በግጭትና በብልሽት መስመር ላይ የሚቆሙ ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ላይ ቅጣት የሚጥል መመሪያ ሊዘጋጅ ነው

0
870

በብልሽትና በግጭት ምክንያት መንገድ ላይ ቆመው በወቅቱ የማይነሱ ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ላይ ቅጣት የሚጥል መመሪያ እያዘጋጀ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አስታወቀ።

መንገድ ላይ ያለአግባብ የሚቆሙ ተሽከርካሪዎችን በወቅቱ ለማያነሱ ባለንብረቶች የገንዘብ ቅጣት የሚጥል መመሪያ ረቂቅ እየተዘጋጀ መሆኑን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ማኔጅመነት ኤጀንሲ የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ብርሃኑ ኩማ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በግጭትና በብልሽት ምክንያት መንገድ ላይ ያለአግባብ የሚቆሙ ተሽከርካሪዎችን እስከዛሬ ኤጀንሲው ነው የሚያነሳቸው ያሉት ብርሃኑ፤ ተሽከርካሪዎችን በወቅቱ ለማያነሱ ባለንብረቶች የመቀጮ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀቱ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል።

በብልሽትና ግጭት መስመር ላይ የቆሙ ተሽከርካሪዎችን በወቅቱ የማያነሱ ባለንብረቶች ምን መቀጣት እንዳለባቸው እስካሁን የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ፣ ተሽከርካሪውን ከማንሳት ውጪ መቅጣት የሚቻልበት ሁኔታ አልነበረም ተብሏል።

ኤጀንሲው በበጀት ዓመቱ ሩብ ዓመት በወቅቱ ያልተነሱ 325 ተሽከርካሪዎችን ማንሳቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ከ325 ተሽከርካሪዎች መካከል 60 የሚሆኑት በኤጀንሲው ወጪ በክሬን የተነሱ ናቸው ብለዋል። ቀሪዎቹ 265 ተሽከርካሪዎች ደግሞ ባለንብረቶቹ እንዲያነሱ ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው በኋላ የተነሱ ናቸው።

ተሽከርካሪዎች ከአንድ ቀን በላይ መንገድ ላይ መቆም እንደሌላባቸው መመሪያው ያዛል የሚሉት ብርሃኑ፣ በወቅቱ መነሳት ያልቻሉ በርካታ ተሽከርካሪዎች አሁንም አሉ። ይህም የትራፊክ ፍሰቱን እያስተጓጎለ ነው ሲሉ ጠቁመዋል።

ኤጀንሲው ተሽከርካሪዎችን የሚያነሳው ክሬን በመከራየት መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ምንም እንኳ በአንገብጋቢ ቦታዎች መንገድ ዘግተው የሚገኙ 365 ተሽከርካሪዎችን በሩብ ዓመቱ ቢነሱም፤ ሙሉ በሙሉ ግን ማንሳት አለመቻሉን ብርሃኑ ተናግረዋል።

ኤጀንሲው በወቅቱ የማይነሱ ተሽከርካሪዎችን የሚያነሳው ባለንብረቶች በወቅቱ ሳያነሱ ሲቀሩ እስከ አምስት ቀን ድረስ እንዲያነሱ ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኋላ መሆኑ ተመላክቷል። የተበላሹና የተጋጩ ተሽከርካሪዎች መንገድ ላይ በወቅቱ አለመነሳታቸው የትራፊክ ፍሰቱን ከማስተጓጎል ባሻገር ለአደጋ የሚዳርግ በመሆኑ ባለንብረቶች በተሽከርካሪዎች ላይ ችግር ሲገጥማቸው በፍጥነት በማንሳት እንዲተባበሩ ተቋሙ ጥሪ አቅርቧል።

በወቅቱ የማይነሱና የትራፊክ ፍሰቱን እያወኩ ነው የተባሉት ተሽከርካሪዎችም ሹፌሮች ትተዋቸው የሚሄዱ የተሳቢ ተጎታቾች፤ ጎማቸው የተበላሸ፤ የፈራረሱና እንዲሁም ግጭት ገጥሟቸው ሹፌሮች ትተዋቸው የሄዱ ተሽከርካሪዎች መሆናቸውንም ብርሃኑ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ማንኛውም መንገድ ሲገነባ ለተሽከርካሪ መመላለሻ በመሆኑ ችግር ያለባቸውን ተሽከርካሪዎች በወቅቱ ማንሳት የባለንብረቶች ግዴታ ነው ተብሏል። ብልሽት የገጠማቸው ተሽከርካሪዎች በወቅቱ መንገድ ላይ ካልተነሱ በተለይም በምሽት የሚጓዝ መኪናን ለግጭት እንደሚዳርጉና ከዚህም ባሻገር በራቸው የተበላሸ ከሆነ ለስርቆትም የመጋለጥ እድላቸው የሰፋ ነው ተብሏል።

በ2014 በጀት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 411 ሰዎች በትራፊክ አደጋ መሞታቸውንና ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ22 ሰዎች ብልጫ እንዳለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ከዚህ በፊት መግለጹ ይታወሳል።


ቅጽ 4 ቁጥር 207 ጥቅምት 12 2015

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here