ቱሪዝም በኢትዮጵያ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ዘርፍ መሆኑ እሙን ነው። ኢትዮጵያ በርካታ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ የቱሪስት መስህቦች ያላት አገር መሆኗም ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ በብዙ ችግሮች እየተፈተነ ያለ ዘርፍም ሆኗል። ቀደም ብሎ በዓለም ዐቀፉ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተነሳ የበርካታ አገራት ቱሪዝም ክፉኛ ተፈትኗል። ሆኖም ወረርሽኙ የቀነሰ ሲመስል አገራት ተዘግቶ የነበረውን ዘርፍ በመክፈት እንዲሁም በደንብ ለማነቃቃት በርካታ እርምጃዎችን ሲወስዱ ተስተውሏል።
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ደግሞ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተፅዕኖ ሳያገግም፣ በጦርነትና በግጭቶች ጉዳት እያስተናገደ መሆኑ ይገለጻል፡፡ ይህን ተከትሎም አገሪቱ ያላትን የቱሪዝም ሀብት በማስተዋወቅና ዘርፉን በማልማት፣ በዓመት ስታገኘው የነበረውን እና ማግኘት ያለባትን ገቢ እያጣች እንደሆነ ነው የሚወጡ መረጃዎች የሚጠቅሱት፡፡
በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎች ያሉትና በዚህ ዘርፍ በስፋት የሚታወቀው የሰሜኑ ክፍል ደግሞ ይበልጥ ከተጎዱ አካባቢዎች ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።
ቀድሞውንም ኢትዮጵያ ያላት የቱሪዝም ሀብትና የምታገኘው ገቢ የማይጣጣም መሆኑ ሲገለጽ የነበረው ይህ ዘርፍ፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከመቼም ጊዜ በከፋ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ይነገራል። አክሱምን ጨምሮ በትግራይ ክልል ካሉ በርከት ያሉ የቱሪዝም ሀብቶች የሚገኘው ገቢ ኹለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ዜሮ መሆኑ የሚታወቅ ነው።
አማራ ክልልም ባለፈው በጀት ዓመት ከቱሪዝም ሀብት ያመነጨው ገቢ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በፊት ያገኘው ከነበረው ከ50 በመቶ በታች ያነሰ መሆኑን ከዚህ በፊት አዲስ ማለዳ መዘገቧ አይዘነጋም።
እንዲሁም በጦርነቱ ወቅት በርከት ያሉ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ የቱሪስት መስህቦች ጉዳት ማስተናገዳቸው ደግሞ የዘርፉን ችግር ይበልጥ ያባብሰዋል ነው የሚባለው። ጦርነቱ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው የክልሉ ቦታዎች በሚገኙ መዳረሻዎች ጭምር አሉታዊ እያሳደረ መሆኑ ይነሳል።
በቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ የሚታየው ችግር የአንድ ወይም የኹለት ክልል ብቻ አለመሆኑም ይስተዋላል፡፡ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች ትኩረት ይስብ የነበረው የአፋር ዝቅተኛ ስፍራም ከእነዚህ ተጠቃሽ ነው። እንዲሁም፣ በሰሜን ካለው ሁኔታ የተሻለ እንደሆነ የሚጠቀስ ቢሆንም በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች ያለው የቱሪዝም እንቅስቃሴም የዚሁ ችግር ሰለባ ሳይሆን እንዳልቀረ ማሳያዎች አሉ።
በተለይ በኦሮሚያ በስፋት የሚንቀሳቀሰውና አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው የሸኔ ቡድን በደቡብ እና በኦሮሚያ ክልሎች ባለው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ ቀጥተኛ ስጋት መደቀኑ ተስተውሏል።
ላሊበላ
የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት በአማራ ክልል ላሊበላን ጨምሮ ከሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እና ከሌሎች የቱሪስት መዳረሻዎች የሚገኘው ገቢ ከበፊቱ አንጻር አነስተኛ መሆኑን በተለያየ ጊዜ የወጡ ዘገባዎች ያስረዳሉ።
