የፈረሱ ተቋማት ሠራተኞች አለመመደብ ቅሬታ አስነሳ

0
579

በአዲሱ የአስፈጻሚ ተቋማት አደረጃጀት በፈረሱ ተቋማት ውስጥ ከነበሩ ሠራተኞች መካከል እስካሁን ያልተመደቡ መኖራቸው ቅሬታ አስነሳ። የሠራተኞች ምደባ እስከመቼ ይጠናቀቃል ለሚለው የተቆረጠ ጊዜ ማስቀመጥ እንደማይቻል ሲቪል ሰርቪሰ ኮሚሽን ገልጿል።
ከፈረሱት ተቋማት መካከል ከ180 እስከ 200 ሠራተኞች ያሉት የሆርቲካልቸርና ግብርና ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን አንዱ ሲሆን፣ ሠራተኞቹ እስካሁን ባለመመደባቸው ቅሬታ ውስጥ ገብተዋል። ሠራተኞቹ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት እስካሁን ወዴት እንደሚሄዱ በግለጽ የተነገራቸው ነገር የለም። ባለሥልጣኑ ሲፈርስ የሆርቲካልቸር ዘርፉ ሥልጣንና ተግባር ወደ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የግብርናው ዘርፍ ደግሞ ወደ ግብርና ሚኒስቴር እንዲጠቃለል መወሰኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥቅምት 6/2011 ባጸደቀው የሥራ አስፈጻሚ መልሶ ማደራጃ አዋጅ ተመልክቷል።
በወቅቱ ስለፈረሱ ተቋማት ሠራተኞች ዕጣ ፈንታ የተጠየቁት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ሠራተኞቹ የነበሩበት የሥራ ዘርፍ ወደሄደበት ተቋም እንደሚሄዱ ተናግረው ነበር። ጠቅላይ ሚንስተሩ ተቋማት አደረጃጀትና የሠራተኛ ምደባቸውን ፈጥነው በማጠናቀቅ ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲገቡ ማሳሰባቸውም ይታወሳል። በዚህ መሠረት ሠራተኞቻቸውን ያከፋፈሉ ተቋማት ቢኖሩም እስካሁን ዕጣ ፈንታቸውን ያላወቁት የቀድሞው የሆርቲካልቸርና ግብርና ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን ሠራኞች ግን ግራ እንደተጋቡ ተናግረዋል።
ሠራተኞቹ እንደሚሉት ኮሚቴ ተዋቅሮ የሠራተኞቹን ቀጣይ ማረፊያ እየፈለጉ ይሁን እንጂ እስካሁን ስለደረሱበት ነገር ለሠራተኞቹ ያሳወቁት ነገር ባለመኖሩ በተባራሪ ወሬ እየተረበሹ ነው። ዘጠኝ የኮሚቴ አባላት ቢኖሩም ሠራተኛውን ሰብስበው እየሄዱበት ያለውንና ያገኙትን ውጤት በመደበኛ መንገድ ባለመንገራቸው፣ መደበኛ ባለሆነ መንገድ ከእያንዳንዱ ኮሚቴ አባል የተለያየ መረጃ እየተሰጣቸው መደናገራቸውን አሳውቀዋል። ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ግብርና ሚኒስቴር አደረጃጀት እያጠኑ መሆኑን ቢስማሙም ተቋማቱ የባለሥልጣኑን ሙሉ ሠራተኞች ለመቀበል ፍላጎት አለማሳየታቸውን መስማታቸውን በመጥቀስ ሥጋት እንዳደረባቸው ገልጸዋል።
መንግሥት ተቋማትን እንደአዲስ ያደራጀው የሰው ኃይሉን ለመጠቀምና ወጪ ለመቆጠብ ይሁን እንጂ ከጥቅምት 6/2011 ጀምሮ የፈረሰው ባለሥልጣን ሠራተኞች እስካሁን ደመወዝ እየተከፈላቸው ያለሥራ መቀመጣቸውን ጠቅሰዋል። አብዛኛው ሠራተኛ ቢሮ እንደማይውልም አዲስ ማለዳ ባደረገችው ቅኝት አረጋግጣለች። ቢሮ ውስጥ ያገኘናቸው ሠራተኞች እንደሚሉት ሥራ ባለመኖሩና ለምን ወደቢሮም እንደሚመጡ ስለማይገባቸው አብዛኞቹ እንደሚቀሩ ጠቁመዋል።
ባለሥልጣኑ ግሎባል ሆቴል አካባቢ ለተከራየው ሕንጻ በዓመት እስከ 13 ሚሊዮን ብር እንደሚከፍል አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ ሰምታለች። የባለሥልጣኑ ሠራተኞች ፈጥነው አለመመደብም የፈረሰው ባለስልጣን ያለሥራ ለያዘው ቢሮ በየወሩ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ እየከፈለ ሁለተኛ ወሩን በማገባደድ ላይ ይገኛል።
