የ16 ቀኑ “እኔንም ስሙኝ” ዘመቻ ለ366 ቀናት ይዝለቅ!

0
847

የሴቶችን ጥቃት በመቃወም ከእሁድ፣ ኅዳር 16 እስከ ታኅሣሥ 1/ 2011 ለ16 ቀናት “እኔንም ስሙኝ” በሚል መፈክር ዓለም ዐቀፍ ዘመቻ እየተካሔደ ይገኛል፡፡ የዘመቻው ዓላማ የፆታዊ ጥቃት ተጠቂዎች ታሪካቸውን እንዲናገሩ መድረክ ማመቻቸት እና ማበረታታት ነው፡፡
ተባእታዊ ማኅበራዊ ስርዓት እና ፆታዊ ትንኮሳ በዓለማችን ያሉ ሴቶችን ሕይወት ከሚያከብዱባቸው ነገሮች ዋነኞቹ ናቸው። ተባእታዊ ማኅበራዊ ስርዓት በማኅበረሰብ ውስጥ ወንዶች እና ሴቶች መካከል ያለው የኃይል ግንኙነት ወይም የተዛባ ሚዛን የሚገለጽበት ማኅበራዊ መዋቅር ነው። ይህ ስርዓት ወንዶች ሴቶችን በባሕል፣ በማኅበራዊ ጉዳዮች፣ በምጣኔ ሀብት እና በፖለቲካ ጉዳዮች ተቋማዊ በሆነ መልኩ የወንዶች ጥገኛ እና ተጨቋኝ አንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ በተለያዩ ማኅበረሰቦች ዓይነቱና መገለጫዎቹ በጥቂቱ ይለያይ እንጂ የሴቶች የፆታ ጥቃት ወይንም ትንኮሳ በገጠርም ይሁን በከተማ፣ በተማረውም ይሁን ባልተማረው፣ በሠለጠነውና ባልሠለጠነው፣ ወዘተ… የማኅበረሰብ ክፍል ውስጥ የፆታዊ ጥቃት ወይም ትንኮሳ ተንሰራፍቶ ይገኛል፡፡ ተባእታዊው ማኅበራዊ ስርዓት የተዛባ የኃይል ግንኙነት ከመፍጠሩም ባሻገር፣ ሴቶች መብቶቻቻውን ለማስከበር እና የተዛባውን የኃይል ሚዛን ለማስተካከል የሚያደርጉትን ከፍተኛ ጥረት በማጣጣል እና በማንኳሰስ ስርዓተ ተዋረዱ እንዲቀጥል እያደረገ ነው፡፡
ፆታዊ ጥቃት ስንል ፆታን መሠረት ያደረገ፣ በተለይ ሴቶችን ሴት በመሆናቸው ብቻ ተጎጂ የሚያደርግ የቃል፣ የምልክት፣ የአካል እንዲሁም ወሲባዊ ትንኮሳን እና ጥቃትን የሚያካትት፣ በቤት ውስጥ ባሉ ወዳጅ ዘመዶች፣ በመንገድ ላይ በሚገጥሙ የማይታወቁ ሰዎች፣ በመሥሪያ ቤት፣ በሥራ ቦታ ወይም በበይነመረብ ላይ የሚፈፀም፣ ከሥነ ልቦናዊ ጫና እስከ አካላዊ ጉዳት፣ አስገድዶ መድፈር እና ነፍስ ማጥፋት የሚዘልቅ ጥቃት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ምንም እንኳን የዓለም ዐቀፉን ሴቶች ፀረ-ፆታዊ ትንኮሳ አስወጋጅ ሥምምነትን የተቀበለች ቢሆንም ግዴታዎቿን ግን በሚፈለገው መጠን እየተወጣች አይደለም፡፡ ለሴቶች መብቶች የሚሟገቱ ድርጅቶች ከፍተኛ ትግል በማድረግ አንፃራዊ የሆነ ተፅዕኖ በመፍጠራቸው የቀድሞው ወንጀል ሕግ እያደገ የመጣውን የሴቶች ጥያቄዎችን በተወሰነ መልኩ እንዲያስተናግድ መደረጉ የሚያስመሰግናቸው ቢሆንም ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ዓለም ዐቀፍ ድንጋጌዎች በሚገባ ተፈፃሚ እያደረገች አይደለም፡፡
የፆታ ትንኮሳ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃቶችን ያካትታል፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ሴቶች የፆታ ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ እንኳን ለመናገር ይፈራሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በቂ የሕግ ከለላ ካለመኖሩም በላይ በማኅበረሰቡ ዘንድ ተጠቂዋን መልሶ የመውቀስ እና የማሸማቀቅ ልማድ ስለተንሰራፋ ነው፡፡