የላሊበላ ቅርስ ሰፊ የቱሪዝም መዳረሻ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ኢትዮጵያ ከዚህ ቅርስ ከምታገኘው ገቢ ባለፈ፣ የላሊበላ ከተማ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንትም ግብርና ወይም ሌላ ንግድ ሥራ ሳይሆን ቱሪዝም እንደሆነ ይገለጻል።
ስለሆነም፣ እንደአገር ከሚታጣው ገቢ ጎን ለጎን በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ የደቀነው ችግር ጉልህ ነው። ለአብነት ከኹለት ዓመት በፊት በዓመት እስከ 32 ሺሕ የውጭ ጎብኝዎች ቅርሱን ይጎበኙት ነበር ይላል የላሊበላ ከተማ ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት።
አክሎም፣ በሩብ ዓመት ሲሰላ ስምንት ሺሕ ገደማ የውጭ ቱሪስቶች ላሊበላን ይጎበኙ እንደነበር አንስቶ፣ በተያዘው 2015 ሩብ በጀት ዓመት ግን 800 የውጭ አገር ቱሪስቶች ብቻ ናቸው ቅርሱን የጎበኙት ሲል ይገልጻል።
ከበፊቱ የጎብኚ ቁጥር አንጻር እንዲሁም በከተማው ማኅበረሰብ ላይ እየደረሰ ካለው ጫና አኳያ ሲታይ በጣም አስደንጋጭ ነው። ግን ደግሞ ከሩብ ዓመቱ በፊት በነበሩት ወራት ከነበረው የጎብኚ ቁጥር አንጻር ሲታይ የአሁኑ የተሻለ በመሆኑ ተስፋ ሰጪ ነው በማለት ጽሕፈት ቤቱ ያስረዳል።
እንደ ጽሕፈት ቤቱ ገለጻ፣ ሕወሓት በክልሉ የከፈተው ጦርነት ከቆመ በኋላ ሦስተኛ ዙር ወረራ እስከሚፈጽምበት ጊዜ የነበረው የአገር ውጪ ጎብኚ መጠን በቁጥር 770 ገደማ ነበር። ስለሆነም፣ ከዚህ አንጻር ሲታይ በሩብ ዓመቱ የተሻለ ጎብኚ መጥቷል ነው የሚለው። አካባቢው ከጦርነት ስጋት ነጻ ቢሆን ኖሮ ግን ላሊበላን ለመጎብኘት 10 ሺሕ ገደማ የውጭ ቱሪስት በሩብ ዓመቱ መምጣት ነበረበት።
የላሊበላ ከተማ የባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እንዲሁም ምክትል ከንቲባ አዲሴ ደምሴ (ዲ/ን) ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ አሁን ያለው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ሁኔታ መልካም ነው ብለዋል፡፡ ከኹለት ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ግን ዜሮ ነው ማለት ይቻላል ሲሉ ይገልጻሉ።
ባለፈው መስከረም 21/2015 በርከት ያሉ የአገር ውስጥ ቱሪስቶች ቦታው ላይ መገኘታቸውን በመግለጽም፣ ከአዲስ አበባም የአየር በረራ መኖሩ ተስፋ ሰጪ መሆኑን አንስተዋል።
ሆኖም ለቱሪዝም የጸጥታ ሁኔታ የጀርባ አጥንት እንደሆነ የጠቀሱት ኃላፊው፣ ከነበረው ጦርነት ጋር ተያይዞ የተከሰቱ ችግሮች አሁንም ለከተማዋ የቱሪዝም ፍሰት ከፍተኛ እንከን ሆነው መቀጠላቸውን አመላክተዋል።
ሕወሓት ጦርነት ከከፈተበት ወቅት ጀምሮ መብራት ማግኘት ያልተቻለ ሲሆን፣ በቅርቡ ከገንዘብ ሚኒስቴር በተገኘ 15 ሚሊዮን ብር፣ ከተማውን ለአራት በመክፈል በቀን ለአራት ሰዓት መብራት እንዲያገኝ እየተደረገ ነው ብለዋል።
‹‹መብራት መሠረታዊ ነገር ነው፤ በተለይም ለቱሪስት ከተሞች›› ካሉ በኋላም፣ ላሊበላ ውሃ የምታገኘው ከዝቅተኛ ቦታ ተገፍቶ በሚወጣ ውሃ በመሆኑና ለዚሁ የሚሆን የመብራት ኃይል ባለመኖሩ ማኅበረሰቡ በኹለት ሳምንት አንዴ ውሃ እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑን ሳይጠቅሱ አላለፉም።
‹‹እነዚህ ጥረቶች ከምንም ይሻላሉ እንጂ በዚህ የተነሳ ከነበሩት 40 በላይ ሆቴሎች አገልግሎት እየሰጡ ያሉት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ከመብራት ጋር የተያያዙ ሥራዎች በሙሉ ቆመዋል። በርካታ አስጎብኚዎች ተበትነዋል። ሌላ ከተሞችን ብንጠራ አማራጭ የኢኮኖሚ ምንጭ አላቸው። ላሊበላ ግን ቱሪዝም ብቻና ብቻ ነው መኖሪያዋ። ከቀን ሠራተኛ እስከ ባለሀብት ሕይወቱ የተመሠረተው በቱሪዝሙ ላይ ነው። ስለሆነም አሁን ያለው ሁኔታ ከባድ ችግር እየፈጠረ ይገኛል።›› ኃላፊው ያሉት ነው።
ከኹለት ዓመት በፊት ማኅበረሰቡ ከጎብኚዎች የሚያገኘውን ጥቅም ሳይጨምር በዓመት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ይገኝ ነበር። ይህ አሁን አይታሰብም በማለት በዚህ ወቅት ያለውን ዝቅተኛ የቱሪስት ፍሰትና ገቢ ይጠቅሳሉ።
