ማክሰኞ ነሐሴ 16 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የአማራ ክልል ምክር ቤት በባህር ዳር ከተማ በሚገኘው የክልሉ ምክር ቤት አዳራሽ በመጪው አርብ ነሐሴ 19/2015 የሚካሄድ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል።
በዚህ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ለክልሉ ምክር ቤት አባላት ጥሪ የተላለፈው ትላንት ሰኞ ረፋድ መሆኑን ኹለት የምክር ቤቱ አባላት ነግረውኛል ሲል “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘግቧል።
የክልሉ ምክር ቤት አባላት ስብሰባው ከሚካሄድበት ዕለት አንድ ቀን በፊት በምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ተገኝተው ሪፖርት እንዲያደርጉ ቢነገራቸውም፤ የስብሰባው አጀንዳ እንዳልተገለጸላቸው አመልክተዋል።
ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የክልሉ ምክር ቤት አባል፤ “አስቸኳይ ስብሰባ ስለሆነ አጀንዳውን መናገር አልፈለጉም” ያሉ ሲሆን፤ ሆኖም “ወቅታዊ የክልሉ ጉዳዮች” የስብሰባው አጀንዳ ሊሆኑ እንደሚችሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
በአርቡ የአማራ ክልል ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ “በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ” ይደረጋል ተብሎ ከሚጠበቀው ውይይት በተጨማሪ፤ “ሹመት ሊኖር ይችላል” ሲሉ አንድ የምክር ቤት አባል የተናገሩ ሲሆን፤ ሌላ የክልሉ የምክር ቤት አባልም “በአንዳንድ አመራሮች ላይ ሹም ሽር የመደረግ ዕድል አለ” ሲሉ ግምታቸውን ማስቀመጣቸውንም ዘገባው አመላክቷል።



