አርብ መስከረም 11 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እና በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት እንደገለጹት፤ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት በሱዳን ከ700 ሺሕ በላይ ሕጻናት በሞት አፋፍ ላይ ናቸው።
ከሕጻናቱ በተጨማሪም በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች በተለይ በካርቱም፣ ዳርፉር እና ኮርዶፋን የምግብ፣ የውሃ፣ የመጠለያ፣ ኤሌክትሪክ፣ ትምህርት እንዲሁም የጤና አገልግሎት እያገኙ እንዳልሆነ ተነግሯል።
በአገሪቱ ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል እየተደረገ ባለው ውጊያ ግማሹ የአገሪቱ ሕዝብ ምንም ዓይነት የምግብ ዋስትና የሌለው መሆኑን የገልጸው የመንግሥታቱ ድርጅት፤ ከስድስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች እጅግ ለከፋ ረሃብ መጋለጣቸውን ጠቅሷል፡፡
በዚህም ለረሃብ የተጋለጡ ሰዎች ለተለያዩ ወረርሽኞች እና ተላላፊ በሽታዎች ሊጋለጡ ይችላሉ ያለው ተመድ፤ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃትም በእጅጉን አሳሳቢ ነው ማለቱን አዲስ ማለዳ ከመግለጫው ተመልክታለች፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በኹለቱ ኃይሎቸ መካከል እየተደረግ ያለው ውጊያ፤ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሕፃናትን ጨምሮ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ከቤታቸው ንብረታቸው አፈናቅሏል።
ሰባተኛ ወሩን ባስቆጠረው የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ከሰባት ሺሕ በላይ ሰዎች ለሞት የተዳረጉ ሲሆን፤ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የአገሪቱ ዜጎች ደግሞ ወደ ተለያዩ ጎረቤት አገራት ተሰደዋል።



