ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔ እንዲያከናውን ተጠየቀ

0
623

የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት የሲዳማ ብሔር ራሱን ችሎ ክልል ለመሆን ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የወሰነው ውሳኔ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔ እንዲያከናውን ተጠየቀ።
የክልሉ ምክር ቤት ጥቅምት 23/2011 ባደረገው 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤ የሲዳማ ዞን ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ የወሰነበትን ክልል የመሆን ጥያቄ ተቀብሎ የአፈፃፀም አቅጣጫ መስጠቱ ይታወቃል። በዚም መሠረት የሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ምክር ቤቱ በዚህ ሳምንት ምርጫ ቦርድን መጠየቁን የሲዳማ ዞን ምክር ቤት ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አብረሃም ምትኩ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት መሠረት ክልል የመሆን ጥያቄው በብሔሩ ሕዝበ ውሳኔ በአብላጫ ድምፅ ካለፈ የክልሉ ምክር ቤት አዲስ ለሚመሠርተው የሲዳማ ክልል ሥልጣኑን የሚያስረክብ ይሆናል።
በተመሳሳይ የተለያዩ የደብብ ክልል ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ብሔሮች ክልል የመሆን ጥያቄን ለዞን ምክር ቤት አቅርበው ማስወሰናቸው ይታወሳል።
የካፋ ዞን ምክር ቤት ኅዳር 6 የብሔረሰቡን የክልልነት ጥያቄ በሙሉ ድምፅ ያፀደቀ ሲሆን የወላይታ ዞን በክልል የመደራጀት ጥያቄ ላይ የዞኑ ምክር ቤት ውይይት አድርጎ የጥያቄውን አግባብነት ከተቀበለ በኋላ በጉዳዩ ላይ ኅብረተሰብ እንዲወያይበት በሚል ለዞኑ መስተዳደር ምክር ቤት (ካቢኔ) መምራቱም ይታወሳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here