በሐዋሳ ደረቅ ወደብ ሊገነባ ነው

0
726

በሐዋሳ በተከራየው መሬት ላይ የደረቅ ወደብ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ለወደብ ግንባታ የሚሆን ሦስት ሄክታር መሬት ተረከበ።
የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪው አሸብር ኖታ ድርጅቱ እስከ አሁን ድረስ በሐዋሳ በተከራየው መሬት ላይ የደረቅ ወደብ አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነ በመግለጽ ከኪራይ የሚያድነውን የደረቅ ወደብ ግንባታ እንዲያከናውን የሚያስችለውን መሬት ከመንግሥት እንደተረከበ ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።
የደረቅ ወደብ ግንባታው ሲጠናቀቅ በሀዋሳ ኢንደስትሪያል ፓርክ ለሚገኙ አምራች ተቋማትና በአጠቃላይ በደቡብ ክልል ለሚገኙ ድርጅቶች አገልግሎት በመስጠት የጎላ ሚና ይጫወታል በሚል ተስፋ ተጥሎበታል። ይህንና ድርጅቱ መሬቱን ከመረከብ ባለፈ ግንባታውን መቼ ይጀምራል ለሚለው የጊዜ ገደብ እንዳላስቀመጠና ገና በንድፍ ጥናት ላይ መሆኑ ታውቋል።
ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡት ደረቅ ጭነቶች ውስጥ 80 በመቶ ለሚሆኑት አገልግሎት የሚሰጠው የሞጆ ደረቅ ወደብ በስምንት ነጥብ አራት ሄክታር መሬት ላይ በአንድ ጊዜ ስድስት ሺህ 300 ሀያ ፊት መጠን ያላቸውን ኮንቴነሮች የመያዝ አቅም አለው። ከዚህ በመነሳት በሶስት ሄክታር መሬት ላይ የሚገነባው የሐዋሳው ደረቅ ወደብ በአንድ ጊዜ በአማካኝ ሁለት ሺህ 250 ሀያ ፊት ኮንቴነሮችን የመያዝ አቅም ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል። እንዲሁም ለደረቅ ወደቡ ግንባታ ወደ 5 ሚሊየን ዶላር የሚገመት ወጪ ይጠይቃል።
በተያያዘ ዜና ባለፈው ዓመት በወረታ ለደረቅ ወደብ ግንባታ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ቦታ የተረከበ ሲሆን በኮምቦልቻ ደግሞ መሬት ለመረከብ ከመንግሥት ጋር እየተነጋገረ ይገኛል። የወረታ፣ ኮምቦልቻና ሐዋሳ ደረቅ ወደቦች መንግሥት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ላይ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ሊገነባቸው ካሰበቸው 35 ደረቅ ወደቦች መካከል ይመደባሉ።
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት 11 መርከቦች፣ 450 ከባድ መኪና እና 3,743 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን በ309 መዳረሻ ወደቦች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ከድርጀቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here