በቻይናዊያን አሽከርካሪዎች ተይዞ የሚገኘውን የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር በኢትዮጵያዊያን ለመተካት ለአሽከርካሪዎች ስልጣና መሰጠት ጀመረ። 45 አባላት ያሉት የሰልጣኞች ቡድን የንድፈ ሃሳብ ስልጠናውን በኢትዮጵያ በማከናወን ቀጣይ ለተግባር ልምምድ ወደ ቻይና እንደሚያመሩ ተገልጿል። ቻይናው የግንባታ ኩባንያ ሲሲኢሲሲ የሚያስተዳድረው የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር በአጭር ጊዜ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያዊያን እና በጅቡቲያዊያን አሽከርካሪዎች መተካት እንደሚኖርበትም በኢትዮጵያ የቻይና ኢምባሲ የንግድ አማካሪ ሊ ዮ አስታውቀዋል።
አማካሪዋ አያይዘውም ከዚህ ቀደም 46 የሚሆኑ ሰልጣኞች መሰረታዊ ባቡር ማሽከርከር ክህሎትን የተሰለጠኑ መሆናቸውን አውስተው አሁኑ ዙር ሰልጣኞችም በተሻለ ስልጠና ራሳቸውን አብቅተው የኢትዮጵያዊያንን የባቡር አሽከርካሪዎች ቁጥር ከፍ እንዲያደርጉ አስታውቀዋል። ሲሲኢሲሲ በኢትዮ-ጅቡቲ መድር ባቡር ፕሮጀክት ለ3000 ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን የስራ ዕድል መፍጠር እንደቻለም ታውቋል።
ሲሲኢሲሲ በዕውቀት ሽግግር ረገድ በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ለአዲስ ማለዳ የገለፁት የስልጠናው አስተባባሪ፤ ብቃት ያላቸው ቻይናዊያ አሰልጣኞችን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት የንድፈ ሃሳብ ስልጠና የሚሰጡበትን መንገድ ማመቻቸቱን አስታውቀዋል።
ቻይና ለኢትዮጵያዊያን የምትሰጠውን የትምህርት እድል አጠናክራ እንደምትቀጥል ቃል ገቡት አማካሪዋ፤ እስከ ጥቅምት ወር መጨረሻ ድረስም በቻይና 8 ሽህ 300 ኢትዮጵያዊያን በቻይና በተለያዩ ዘርፎች የትምህርት ዕድል አግኝተው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።
በቀጣዩ ዓመት ኢትዮጵያ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 50ኛ ዓመት የሚያከብሩ ሲሆን የኹለትዮሽ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ጨምሮ በርካታ አመርቂ ስራዎች መሰራታቸውንም አማካሪዋ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።



