ይኾኖ!

0
478

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ካለፈው ሳምንት ቀደም ብሎ በመቀሌ ከተማ ‹ይኾኖ!› ወይም ‹ይበቃል!› የሚል ሰልፍ ተካሒዶ ነበር። ሰልፍም ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ማህበራዊ ገጾችም ተመሳሳይ ቅስቀሳዎችና ማንቂያ ደወሎቸ ታይተዋል፤ ተሰምተዋል። ግን ‹ይበቃል› ባልን ቁጥር ‹ይበል› የተባለ ይመስል ችግር እንደ አዲስ እየተሰማ ይገኛል።

በአገራችን የተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሁን ላይ ባሉ አለመረጋጋቶች ሕይወታቸው ካለፈ ተማሪዎች በተጓዳኝ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችም አሉ። ጥበቃ እንዲደረግላቸው አቤት ቢባልም ነፋሱ ድምጽና ጩኸቱን የት እንደሚያደርሰው አይታወቅም፤ የሰማም ያለ አይመስል።

ከተለያዩ ምንጮች መረዳት እንደተቻለው አለመረጋጋት ባለባቸው ዩኒቨርስቲዎች ሴት ተማሪዎች ወጥተው ለመመገብ እንኳ ተቸግረዋል። ያልተሰሙና ያልተነገሩ ለቅሶዎች እንዳለፉና እያለፉ እንደሆነም ጥርጥር የለውም። እናም ዛሬም ይኾኖ እንድንል ያስገድዳል። ግን እስከመቼ?

አንድ እውነት አለ፤ ግርግርና ሁከት ባለባቸው ቦታዎች ሁሉ የሴቶች ጥቃት ይከሰታል። ይህንን ሐሳብ አንስተውም በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ‹መደበኛ› ለማድረግ የሚሞክሩ ሰዎች አሉ። ይህን ሐሳብ እንደ አውዱ ልዩነት በተለያየ ምክንያት ልንጠቀመው ብንችልም ለሁሉም እውነት መሆን አለበት ማለት ግን አይደለም።
ተመልከቱ! ከአውሮፓውያን አቆጣጠር 1960 ቀድሞ በርካታ የአፍሪካ አገራት በቅኝ ግዛት ስር ነበሩ። ሁሉም በቅኝ ግዛት ስር ስለሆኑና ቅኝ ግዛት የብዙ አፍሪካውያን የጊዜው ‹ነባራዊ› እውነት ቢሆንም፤ ለኢትዮጵያ ግን ሊሠራ አልቻለም። ‹የትኛውም የአፍሪካ አገራት› እንደሆኑት አይደለም ኢትዮጵያ የሆነችው፤ ታሪክ መሥራት ችላለች። ሕዝቧ ራሱን ከራሱ ጋር እንጂ ከማንም አላነጻጸረም፤ ነገሥታቱም ሰው ብሎ ከሰው የሚያንስም ሆነ የሚበልጥ የለም ብለው አሸናፊ ሆነዋል፤ ነጻነቷም ተጠብቆ ቆይቷል።

ይህ በአገር ከሆነ በሴቶችም ለምን አይሆንም። እስከ መቼ ነው ‹በሁሉም አገር ያለ ነው!› እያልን የምናቀርበው፤ ‹ይበቃል!›ስ የምንለው? የ‹ይበቃል› አብዮት መቼ ነው የሚያበቃው? በብሔርና በመሰለው ከማንነት ደረጃ ዝርዝር መጨረሻ የተቀመጠን ጉዳይ መነሻ አድርገው ‹እንደራጅ!› የሚሉ ሰዎች ብዙ ናቸው። ከሰውነት በላይ ብሔርን አድርገው፣ ከሰውነት በላይ ጎሳን ጠርተው ‹ተደራጅ!› ይላሉ። ያውም ተደራጅተው መንገድ የዘጉ፣ ወገናቸውን የገደሉ እና የተሳደቡ እንጂ ቁም ነገር የሠሩ ብዙም የሉም።

አዲስ ማለዳ ጥቅምት 29 በወጣው በ53ኛ እትሟ ከሴታዊት የሴቶች መብት ተሟጋቾች መካከል ከሆነችው ስሂን ተፈራ (ፒ.ኤች.ዲ) ጋር ባደረገችው ቆይታ፤ ስሂን ይህን ሐሳብ ጠቅሳ ነበር። የሚያሳስባትም በተለይ ስኬት ላይ ደረሱ የተባሉ ሴቶች ለምን ለሌላ ሴቶች አይቆሙም የሚል ነበር። ይህ አንዱ ነገር ሆኖ ሳለ፤ ሴቶችስ ለምን አንደራጅም!? ለስድብና ለጥላቻ አይደለም፤ እርስ በእርስ ለመጠባበቅ። በዩኒቨርስቲ አንዲት ሴት ብቻዋን እንድትገኝ ለምን ይሆናል? ‹ይበቃል!› ብለን ጥቃት ለደረሰባቸው እንደጮኽን፤ ከዚህ በኋላ ማንም ላይ ጥቃት እንዳያደርስ ለምን አንዳችን ለሌላችን አንቆምም? ስንቱ ለማይረባ ነገር ሲደራጅ…ለመብታችን ያውም በደኅና የመኖር መብታችንን ለምን እናስነካለን!

ይህን ማድረግ ከተቻለ ለሴቶች ብቻ ሳይሆን ለአገር የሚተርፍ ጉልበት አለ ብዬ አምናለሁ። ከዚህም አልፎ ከዚህ ሐሳብ ጎን የሚቆሙ ወንዶች፤ ‹ሴት እህትህ! እናትህ! ልጅህ! ሚስትህ!› በሚል ሰበካ ሳይሆን ሰውን በሰውነት የማክበር ልኅቀት ላይ የደረሱ ሲገኙ፤ በሩን ከፍቶ ማስገባት። ከዚህ በኋላ ይበቃል ብለን የምንጮኸው ማን እንዲሰማ ነው? ማንስ ሰምቶ ያበቃዋል?

ለጊዜው ያለው አማራጭ እርስ በእርስ ለመጠባበቅ፣ እህትማማች ለመሆን ቃል በመገባባት መደራጀት ነው። አልፎም ለጩኸቱ መልስ ሊሰጥ የሚችለው ወንበር ላይ ደርሶ፤ በብቃትም በእውቀትና በማስተዋልም የመፍትሔ ሰው መሆን።
በሊድያ ተስፋዬ

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here