኩት ይህንኑ አውቄ አይደለምን? ጌሾው ከጓሮዬ ተቆርጦ ገብሱ ከመሬት መጥቶ ከገዛ ቤቴ ባለቤቴ የጠመቀችውን ጠላ እንኳ ልጠጣ በፈለግኩኝ ጊዜ የሚያቀርቡልኝ ቤተሰቦቼ መጀመሪያ እየቀመሱ እየሰጡኝ ነው የምጠጣው። ይህንማ ከሰው አገር የመጣውን የጠመቀው ማን እንደሆነ፣ የተሠራውስ ከምን እንደሆነ አውቄ እጠጣለሁ? ካገሩ ሲመጣም እንደ ተዘጋ ነው። ከዚህም ነጋዴዎች እንኳ ቀምሰው አይሸጡ። ቢሆንስ ያረቄ መጠጥ ከማቃጠሉ በተቀር የውኃ ጥም አያስታግስ፣ የረሀብን ኃይል አይቀንስ፣ ከቶ ለምን ጉዳይ ይጠቅመኛል ብዬ ልጠጣው? እኔስ ይህን የቀረበልኝን የገብስ ጠላ እጠጣለሁ። ደግሞ አንዲት ብርሌ ጠጅ ብትሰጡኝ እጨምራለሁ እንጂ አረቄንስ አልጠጣም” አሉ።
ደራሲ መዓዛ ለማ “ሀብትና ጤንነት” ባሰኙት መጽሐፋቸው ማጠቃለያ ያነሱት ሐሳብም በአለቃ ለማ ኃይሉን ጥርጣሬ ውስጥ ያለውን እውነት ለመመርመር ዕድል የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን፣ አሁን ኢትዮጵያዊያን ባልተለመዱ ሕመሞች ተጠቂ ለመሆናቸው እየተሰጡ ላሉትግምታዊ አስተያየቶችስ ምን ያህል እውነትነት ይኖራቸው ይሆን? የሚለውንም ለመመርመርም የሚያነሳሳ ነበር። “የአልኮል መጠጦች (በተመረቱበት)አገር በከፍተኛ ዋጋ ሲሸጡ ከአገራቸው ወጥተው የትራንስፖርቱንና ታክሱን ሁሉ ተሸክመው ከሰው አገር በደረሱ ጊዜ (በተመረቱበት) አገር ይሸጡበት ከነበረው ዋጋ ቀንሰውና ዝቅ ባለ ዋጋ የሚሸጡበት በምን ምክንያት ይሆን?” ያሉት ደራሲ መዓዛ ለማ፣ በዘመኑ አንድ ፓውንድ በስንት የኢትዮጵያ ብር ይመነዘር እንደነበር ባያመለክቱም፣“ዊስኪ አንዱ ጠርሙስ ፋብሪካው ባለበት በሎንዶን ከተማ በ50 ብር በአዲስ አበባ ላይ በ18 ብር ይሸጣል” በማለት ምክንያቱን የመጽሐፋቸው አንባቢያን እንዲወያዩበት ጋብዘው ነበር።
ብርሃኑ ሰሙ በተለያዩ የሕትመት ብዙኃን መገናኛዎች ለሁለት ዐሥርት ዓመታት የሠሩ ሲሆን፣ የመጽሐፍት ደራሲም ናቸው፡፡ በኢሜይል አድራሻቸው ethmolla2013@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ፡፡