አሜሪካ ለኢትዮጵያ ሚስጥራዊ መረጃዎችን አቀብሏል ያለችውን ግለሰብ ከሰሰች

0
478
አርብ መስከረም 11 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የአሜሪካ መንግሥት ለፍትህ ቢሮውና ለውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በኮንትራት ተቀጥሮ በሠራተኝነት ይሰራ የነበረውን ግለሰብ፤ በስለላ ጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ተገልጿል።
ግለሰቡ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለኢትዮጵያ በማቀበል መጠርጠሩን አቃቢያን ሕጎች አስታውቀዋል።
በዚህም አብርሀም ተክሉ ለማ የተባለው የ50 ዓመት ግለሰብ ሦስት ክሶች እንደቀረቡበት ተገልጿል፡፡
እነርሱም የአገሪቱ ፍትህ ቢሮ የብሄራዊ መከላከያ መረጃዎችን ለሌላ አገር ማስተላለፍ፣ ለውጭ አገር የመከላከያ መረጃዎችን ለማስተላለፍ በማሴር እና ጥብቅ የመከላከያ መረጃዎችን በመያዝ ወንጀሎች የሚሉ መሆናቸው ተነግሯል።
ተጠርጣሪው ከታህሳስ 2022 እስከ ነሀሴ 2023 ድረስ ከደህንነት ሪፖርቶች ሚስጥራዊ መረጃዎችን ቀድቷል የተባለ ሲሆን፤ የተለያዩ የምደባ ምልክቶችን ከውስጣቸው መሰረዙንም የአገሪቱ ፍትህ ቢሮ ገልጿል።
በክሱ ዐቃቤ ሕግ በቀጥታ የኢትዮጵያን ሥም ባይጠቅስም፤ ግለሰቡ ለትውልድ አገሩ፣ ቀድሞ ዜጋ ለሆነበትና ቤተሰቦቹ ለሚኖሩበት አገር ሰልሏል ማለቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
ፍትህ ቢሮ በተጨማሪም ግለሰቡን “ትውልደ ኢትዮጵያዊ የአሜሪካ ዜጋ” ሲል መጥራቱ ተነግሯል።
እንዲሁም ግለሰቡ ‘ሚስጥራዊ’ እና ‘ከፍተኛ ሚስጥር’ በሚል የተፈረጀውን መረጃ ከስቴት ዲፓርትመንት ጥብቅ ተቋማት ማስወገዱ የተገለጸ ሲሆን፤ ያለፍቃድ ይህ መረጃ ደርሶታል፣ ገልብጧል፣ አስወግዷል እንዲሁም በእጁ ላይ አቆይቷል ተብሏል፡፡
አብርሀም ይህን ሚስጥራዊ የሆነ የአገር መከላከያ መረጃ ከውጭ አገር የስለላ አገልግሎት ጋር ግንኙነት ላለው የውጭ መንግሥት ባለስልጣን ለማስተላለፍ ሚስጥራዊ የሆነ መተግበሪያ (አፕሊኬሽን) መጠቀሙንም የአገሪቱ ፍትህ ቢሮ አስታውቋል።
በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
ግለሰቡ በኹለቱ የስለላ ክሶች ጥፋተኛ ከተባለ ከእድሜ ልክ እስራት እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣት ይጠብቀዋል የተባለ ሲሆን፤ በተጨማሪም መረጃውን ሆን ብሎ በማቆየት ክስ ከፍተኛው የ10 ዓመት እስራት እንደሚያስቀጣው ተመላክቷል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here