አርብ መስከረም 11 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በሽብር ተግባር ላይ ተሰማርቶ በማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን ሲፈጽም የነበረውና ጃል አብዲ ጌታቸው (በቅፅል ሥሙ ጃል ዬወሚፈን) በመባል የሚጠራው የኦነግ ሸኔ አመራር፤ ሰሞኑን በመከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገልጿል።
ሻለቃ ሲሳይ አብዲ “አሸባሪውን የኦነግ ሸኔ ቡድን እግር በእግር ተከታትሎ ከመምታት ባሻገር የመረጃ ሥራዎችን በዘመናዊ መልክ በማጠናከር ጠላትን ከማህበረሰቡ የመነጠል ሥራ እየተሠራ ነው።” ያሉ ሲሆን፤ የሽብር ቡድኑ በተለያዩ ጊዜያት የሸኔ አባላትን እያሰለጠነ ቢልክም የጥፋት አላማውን ማሳካት ሳይችል መቅረቱን ተናግረዋል።
የሽብር ቡድኑ መሪ የሃሩ ጥሮ ከተማ ንዋሪ የሆኑትን ጉልማ ዲሳሳ፣ ወርቁ ሙልጌታ፣ ሞቱማ አስራቴ እና በርሲሳ ቶሎሳን “የመንግሥት ደጋፊ ናችሁ” በማለት በማሰርና በአሠቃቂ ኹኔታ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ሲፈጽም መቆየቱንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም በሃሩ ጥሮ ከተማ ወስጥ አንድ ቤተሰብ ሙሉ በማፈን ገንዘብ በመጠየቅ ሲያሰቃይና ሲያንገላታ ከቆየ በኋላ፤ ወላጅ አባታቸውን በመግደል ከልጆቹ 100 ሺህ ብር መቀበሉን ሻለቃ ሲሳይ አብራርተዋል።
በቁጥጥር ሥር የዋለው ይህ የሽብር ቡድኑ መሪ በአውደ ውጊያ ውስጥ 21 የኦሮሚያ ፓሊሶችን በማፈን ከፍተኛ እንግልትና ስቃይ እንዳደረሰባቸውም ምክትል መቶ አለቃ ኢብራሂም ሙሳ መናገራቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።



