ህፃን ሳሙኤል ዩሃንስን ይዘው በመሰወር 10 ሚሊዮን ብር ሲጠይቁ በነበሩ ሦስት ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ

0
1353

ረቡዕ ኀዳር 14 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ፤ ህፃን ሳሙኤል ዩሃንስ ይዘው በመሰወር 10 ሚሊዮን ብር ሲጠይቁ በነበሩ ሦስት ግለሰቦች ላይ ክስ መስርቷል።

ዐቃቤ ሕግ በፈፀሙት ከባድ ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅን መጥለፍ ወንጀል ክስ የመሰረተባቸው፤ 1ኛ መሪጌታ ምስጥሩ ይግዛው፣ 2ኛ ዘውዲቱ ገብሬ እና በ3ኛ ብሩክ ቸኮል የተባሉ ተከሰሾች ላይ ነው፡፡

የዐቃቤ ህግ ክስ እንደሚያመላክተው ኹለተኛ ተከሳሽ ዘውዲቱ ገብሬ ቀደም ብላ በቤት ሠራተኛነት ተቀጥራ ስትሰራበት በነበረበት ቤት ውስጥ እድሜው 2 ዓመት ከ11 ወር የሆነው ህጻን መኖሩን ለአንደኛ ተከሳሽ መጠቆሟ ተጠቅሷል።

በዚህ መሰረት ከህጻኑ ቤተሰቦች ብር ለመቀበል በመነጋገርና በመስማማት 2ኛ ተከሳሽ ሥራዋን ለቃ ከቆየችበት የመኖሪያ ቤት በድጋሚ ተቀጥራ እንድትገባ መደረጉ ተገልጿል፡፡

በስምምነታቸው መሰረትም ጥቅምት 6 ቀን 2015 በግምት ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚኩራ ክ/ከተማ ወረዳ 10 ክልል ልዩ ቦታው አያት ጣዕም ዳቦ ቤት እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ከሚገኘውና፤ በሠራተኝነት ተቀጥራ ከምትሰራበት የመኖሪያ ቤት ውስጥ ህጻን ሳሙኤልን ማስቲካ ልግዛለት ብላ በማታለል ይዛው ከቤት በመውጣት በወቅቱ እዛው አካባቢ ይጠብቁዋት ከነበሩ 1ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ጋር በመገናኘት ከአዲስ አበባ ውጭ ህጻኑን ጠልፈው መሰወራቸው በክስ ተመላክቷል።

በዚህ መልኩ ከተሰወሩ በኋላ 1ኛ ተከሳሽ ለህጻኑ አባት ስልክ በመደወል ህጻኑ ከእነሱ ጋር እንዳለ እና 10 ሚሊዮን ብር ካላመጡ እንደሚሸጡት በመግለጽና በማስፈራራት ሲደራደሩ እንደነበረም ተገልጿል።

ሦስተኛ ተከሳሽም በተመሳሳይ ስልክ በመደወል “ብሩን ቶሎ ካልከፈላችሁ ህጻኑን ወደ መተማ ሊወሰዱት ነው” በማለት ገንዘቡን አስፈራርተው ለመቀበል ሲደራደሩ ቀናት ማስቆጠራቸው ተመላክቷል።

ተከሳሾች ህጻን ሳሙኤልን በተቀናጀ አካሄድ ይዘውት መሰወራቸውን ተከትሎም፤ የፌዴራል ፖሊስ፣ የክልል ፖሊስ እና የደህንነት መስርያ ቤት ከፍተኛ ኦፕሬሽን በማካሔዳቸው፤ ጥቅምት 16 ቀን 2015 1ኛ ተከሳሽ በፖሊስ ከተያዘ በኋላ፣ የግል ተበዳይ ጨምሮ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች በኦሮሚያ ክልል ኢጅሬ ወረዳ አዲስ አለም ከተማ ጨረቃ ሠፈር በሚገኝው 1ኛ ተከሳሽ ተከራይቶት በነበረው ቤት ውስጥ በፖሊስ እጅ ከፍንጅ መያዛቸው ተገልጿል፡፡

ህፃን ሳሙኤል ዩሃንስም ከቤተሰቦቹ ጋር እንዲገናኝ ማድረግ መቻሉም ተነግሯል።

በዚህም፤ ጉዳዩ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የልዩ ልዩ ወንጀል ችሎት ተከሳሾቹ ከጠበቃ ጋር ተማክረው የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ለህዳር 20 ቀን/2015 ቀጠሮ መሰጠቱን ፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here