ኤች ሲ በአማካይ 750 ሺሕ ቶን የድንጋይ ከሰል ለማቅረብ ተስማማ

0
1224

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅርቦት ኢንተርፕራይዝ ለድንጋይ ከሰል አቅራቢዎች አውጥቶት በነበረው ጨረታ ላይ ኤች ሲ ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር አሸነፈ። በመሆኑም ከደርባን ሲሚንቶ ፋብሪካ ውጪ ላሉት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚገመት፣ በዓመት በአማካይ 750 ሺሕ ቶን የድንጋይ ከሰል ለማቅረብ ተስማምቷል። ጨረታው በወጣበት ወቅት ዐሥራ ሁለት ድርጅቶች የጨረታውን ሰነድ የገዙ ቢሆንም የቴክኒክና ገንዘብ ነክ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የተሟላ ሰነድ ያቀረቡት ኤች ሲ እና ግሊን ኮር ኢንተርናሽናል የተባሉ ሁለት ድርጅቶች ብቻ ናቸው። በኢንተርፕራይዙ የነዳጅ ግዢና አቅርቦት ጉዳይ ዋና ኃላፊ የሆኑት አባይነህ አወል ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ግዢው በተለያየ ጊዜ ለአንድ ዓመት የሚቀርብ ሲሆን የዓለም ዐቀፍ ዋጋ እየታየ ማስተካከያ ይደረጋል። ነገር ግን ኤች ሲ ያቀረበው የትርፍ ሕዳግ ድርጅቱ ቀድሞ ባቀረበው መሠረት ይሆናል።
ኤች ሲ መቀመጫውን በጀርመን ያደረገ ተቋም ሲሆን በዓለም ላይ የግንባታ ቁሳቁሶችን በማቅረብ ይታወቃል። በ2008 በወጣ መረጃ መሠረት ድርጅቱ በዓለም ላይ በሚገኙ ወደ ስልሳ የሚጠጉ አገራት የሚንቀሳቀስ ሲሆን ወደ 60 ሺሕ ሠራተኞች አሉት። እንዲሁም ዓመታዊ ገቢው 15 ነጥብ 17 ቢሊዮን ዩሮ ይገመታል። ኤች ሲ 139 የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን የሚያንቀሳቅስ ሲሆን ፋብሪካዎቹ በዓመት 176 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም አላቸው።
የድንጋይ ከሰልን ለማቅረብ ከኤች ሲ ጋር ተፎካክሮ የነበረውና መቀመጫውን በሲዊዘርላንድ ያደረገው ግሊን ኮር ኢንተርናሽናል በዓለም ላይ ትልቅ ከሚባሉት ተቋማት መካከል አንዱ ነው። ግሊን ኮር የተለያዩ ምርቶችን በማምረት የሚታወቅ ሲሆን ከነዚህም መካከል ብረታ ብረት፣ ማዕድናት፣ ድፍድፍ ዘይት፣ የተፈጥሮ ዘይት፣ የግብርና ምርቶችንና የድንጋይ ከሰልን መጥቀስ ይቻላል። በ2009 በወጣ መረጃ መሠረት ድርጅቱ ከ145 ሺሕ በላይ ሠራተኞች አሉት። እንዲሁም ዓመታዊ ገቢው ከ205 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ይገመታል።
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅርቦት ኢንተርፕራይዝ በዓመት ውስጥ ወደ 600 ሺሕ ቶን የድንጋይ ከሰል በሀያ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጥያቄ መሠረት ከውጪ ወደ አገር ውስጥ ያስገባል። ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅርቦት ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ የነዳጅ ግዢን ማካሔድ ቢሆንም በተለያዩ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች እና ሌሎች ድርጅቶች ጥያቄ መሠረት ከ2005 ጀምሮ ድርጅቶቹን በመወከል የድንጋይ ከሰልን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ላይ ይገኛል።
በዓመት ከ750 ሺሕ ቶን በላይ የድንጋይ ከሰል ወደ አገር ውስጥ የሚገባ ሲሆን፣ ሁለት ሦስተኛ ያህሉን የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ይጠቀሙታል። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ በዓመት 197 ሜትሪክ ቶን የድንጋይ ከሰል የማምረት አቅም ቢኖራትም አብዛኛው የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ለኃይል ምንጭነት የሚጠቀሙትን የድንጋይ ከሰል ከውጪ አገር ነው የሚያስገቡት።

 

ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here