የቤንዚን ኮንትሮባንድ የነዳጅ እጥረት አስከተለ

0
744

በያዝነው ዓመት በአገሪቷ የገባው የቤንዚን መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ15 በመቶ ቢያድግም ከፍተኛ እጥረት አጋጥሟል። ለዚህም የቤንዚን ጥቁር ገበያ መስፋፋትና የኮንትሮባንድ ንግድ መጠናከር እንደ ዋና ምክንያት ቀርቧል። እጥረቱ በዚህ በያዝነው ኅዳር ወር ሲያጋጥም ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች የሚገኙ ነዳጅ ማደያዎች ሥራ ለማቆም ተገደዋል።
ሜክሲኮ አካባቢ የሚገኘው የኖክ ነዳጅ ማደያ የሽያጭ ሠራተኛ ለአዲሰ ማለዳ እንደገለጸው ከሆነ ባለፉት ዓመታት የኖክ ነዳጅ ማደያ በ24 ሰዓት ውስጥ በአማካይ አምስት ሺሕ ሊትር ነዳጅ ይሸጥ ነበር። ከጥቂት ወራት ወዲህ ግን በከተማው ውስጥ ባጋጠመው የነዳጅ እጥረት ሳቢያ የነዳጅ ፍላጎት በመጨመሩ በ24 ሰዓት ውስጥ እስከ 10 ሺሕ ሊትር ነዳጅ በመሸጥ ላይ ነበሩ። ከሳምንታት በፊት ግን የቤንዚን እጥረቱ እየተባባሰ በመምጣቱ ባለፉት ሰባት ቀናት ምንም ዓይነት ቤንዚን ማደያው ማግኘት አልቻለም። በመሆኑም ማደያው ለተጠቃሚዎቹ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዳልቻለ የሽያጭ ሠራተኛው ገልጿል።
የማደያው ተጠቃሚ የሆነው አብርሃም ሲራክ የተባለ የጥናት ባለሙያ ሥራውን ለማቀላጠፍ በአብዛኛው ተሸከርከሪን መጠቀም ከሚገደዱት መካከል ነው። በተለይም በአገሪቱ ካለው የመጓጓዣ እጥረት አንፃር መረጃ ከተለያዩ ድርጅቶች ለመሰብሰብ በሚወጣበት ወቅት መኪና መጠቀም ይኖርበታል። ባለፉት ሰባት ቀናት ግን የተለመደውን የሥራ እንቅስቃሴ ካጋጠመው የቤንዚን እጥረት ጋር በተያያዘ ማድረግ አልቻለም። በከተማው ውስጥ የሚገኙ ከስድስት በላይ ማደያዎች ጋር ቢሔድም የፈለገውን ቤንዚን ማግኘት አዳጋች ሆኖበታል። ስለሁኔታው ሲገልጽም “ሥራችንን በተቀላጠፈ መልኩ ለመፈጸም መኪና መጠቀም የግድ ቢሆንም መኪናችንን አቁመን በእግር ለመሔድ ተገደናል” ብሏል።
ችግሩን ለወዳጆቹ ያስረዳው አብርሃም፣ መፍትሄ ከጥቁር ገበያ እንደሚያገኝና የፈለገውን ያህል ቤንዚን መግዛት እንደሚችል ይረዳል። በዚህም መሠረት “ከዋናው ዋጋ በሶስት ብር ጭማሪ የምፈልገውን ያህል ቤንዚን ቀጨኔ አካባቢ ከሚገኝ መሸጫ ገዝቻለሁ” ብሏል። እጥረቱ ከኅዳር ወር መጀመሪያ አንስቶ እየተባባሰ መምጣቱን የገለጸው አብርሃም ለብዙ ቀናት መጉላላቱ ወደ ጥቁር ገበያ ፊቱን እንዲያዞር እንዳስገደደው ይገልጻል። በእርግጥ አብርሃም ብቸኛው የጥቁር ገበያ ተጠቃሚ አልነበረም። ባለፈው ሳምንት ጥቂት የማይባሉ የመኪና ባለቤቶችና ድርጅቶች ያላቸውን ፍላጎት ለማሳካት ፊታቸውን ቤንዚን በሌትር ወደ 23 ብር ገደማ ወደሚሸጥበት ጥቁር ገበያ ለማዞር ተገደዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአውሮፓውያኑ 2016/17 ግምቱ 37 ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር የሚሆን ሦስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ በኢትዮጵያ ነዳጅ ኢንተርፕራይዝ አማካይነት ወደ አገር ውስጥ ገብቷል። ይህም የነዳጅ ዋጋ በ23 ነጥብ አንድ በመቶ፣ መጠኑ ደግሞ በ13 በመቶ ማደጉን ያሳያል። ከዚህ ውስጥ ከ363 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ የሚሆነው ቤንዚን ነው። ምንም እንኳን አቅርቦቱ በ13 በመቶ ቢያድግም በአዲስ አበባ የቤንዚን እጥረት ሲታይ ቆይቷል።
