ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ በብደርና በድጋፍ ያገኘችው 600 ሚሊዮን ዶላር በጦርነትና በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች ማገገሚያ እንዲውል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።
ከዓለም ባንክ ከተገኘው አጠቃላይ ገንዘብ 400 ሚሊዮን ዶላር ያህሉ በብድር የተገኘ ሲሆን፣ 200 ሚሊዮን ዶላር በእርዳታ የተለገሰ ነው። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥቅምት 08/2015 ባካሄደው 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባ ከዓለም ባንክ የተገኘውን የብድርና ድጋፍ ስምምነት አዋጅ ቁጥር 2/2015 አድርጎ አጽድቋል።
የብድርና ድጋፍ ስምምነቱ የሥርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ መርሃ ግብርን ለማስፈጸም የሚውል ሲሆን፣ የምክር ቤቱ አባላት የተገኘው ገንዘብ በድርቅና ጦርነት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የሚገኙ በሰብል ልማትና በእንስሳት እርባታ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች እንዲውል ጠይቀዋል።
የምክር ቤት አባላቱ አክለውም፣ በሀብት ክፍፍሉ ወቅት ኹሉንም የአገሪቱ አካባቢዎች ያማከለ ፍትሐዊ ተደራሽነት እንዲኖር አሳስበዋል። ገንዘቡ በዋናነት አርሶ አደር እና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን የጠቆመው ምክር ቤቱ፣ የሴት አርሶ አደሮችንና ወጣቶችን በተለየ መልኩ ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ አዳዲስ ግኝቶችን፣ አሠራሮችንና የቴክኒክ ድጋፎችን ያደርጋል ሲል ነው የገለጸው።
የአርሶና አርብቶ አደሩን ገቢ በማሳደግና ከድህነት በማላቀቅ፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ብሎም እሴት የታከለበት የግብርና ግብዓት ለውጭ ገበያ ማቅረብ እና በገጠር በቂ የሥራ ዕድል መፍጠር አስፈላጊ ነውም ብሏል።
ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው ለሥርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚውል ብድር ከዓለም ዐቀፉ የልማት ማኅበር ለማግኘት የተፈረመውን የብድር ስምምነት የማስጸደቂያ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ያጸደቀ ሲሆን፣ የገንዘብ ሚኒስቴር በብድር ስምምነቱ የተገኘውን ገንዘብ በብድር ስምምነቱ በተመለከቱት ሁኔታዎች መሠረት ሥራ ላይ እንዲያውል በአዋጁ ሥልጣን ተሰጥቶታል።
መርሃ ግብሩ በተመረጡ 181 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ቤተሰቦችን በቀጥታ እንዲሁም 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቤተሰቦችን በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ታምኖበታል።
የሥርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ መርሃ ግብሩ የተሻሻሉ የገበያ አገልግሎቶች እና መሠረተ ልማት፣ የኢንተርፕራይዞች ልማት፣ የአነስተኛ አርሶ አደሮችን የገበያ ትስስር ማጠናከር እንዲሁም የእሴት ሰንሰለትን ማጠናከር የሚሉ ዋና ዋና ክፍሎችንም ይዟል።
ከዓለም ዐቀፉ የልማት ማኅበር በብድር የተገኘው 400 ሚሊዮን ዶላር ከወለድ ነጻና በረጅም ጊዜ የሚከፈል መሆኑም ተመላክቷል። በዚህም የስድስት ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ የሚያልቅ መሆኑ ተገልጿል።
ይሁን እንጂ፣ ባንኩ በሚወስነው መሠረት ጥቅም ላይ ባልዋለው የብድሩ ገንዘብ ላይ በዓመት እስከ 0.5 በመቶ የሚደርስ የግዴታ ክፍያ ሊከፈልበት ይችላል ነው የተባለው።
በብድር የተገኘው ገንዘብ የኢትዮጵያን የምግብ ዋስትና ችግርን በመቅረፍ፣ ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል እንዲሁም ለገበያ ተፈላጊነት ያላቸውን ምርቶች በማምረት የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የጎላ ነው ተብሏል። በተለይም በመስኖ መሠረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ትኩረት በመስጠት ጠንካራ አነስተኛ መስኖ ልማት አስተዳደር ለመፍጠርም ታስቧል።
ቅጽ 4 ቁጥር 207 ጥቅምት 12 2015



