ኢትዮጵያ በቀጣዩ ወር የመጀመሪያ ሳተላይቷን ወደ ህዋ ልታመጥቅ ነው

0
782

ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሳተላይቷን በመጪው ወር ታህሳስ 7 2012 ወደ ህዋ እንደምታመጥቅ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ሳተላይቷ ኢቲ. አር ኤስ . ኤስ / አንድ የሚል ስያሜ የተሰጣት ሲሆን በግብርና ፣ በውሃ፣ በከተማ ልማት ፣ በአደጋ ሥራ አመራር እና በመሰል በርካታ ጉዳዮች ላይ መረጃ እንደምታቀርብ ተገልጿል፡፡ ሳተላይቷም ከቻይና መንግሥት የጠፈር ምርምር ተቋም ጋር በመተባበር ነው የምትመጥቀው፡፡

72 ኪሎ ግራም የምትመዝነው በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሳተላይት፣ በተወነጨፈች በግማሽ ሰዓት ውስጥ ከመሬት 700 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ምህዋርዋን እንደምትይዝ ተገልጿል፡፡

ሳተላይቷ ወደ ህዋ ከመጠቀች በኋላ በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ እና ምርምር ማዕከል ቅጥር ግቢ ውስጥ ለሳተላይቷ ትዕዛዝ ለመስጠት፣ ለመከታተል እንዲሁም ከሳተላይቷ የሚገኘውን መረጃ ለመቀበልና ለተጠቃሚ ለማዘጋጀት የሳተላይት መረጃ መቀበያ ጣቢያ ማዕከል ግንባታ መጠናቀቁን ኢንስቲቲዩቱ ገልጿል።

መንግሥት ለሳተላይት መረጃ ሲያወጣ የነበረውን በርካታ ወጪ ያስቀራል የተባለ ሲሆን በሳተላይቷ የዲዛይን ሥራ እና ግንባታ ላይ ኢትዮጵያውን ባለሙያዎች መሳተፋቸው በዘርፉ ኢትዮጵያ ያላትን ልምድ እና አውቀት ያሳድጋል ተብሏል፡፡ የሳተላይቷ መምጠቅ ኢትዮጵያ ለሳተላይት ምስል ግዢ በዓመት የምታወጣውን ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚያስቀርም ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የህዋ ሳይንስ መርሃ ግብሮች በተለይም በአደጉት አገራት እስከ 450 ቢሊዮን ዶላር ያንቀሳቅሳሉ ሲል የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት የገለፀ ሲሆን በቀጣይ ጊዜያት በኢትዮጵያ በሚኖረው የመሰረተ ልማት ግንባታ በኤሌክትሪክ እና ባቡር መስመሮች ዝርጋታ እንዲሁም በኢንቬስትመንት ዘርፎች ላይ ቀላል የማይባል ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡

የሳተላይቷ ግንባታ 2008 ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ የተፈረመና 2009 ላይ የተጀመረ ነው፡፡ ሥራውንም ለማጠናቅቅ ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የተደረገ ሲሆን ገንዘቡ ከቻይና መንግሥት የተገኘ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 55 ኅዳር 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here