ያነጋገርናቸው የኮሚቴ አባላት እንደሚሉት መረጃን ለሠራተኛው ቶሎ ተብሎ ማድረስ የሚገባ ቢሆንም፣ በኮሚቴው በኩል ውጤቱ ይታወቅና የተደራጀ መረጃ እንስጥ የሚል መግባባት ላይ መደረሱ ሠራተኞቹ ምን እየተካሄደ እንደሆነ ባለማወቃቸው ቅሬታ ፈጥሯል። በግብርና ሚኒስቴርም ይሁን በኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኩል እየተሠሩ ያሉ አደረጃጀቶች ላይ የቀድሞው ባለሥልጣን ሠራተኞች ሙሉ በሙሉ ይካተቱ አይካተቱ ኮሚቴው በግልጽ የሚያውቀው ነገር እንደሌለም ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን የኮሚቴ አባላት ነግረውናል። መሥሪያ ቤቶቹም አደረጃጀቱን የሚያጠኑት ቀድሞ ከነበራቸው ሠራተኛ በተውጣጣ ቡድን እንጂ ከባለስልጣኑ ሰዎች እንዲወከሉ አለመፍቀዳቸውን ጠቁመዋል።
በሁለቱም ተቀባይ መሥሪያ ቤቶች በኩል ሁሉንም ሠራተኛ ተቀብሎ ለመመደብ ፍላጎት አለመኖሩን እንደተረዱ የጠቆሙን የኮሚቴው አባላት፣ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እስካሁን ኮሚቴው ሲጠይቀው መቀበል አለባቸው ከሚል ምላሽ ባሻገር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላለፈ ውሳኔን ለማስፈጸም እንደሠራተኛ አስተዳዳሪነቱ እምብዛም ትኩረት ሰጥቶ አልተንቀሳቀሰም በሚል ይወቅሳሉ። የፈረሰው ተቋም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወደሌላ ተቋም ኃላፊነት መዛወራቸውም ሠራተኞቹን ወክሎ በፍጥነት የሚያስፈጽምላቸውን ሰው እንዳሳጣቸው ተነስቷል።
የኮሚቴው ጸሐፊ ካሳሁን መንጅግስ ለሠራኞቹ መረጃ አልደረሰም በሚለው እንደማይስማሙ በመጥቀስ፣ ኮሚቴው በተቀባይ ተቋማት በኩል ውስን ሠራተኞች ለመቀበል የነበረውን አቋም ከኮሚሽኑ ጋር በመሆን አሳምኖ በሁለቱም ተቋማት በኩል ሠራኞችን ለመመደብ አደረጃጀቱ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል። ይህንንም በመጪው ሰኞ እንደሚገመግሙ አክለዋል።
ምደባውና የቢሮ እቃዎች ክፍፍሉ እስከ ኅዳር 30/2011 እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ዕቅድ መውጣቱንም ካሳሁን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ከሁለቱ ተቋማት ውጭ የሚሆኑ ሠራተኞች ካሉ ሲቪል ሰርቪስ እንደሚመድባቸው ለኮሚቴው አሳውቋልም ብለዋል።
የማይመደብ ሰራተኛ አይኖርም ያለው የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ተቋማት አደረጃጀታቸውን እያጠኑ በማቅረብ ላይ በመሆናቸው ምደባውም አብሮ እየተካሄደ ስለመሆኑ አንስቷል። በኮሚሽኑ የኮሙዩኒኬሽን ተወካይ ዳይሬክተር አለባቸው አለሙ የሰራተኞች ምደባ ፍጥነቱን የሚወስነው ተቋማት አደረጃጀታቸውን እያጠኑ የሚቀርቡበት ጊዜ ነው ብለዋል። ሰራተኛ ያለስራ እንዳይቀመጥ ያለው መፍትሔ አደረጃጀቶችን ቶሎ እየጨረሱ ለኮሚሽኑ ማጸደቅ ነውም ተብሏል። የሰራተኛው ምደባ እስከመቼ ይጠናቀቃል ለሚለው ግን የተቆረጠ ጊዜ ማስቀመጥ እንደማይቻል ገልጸዋል።

 

ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here