በእስራኤል የአራት ዓመት ኢትዮጵያዊ ሕጻንን ተገጭቶ መገደሉን ተከትሎ ተቃዋሚዎች መንገድ ዘጉ

0
516

ማክሰኞ ነሐሴ 16 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በእስራኤል ከሦስት ወራት በፊት አንድ ሹፌር የአራት ዓመት ኢትዮጵያዊ ሕጻንን ገጭቶ በመገደል ማምለጡን ተከትሎ፤ “የአገሪቷ የመንግሥት ባለስልጣናት በሹፌሩ ላይ ክስ ለመመስረት ፈቃደኛ አልሆኑም” ያሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተቃዋሚዎች በትናንትናው ዕለት በቴላቪቭ ከተማ የሚገኘውን አያሎን አውራ ጎዳና በመዝጋት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

ተቃዋሚዎቹ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት ሲሆኑ፤ “ጉዳዩን ትኩረት ያልሰጡት የተገደለው ሕጻን ኢትዮጵያዊ ስለሆነ ነው” ሲሉ፤ የአገሪቱን ባለስልጣናት በዘረኝነት መወንጀላቸውን እየሩሳሌም ፖስት ዘግቧል።

ከሦስት ወራት ከ15 ቀናት በፊት የአራት ዓመቱ ራፋኤል አዳነ በእስራኤል ሰሜናዊ ማዕከላዊ አውራጃ ኔታኒያ ከተማ በመኪና ተገጭቶ ሕይወቱ ያለፈ ሲሆን፤ አሽከርካሪዋም ጉዳቱን ካደረሰች በኋላ ከአካባቢው መሰወሯ ተነግሯል፡፡

በማግስቱ ጠዋት ፖሊስ “በአደጋው እጃቸው አለበት” ብሎ የጠረጠራቸውን ዶ/ር ሃይዲ ፌስለርን እና እናቷን ኤማ ካሮልን በቁጥጥር ሥር አውሏል።

በዚህም ፖሊስ ምርመራ ካደረገ በኋላ “አሽከርካሪዋን በሕጻን ራፋኤል ግድያ ወንጀል ላለመከሰስ” መወሰኑን የገለጸ ሲሆን፤ በምትኩ በቸልተኝነት ማሽከርከር በሚል ቀላል ወንጀል ግለሰቧን ከሷታል።

ይህም ውሳኔ በሕጻኑ ቤተሰብ እና በኢትዮጵያ ማህበረሰብ ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል።ቤተሰቡን ወክሎ በፍርድ ቤት ክርክር ሲያደርግ የቆየው ጠበቃ ሮኒ አሎኒ ሲዶቭኒክ፤ “ሹፌሯን በነፍስ ግድያ እንደማይከሷት በዓቃቤ ሕግ ተነግሮናል፡፡ ነገር ግን ምናልባት በቸልተኝነት ክስ ይመሰረትባት ይሆናል፤ ይህን ግን እርግጠኛ አይደለንም፡፡ ምክንያቱም እሷ እንደገጨችው የሚያሳይ ምንም አይነት ማስረጃ ስለሌለ፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በፖሊስ በኩል የምርመራ ሂደቱን የመሸፋፈን ጥረት መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፤ በዚህም ሕጻን ራፋኤል ከአደጋው ከዘጠኝ ቀናት በኋላ ሕይወቱ ያለፈ ቢሆንም፤ አደጋው ከደረሰ ከአንድ ቀን በኋላ ሕጻኑ መሞቱን የሚገልጽ ጽሁፍ መታተሙን የሕጻኑ ቤተሰቦች ተናግረዋል።

በተጨማሪም በአንድ ወቅት የልጁ ቤተሰብ አባላት አሽከርካሪዋ የ56 ዓመቷ ዶክተር ፌስለር መሆኗን የሚመሰክር ሰነድ የተሰጣቸው ሲሆን፤ ነገር ግን አሽከርካሪዋ የ80 ዓመት እድሜ እንዳላቸው በፖሊስ እንደተነገራቸው ገልጸዋል።

አደጋው በናታኒያ ዋና መንገድ ላይ፣ የመንገድ ላይ ካሜራ ባለበት አካባቢ፣ በጠራራ ፀሀይ የደረሰ ቢሆንም፤ ምን እንደተፈጠረ የሚያሳይ ግልጽ ፎቶግራፎች እንዳልተገኘ ፖሊስ መግለጹም ተመላክቷል።

ጠበቃው በአደጋው ወቅት የነበሩት ብቸኛው ሰው የልጁ አያት እንደነበሩ የገለጹ ሲሆን፤ ነገር ግን አደጋው ከተከሰተ ከኹለት ወራት በኋላ ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ መደረጉን ተናግረዋል።

ከዐቃቤ ሕግ ጋር ባደረጉት ስብሰባ፤ “በአሽከርካሪዋ ላይ ምንም አይነት የወንጀል ሪከርድ ስለሌለባት” ክስ እንደማይመሰርትባት ለቤተሰቡ መነገሩንም ጠበቃው አክለዋል።

ቤተሰቡ በአደጋውን ባደረሰችው ግለሰብ ላይ የራሳቸውን ምርመራ ያደረጉ ሲሆን፤ በ2012 ቀይ መብራት በመጣስና ወደ መሃል መንገድ በመግባት በሞተር ሳይክል ሹፌር ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሷን አረጋግጠዋል ተብሏል።

በዚህም በሕጻኑ ላይ አደጋውን በማድረሷ የተወሰደው ብቸኛ ሕጋዊ ቅጣት የሦስት ወር የመንጃ ፈቃድ እገዳ ሲሆን፤ ይግባኝ ከቀረበ በኋላ ወደ 45 ቀናት እገዳ እንዲቀነስ መደረጉንም ም ዘገባው አመላክቷል።በዚህም ብዙዎች ምርመራው ከዘረኝነት የመነጨ እንደሆነ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

“ኢ-ፍትሃዊነቱ ተደጋጋሚ ነው፡፡ በተለይ የቆዳችን ቀለም ጋር በተያያዘ ኹሉም ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በፖሊስ በተደበደቡበት ወቅት፤ ምንም አይነት ሰነድ የለም ብለው ነበር” ሲሉም ተቃዋሚዎቹ ገልጸዋል፡፡

“ይህ የአራት ዓመት ልጅ በተሳሳተ ማህበረሰብ ውስጥ የተወለደ እና የተሳሳተ የቆዳ ቀለም ያለው፤ የእስራኤል ማህበረሰብ ልጅ ነው፡፡” ያሉት ተቃዋሚዎቹ፤ “ሕጻኑ ተገድሏል፡፡ ውጤቱም አሳዛኝ ነው፡፡ መፍትሄው እስኪመጣ ድረስ ትግሉን እንቀጥላለን” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here