የከተማዋ የውስጥ ለውስጥ መስመር ግንባታ ከዘጠኝ ዓመት በላይ መጓተቱንም እንደሌላ የዘርፉ እንከን አንስተዋል። በቻይና የሚገነባው ይህ መንገድ ለረዥም ጊዜ ተቋርጦ የቆየ መሆኑን በመግለጽ፣ አሁንም በቅርብ ያጠናቅቀዋል ተብሎ እንደማይታሰብ፤ እንዲያውም በጦርነቱ ወቅት ዘረፋ ተፈጽሞብኛል በማለት መንግሥትን ካሳ እየጠየቀ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
ከጋሸና ላሊበላም እንዲሁ ተጀምሮ ያልተጠናቀቀ መንገድ መኖሩ ለቱሪዝም እንቅስቃሴው ተጨማሪ ችግር መሆኑን ጠቅሰው፣ ሌሎች ማስተካከል የሚቻሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም ከተማዋ መብራት ማግኘት እንድትችል ከክልልና ከፌዴራል መንግሥታት ጋር እየተነጋገርን ነው ያሉ ሲሆን፣ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆንም ለቱሪስት ድጋፍ ሰጪዎች የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጡ ጠቁመዋል።
አገልግሎት ያቋረጡ ሆቴሎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ጥረቶች መኖራቸውን አክለውም፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችን ቦታው ድረስ በመጥራት ዜጎቻቸውን እንዲጋብዙ ጥሪ ቀርቧል ነው ያሉት።
በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ቦታው የሚያቀኑ የውጭ መገናኛ ብዙኀንም ስለ ላሊበላ ሽፋን እንዲሰጡ እየተደረገ እንደሚገኝ ሳይጠቅሱ አላለፉም።
ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ
ይህ ፓርክ የኢትዮጵያ ትልቅ የቱሪዝም ሀብት ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ ነው። የአገሪቱ ከፍተኛ ቦታ፣ ተራሮች እንዲሁም በርካታ ብርቅዬ የዱር እንስሳት ያሉበት ነው። በየዓመቱም ቁጥሩ የላቀ የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስት ሲጎበኘው እንደኖረ ይገለጻል።
ሆኖም ቀድሞ በኮሮና ቫይረስ በኋላም በጦርነቱ ምክንያት የቱሪስት ፍሰቱ እጅጉን መቀነሱ ተነግሯል። ፓርኩ በተለይም ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ልቅ ግጦሽ፣ የደን ጭፍጨፋ እንዲሁም መሬት ወረራ የመሳሰሉ ጉዳቶች እንዳጋጠሙትና እነዚህም የወደፊት የቱሪዝም ገቢው ላይ የጎላ ጫና እንደሚፈጥሩ የፓርኩ ጽሕፈት ቤት ከወራት በፊት ለአዲስ ማለዳ መግለጹ አይዘነጋም።
በ2011 በሦስት ወራት ብቻ ከሦስት ሺሕ በላይ የውጭ ቱሪስቶች እንደጎበኙት እና ከዚህም ከኹለት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደተገኘ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ በወረርሽኙ እንዲሁም በፖለቲካ አለመረጋጋት የተነሳ የቱሪዝም እንቅስቃሴው 99 በመቶ መቆሙ ተነገረ።
ሆኖም በ2011 በሩብ ዓመት የተገኘው ገቢ ኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ጀምሮ እስካሁን በዓመትም እንደማይገኝ ይነሳል። በዚህ የተነሳም እስካሁን በፓርኩ ለቱሪስቶች አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ከ20 ሺሕ የማያንሱ ዜጎች ለጉዳት መዳረጋቸው ነው የተገለጸው።
በክልሉ የሚገኙ ሌሎች በርካታ ጥብቅ ሥፍራዎችና ፓርኮች እንዲሁም መካነ ቅርሶችም በጦርነቱ በደረሰባቸው ጉዳት እስካሁን የቱሪዝም እንቅስቃሴያቸው ወደነበረነበት መመለስ እንዳልቻለ ይነሳል።
ስለሆነም፣ ቀድሞም በመሠረት ልማት ጉድለት፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ድክመት እና በሌሎች ተያያዥ ችግሮች ሲፈተን የኖረው የኢትዮጵያ ቱሪዝም አሁን ደግሞ በጦርነትና በግጭቶች የዘርፉ ችግር የባሰ መሆኑ ነው የሚነገረው።
አዲስ ማለዳ ባለፈው በጀት ዓመት ከዘርፉ ምን ያህል ገቢ ተገኘ ስትል ቱሪዝም ሚኒስቴርን የጠየቀች ሲሆን፣ ተቋሙ ኹሉም ክልሎች ያገኙትን ገቢ ባለመላካቸው እስካሁን አልታወቀም ብሏል። እንዲሁም ሌሎች ጥያቄዎችን በማንሳት ማብራሪያ እንዲሰጣት የቱሪዝም ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊን የጠየቀች ቢሆንም፣ ሥራ ይበዛብኛል በማለታቸው ሳይሳካ ቀርቷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 207 ጥቅምት 12 2015



