የወረታ ወደብና ተርሚናል የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ተጠናቀቀ

0
1276

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በደቡብ ጎንደር በወረታ ከተማ በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት እየተገነባ  የሚገኘው የወረታ ወደብና ተርሚናል የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ተጠናቀቀ ።

በኹለት ምዕራፍ ግንባታው የሚካሄደው ይህ ወደብና ተርሚናል በመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ 3 ሔክታር የለማ ሲሆን የመጋዘን፣ የቢሮዎች፣የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ቢሮ የመጸዳጃ ቤት ስራ እና የውሃ መስመር ዝርጋታ ስራ የተጠናቀቀ መሆኑን የወደብ እና ፋሲሊቲ ልማት መምሪያ የኢንጂነሪንግ አገልግሎት ዋና ክፍል ኃላፊ ኢንጂነር ሳሙኤል ሙሴ ተናግረዋል።

በአማራ መንገድ ስራዎች ድርጅት የወረታ ወደብና ተርሚናል የግንባታ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ኪሩቤል ሀሳብነህ በበኩላቸው ለግንባታው የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እጥረት በመፈጠሩ እና የክረምቱ ወራት ቀድሞ በመግባቱ እና የወሰን ማስከበር ችግር አለመፈታት እንዲሁም ተነሺዎች ተገቢው ካሳ ቢከፈላቸውም ከቦታው ላይ በጊዜ ባለመነሳታቸው የ2 ኪሎሜትር የአጥር ስራ ለመስራት በለመቻላቸዉ ምክንያት ግንባታው በታቀደለት ጌዜ መጠናቀቅ አለመቻሉን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የግንባታ ስራው ከ75 በመቶ በላይ መድረሱንና በህዳር ወር መጨረሻ ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃልም ብለዋል።

ወደቡ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ከ900 TEU ኮንቴነር በላይ የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረው የኢባትሎአድ የየብስ ወደቦች ኦፕሬሽን ማስተባበሪያ መምሪያ ዋና ክፍል ኃላፊ  ብሩክ ባዛ ተናግረዋል።

በቀጣይም ኹለተኛው የግንባታ ምዕራፍ ስራ በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚጀመር በወደብ እና ፋሲሊቲ ልማት መምሪያ የኢንጂነሪንግ አገልግሎት ዋና ክፍል ኃላፊ ኢንጂነር ሳሙኤል ሙሴ ገልጸዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here