በአገራችን ያሉ ፆታዊ ጥቃቶች ከግርዛት ጀምሮ ያላቻ ጋብቻ፣ የጠለፋ፣ የቤት ውስጥ ጥቃት እና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡ በሕግ ደረጃ ብዙዎቹን ጥቃቶች ለመከላከል የሚያስችል መዋቅር ቢኖርም ቅሉ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለው የተዛባ አመለካከት ተፈፃሚ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡
ፆታዊ ጥቃቶችን እና የወሲብ ትንኮሳን ለመቀነስ ብሎም ለማጥፋት በአጠቃላይ በማኅበረተሰቡ ላይ ከፍተኛ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መሠራት ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪ ፆታዊ ትንኮሳ የሚደርስባቸው ሴቶች ነጻ ወይም ርካሽ የሕግ ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ፣ የፍትሕ አስፈፃሚ አካላት በጉዳዩ ዙሪያ የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጡ በማድረግ፣ በጉዳዩ ላይ የሚሠሩ ሲቪል ማኅበራትን በማበረታታት እና መንግሥታዊ የፖለቲካ ቁርጠኝነት በጉዳዩ ላይ በማድረግ ተፈላጊውን ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ ይቻላልም፣ ይገባልም፡፡
ፆታዊ ጥቃት እና የወሲብ ትንኮሳ እንዲቀንስ ለማድረግ ብሎም ለማጥፋት በቤት ውስጥ፣ በትምህርት ቤቶች ውስጥ፣ በሥራ ቦታ እና በሌሎችም አካባቢዎች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያሻል፡፡ መገናኛ ብዙኃንም ፆታዊ ጥቃት እንዲቀንስ የራሳቸውን ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል፡፡
የብዙኃን መገናኛ ትኩረት አስፈላጊ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ አዲስ ማለዳ በዚህ ሦስተኛ እትሟ ላይ የወሲብ ጥቃትን የተለየ ትኩረት በመስጠት የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይዋ አድርጋ አቅርባዋለች፡፡
ይሁን እንጂ አዲስ ማለዳ፣ የሴቶችን መብቶች ለማስከበር ለሚደረገው ዘመቻ ዘላቂ አስተዋፅዖ ለማበርከት ሲባል “ሲቄ” የተሰኘች ቋሚ አምድም ሰይማለች፡፡ በአምድዋ፣ ሴቶች የዕለት ተዕለት የፆታዊ መድልዖ ገጠመኛቸውን እና ጎታች እንቅፋት የሚሆንባቸውን የተዛባ ማኅበራዊ ግንኙነት እንዲተቹባት ክፍት ትሆናለች፡፡
በተመሳሳይ ሌሎችም ተቋማት የፆታ ጥቃትን ለመግታት እና በወንዶች እና በሴቶች መካከል የተዛባውን የኃይል ሚዛን ለማረም የሚያስችላቸውን ሥራ በአጭር ቀናት ዘመቻ ሳይሆን፣ በዘላቂነት መሥራት የሚያስችላቸውን መርሐ ግብር በማፅደቅ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ እያቀረበች፤ ሴቶች የማይጠቁበት፣ ከተጠቁም እነርሱ ሳይሆኑ የድርጊቱ ፈፃሚዎች የሚያፍሩበት፣ የሚሸማቀቁበት እና የእርምት ቅጣት የሚያገኙበት ስርዓት እስኪመጣ ዘመቻው ከዓመት ዓመት ይዝለቅ!

 

ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here