ኤሌክትሪክ ኃይል ሩብ ትሪሊየን ብር ዕዳውን መክፈል አቅቶታል

0
883

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል 216 ቢሊየን ብር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኮርፖሬት ቦንድ መልኩ መበደሩንና መክፈል የሚችልበት አቋም ላይ እንደማይገኝ አዲስ ማለዳ ከተለያዩ ምንጮች አረጋገጠች። ድርጅቱ ከውጭ አበዳሪዎች ከወሰደው ብድር ጋር ሲደመር ቁጥሩ ከሩብ ትሪሊዮን ብር ሲያልፍ የአገሪቱን 75 በመቶ በጀት ያክላል። በአገሪቷ ከሚገኙ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች በሀብት አቋሙ የመጀመሪያ ደረጃ የያዘው ኤሌክትሪክ ኃይል ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ቦታዎች ግድቦችና ሰብስቴሽኖችን እንዲሁም ሌሎች ግንባታዎችን ለማካሔድ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያፈሰሰ ቢሆንም፤ ፕሮጀክቶቹ በተያዘው ዕቅድ መሠረት ባለመጠናቀቃቸው እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ገቢ ማስገኘት አለመቻላቸው ለድርጅቱ የብድር የመክፈል አቅም መመንመን ዋነኛ ምክንያት ናቸው።
ብድሩ በአገሪቷ ካሉ ሌሎች ኢንተርፕራይዞች ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛው ሲሆን አዲስ ማለዳ ከብሔራዊ ባንክ ያገኘችው መረጃ እንደሚያሳየው ከባለፈው ዓመት አንፃር የ37 ቢሊየን (21 በመቶ) ጭማሪ አሳይቷል። በዚህ ወር መጀመሪያ አካባቢ በድርጅቱ የኦዲት ሠራተኞች በተደረገ ግምገማ ኢንተርፕራይዙ ዕዳውን ሊከፍል ቀርቶ፥ አሁን ባለው ቁመና የወለድ ክፍያውን መፈፀም አልቻለም ሲሉ ለፕሮጀክቱ ፋይናንስ ቢሮ ቅርበት ያላቸው ባለሙያ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ኢንተርፕራይዙ ከ2007 አንስቶ በገለልተኛ ድርጅት ኦዲት ያልተደረገ ቢሆንም፤ በመንግሥትና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በብድር አኳያ ያለው ተአማኒነት ሊወርድ አልቻለም። በዚህም የተነሳ እንደ ባቡር ኮርፖሬሽን ያሉ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የመክፈል አቅም ያነሰ መሆን ጋር ተያይዞ ብድር አያገኙም፤ ስለዚህም ለእነዚህ ተቋማት በሥሙ መበደሩን የሚገልጽ ማሰረጃ በሚገባ እንዳለ የኤሌክትሪክ ኃይል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ሞገስ መኮንን አስረድተዋል። “የዕዳችንን ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ገንዘብ የተበደርነው ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ለሚገነባቸው የባቡር ፕሮጀክቶች የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማትና ሌሎች ግንባታዎች ለማካሔድ መሆኑን” ኃላፊው አስረድተዋል።
ኤሌክትሪክ ኃይል ከተለያዩ የውጭ ተቋማት ከአራት እስከ ዘጠኝ በመቶ በሚደርስ ወለድ ወደ 45.3 ቢሊየን ብር የተበደረ ሲሆን ባለፉት ሦስት ዓመታት ምንም ዓይነት ክፍያ ለአገር ውስጥ አበዳሪው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አልፈፀመም። በዚህም የተነሳ ከባለፈው ዓመት አንፃር በአራት ቢሊየን ትርፉ የቀነሰው ንግድ ባንክ ከድርጅቱ መቀበል የነበረበትን ከዐሥር ቢሊዮን ብር በላይ የሆነ ገንዘብ ማግኘት አልቻለም።