በአገሪቷ የነዳጅ ግዢና ስርጭትን ለመቆጣጠር የተመሠረተው የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅርቦት ኢንተርፕራይዝ እጥረቱ ሰው ሰራሽ ነው ብሏል። በኢንተርፕራይዙ የነዳጅ ግዢና አቅርቦት ጉዳይ ዋና ኃላፊ አባይነህ አወል ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት በተለያዩ አካባቢዎች በድብቅና አልፎ አልፎም በገሀድ የተከፈቱት የነዳጅ አቅራቢዎች ለእጥረቱ ዋነኛ ተጠያቂ ናቸው ብለዋል። በተጨማሪም በጎረቤት አገራት የተከሰተው የቤንዚን እጥረትና የሕገወጥ የነዳጅ ነጋዴዎች መበራከት ለችግሩ መባባስ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል። የጎምጁ የነዳጅ ማደያ የሽያጭ ሠራተኛ እንደሚሉት ከሆነ ግን ለእጥረቱ ዋነኛ ምክንያት የአቅርቦት እጥረት ነው ብለዋል። ለምሳሌ ጎምጁ በወር 26 መኪና አካባቢ ነዳጅ ብቻ እንደሚያገኝ የገለጹ ሲሆን ፍላጎታቸው ግን ከዚያ በላይ መሆኑን አክለዋል።
በአሁኑ ወቅት የፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን መረጃ እንደሚያመለክተው ከግማሽ ሚሊየን በላይ መኪኖች ይገኛሉ። ከባለፈው ዓመት በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር ቁጥሩ ከ70 ሺሕ (17 በመቶ) በላይ ጭማሪ አሳይቷል። ይህንን ጭማሪ ከግምት ውስጥ ያስገባ ነዳጅ ማስገባቱን የሚገልጸው የነዳጅ አቅራቢ ኢንተርፕራይዝ፣ ለእጥረቱ በአገሪቱ ያለውን የነዳጅ ጥቁር ገበያ መስፋፋት እንደ ዋነኛ ምክንያት ያቀርባል። እንደ አባይነህ ገለጻ በአገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች በተለይም በአዲስ አበባ በሕገወጥ መንገድ ከማደያዎች ጥቂት የማይባል ነዳጅ በበርሜል እየተቀዳ ለተጠቃሚዎች እንደሚሸጥ ይገልጻሉ።
“ችግሩን ቀድመን የተረዳነው ቢሆንም የመቆጣጠር ሥልጣን ስለሌለን ምንም ማድረግ አልቻልንም” ብለዋል። የነዳጅና ሌሎች ግብይቶችን እንዲቆጣጠር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣን የተሰጠው የንግድና ኢንዱሰትሪ ሚንስቴር ነው። ከሚንስቴሩ በስልክም ሆነ በአካል መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ኃላፊዎቹ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አልተሳካም። ይሁንና የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደተናገሩት ከኮንትሮባንዱ በተጨማሪ በሱዳን ድንበር በኩል ያለው አለመረጋጋት የነዳጅ አቅርቦቱን እንደቀነሰው ይናገራሉ፡፡

 

ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here