ባለፈው በጀት ዓመት ወደ 2.7 ቢሊዮን ብር ገቢ ከተለያዩ ምንጮች የሰበሰበው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ በዓመት ወደ 58.5 ቢሊዮን አካባቢ ወጪ ያወጣል። ይህም ድርጅቱ በዓመት ወደ 56 ቢሊዮን ብር አካባቢ ይከስራል ማለት ነው። የድርጅቱ ገቢ መሸፈን የሚችለው የአስተዳደርና የምርት 90 በመቶ ወጪ ብቻ ነው። ስለዚህም የተለያዩ ግንባታዎችን የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማሟላት ብቸኛ ምርጫ የሆነው ብድር ብቻ ሆኗል።
የድርጅቱ የሥራ ድርሻ ኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፍና የኃይል ማመንጫ መገንባት መሆኑን ያስታወሱት ሞገስ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ከመንገባታቸው በፊት የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ቀድመው አለመታሰባቸው ድርጅታቸው የሁሉን ተቋማት ብድር ጫና ተሸካሚ ማድረጉን ይገልጻሉ። እንደ ምሳሌ በባቡር ኮርፖሬሽን የተገነቡት ባቡሮችን ይጠቅሳሉ።
ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የዕዳ ወለድ ክፍያ ወደ 16 ቢሊየን ብር የደረሰ ሲሆን፣ በዋጋ ግሽበትም ምክንያት እንደ ሕዳሴና ሌሎች በመገንባት ያሉ ግድቦችን መዘግየት ምክንያት ወጪያቸው አንዳንዶች መጀመሪያ ከተገመተው ከእጥፍ በላይ እንደደረሱ መረጃዎች ያመለክታሉ። የፋይናንስና ኦዲት ባለሙያ በመሆን ወደ 16 ዓመት ልምድ ያካበቱት አብዱልመናን መሐመድ እንደገለጹት የኤሌክትሪክ ኃይል ገቢው ወጪውን ሙሉ ለሙሉ እንዲሸፍን አሁን የሚያገኘው ዓመታዊ ገቢ በዐሥር ዕጥፍ በላይ ማደረግ አለበት።
በሌላ በኩል ኤሌክትሪክ ኃይል የገዛው ቦንድ በ7 ዓመታት መመለስ ያለበት በመሆኑ፣ ድርጅቱ ያለውን ሀብት ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልበት ጊዜና የብድር መክፈያው ጊዜ አለመመጣጠንና የድርጅቱን ጠቅላላ ሀብት ከእዳው ሊያሳንስ እንደሚችል ተገልጿል። ይህንን በመረዳት፣ ድርጅቱ ያለበትን የገንዘብ እጥረትም ለመፍታት አቅጣጫ ተቀምጧል። አንዱ የድርጅቱን የገቢ ምንጮች ማስፋት ሲሆን እንደ ምሳሌ የተገለጸው ባለፈው ሳምንት ኢትዮ ቴሌኮም በነጻ ለሰባት ዓመታት ሲጠቀምበት የነበረውን ኦፕቲካል ግራውንድ በዓመት 20 ሚሊየን ብር ሊከፍል መስማማቱን ነው።
ከዚህም በተጨማሪ በድርጅቱ ከለላ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ብር የተበደሩት እንደ ባቡር ኮርፖሬሽንና ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያሉ ተቋማት ራሳቸው እንዲከፍሉ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ሞገስ አስረድተዋል። በኢትዮጵያ ብዙዎች የመንግሥት ልማት ድርጅቶች በዕዳ የተዘፈቁ ሲሆን እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድና ብርሃንና ሠላም ያሉ ድርጅቶች በስተቀር ሌሎቹ የመክፈል አቅማቸው ዝቅተኛ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
በተለይ ባቡር ኮርፖሬሽን በአሁኑ ሰዓት ኤሌክትሪክ ኃይል አለበት ከሚለው በተጨማሪ 29.2 ቢሊየን ብር ከንግድ ባንክ ወስዷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያሉትን ቋሚ ንብረቶች ለማወቅ የሚያስችል የሀብት ቆጠራ ጥናት ሊያካሒድ መሆኑ ታውቋል። ድርጅቱ ባለፈው ሐሙስ፣ ኅዳር 20 ፌር ፋክስ ከተሰኘ ዓለም ዐቀፍ ድርጅት ጋር ተፈራርሟል። ሥምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አብረሃም በላይ (ዶ/ር) እና የፌር ፋክስ ዓለም አቀፍ ሊቀ መንበር ዘመዴነህ ንጋቱ ተፈራርመዋል፤ ጥናቱንም ከ8 እስከ 12 ወራት ውስጥ አጠናቆ ለማስረከብ ተስማማተዋል።

 

ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here