ለአዲስ አበባ ከተማ 7.5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት የሚያቀርቡ አራት ድርጅቶች ተመረጡ

0
824

የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ለከተማዋ ሰባት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሊትር የፓልም ዘይት የሚያቀርቡ አራት ድርጅቶችን መርጦ ለንግድ ሚኒስቴር መላኩን እና ከዚህ ቀደም በጨረታ ሂደቱ ላይ ውዝግብ አስነስቶ የነበረው ጌታስ ኢንተርናሽናልም በሌላ አቅራቢ እንዲተካ መደረጉን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ፡፡
ናይል ሶርስ ፣ አፍሪካ እና ስታር ቢዝነስ ግሩፕ ዘይቱን እንዲያስመጡ የተመረጡ ሲሆን በጌታስ ቦታም ደብሊው ኤ የተባለ ድርጅት እንዲተካ መደረጉንም አዲስ ማለዳ ከንግድ ቢሮው ያገኘችው መረጃ ያስረዳል፡፡

የንግድ ሚኒስቴር የህረተሰቡን መሠረታዊ የፍጆታ እቃ የሆነውን የዘይት ምርት አቅርቦትና ፍላጎትን ለማሟላት በ2011 አዲስ መመሪያ አውጥቶ የዘይት ግዢ ሂደቱን ወደ ክልልና ከተማ አስተዳደር በማውረድ እንዲሁም ክልሎችም መመሪያውን ተከትለው አዲስ አስመጪዎችን በመመልመል ለፌደራል መንግስት እጩዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

የመመሪያው ዋና ዓላማም መሰረታዊ ሸቀጥ የሆነውን የምግብ ዘይት ከህብረተሰቡ የመግዛት አቅም ጋር ተገናዝቦ የአቅርቦት፣ ስርጭት እና የዋጋ ቁጥጥር እየተደረገበት ለህብረተሰቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ በሚል በመመሪያው ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ በመንግስት ድጎማ የሚመጣው የፓልም የምግብ ዘይት በአገር ውስጥ አምራቾች በሂደት ለመተካት እቅድ እንዳለውም ንግድ ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ቢያስታውቅም እስካሁን ከውጪ ሃገር በከፍተኛ ወጪ እንዲገባ መደረጉ ቀጥሏል፡፡

በዚህ መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ለአቅራቢዎች ጨረታ በማውጣት አራት ድርጅቶችን ለመምረጥ ባወጣው ጨረታ ተወዳዳሪ የነበረው ጌታስ በባንክ ሂሳቡ ውስጥ በቂ ማስተማመኛ ገንዘብ ባለመኖሩ ምክኒያት ውድቅ መደረጉን በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ውስጥ የገዢ ክፍል ባልደረባ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
‹‹የአስመጪነት የስራ ልምዳቸው፣ በማንቀሳቀስ ላይ የሚገኙት ገንዘብ መጠን፣ ተቀማጭ ገንዘባቸው እንዲሁም የመኪና እና የ መጋዘን አቅርቦት አቅማቸው በመመዘኛነት ተይዧል›› ሲሉም ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱት የግዢ ባለሞያ አክለዋል፡፡

ከ ሁለት ወራት በፊት የአቅራቢዎቹን ውጤት እና ስም ዝርዝር ቢሮው ባሳወቀበት ወቅት ከአራቱ ድርጅቶች መካከል አንዱ የነበረው ጌታስ ኢንተርናሽናል በመጀመሪያዎቹ መለኪያዎች አልፎ የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ግን ገነዘቡ በአካውንቱ መቶ ሚሊዮን ብር መገኘት እለበት በለመገኘቱ ከጨረታው ውጪ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በአንፃሩ በደብሊው ኤ ዘይት ፋብሪካ የባንክ አካውንት ውስጥ ግን በቂ ገንዘብ መኖሩን ተረጋግጧል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። አሰራሩን ግልፅ ለማድረግም የድርጅቶቹን ስም በማሳወቅ ቅሬታ ያለቸው ተወዳዳሪዎች ካሉ ቅሬታቸውን የሚያቀርቡበት እድል ተሰጠጥቶ እንደነበር ተገልጿል፡፡

ለአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በወር ሰባት ሚሊዮን ሌትር በላይ ዘይት እንደሚያስፈልግ የገለፀው ቢሮው ለምን ያህል ጊዜ የሚበቃ ዘይት እንደሚገዛ የሚወስነው ንግድ ሚኒስቴር እንደሚወስን ገልጿል።

ከሐምሌ 2008 ጀምሮ የፓልም ዘይት አስመጪነት ፈቃድ ያላቸው 9 ድርጅቶች በየወሩ 40 ሚሊዮን ሌትር ዘይት የሚያስገቡ ሲሆን ባለፉት አራት ዓመታት ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ የፓልም ዘይት ወደ አገር ውስጥ አስገብተዋል፡፡ መንግስትም በእያንደዳንዱ ሌትር ላይ 0.36 ሳንቲም ደጎማ የሚያደርግ ሲሆን በየወሩ ከ 14 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያደርጋል፡፡

አቅራቢዎቹ በመንግስት በልዩ ሁኔታ የውጪ ምንዛሬ ተፈቅዶላቸው ወደ አገር ውስጥ በማስገባታቸው በአገር ውስጥ የሚገኙ አምራቾች ፍትሀዊ ያለሆነ እና ያልተገባ ተግባር ነው በማለት በማህበሮቻቸው በኩል በተደጋጋሚ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ነበር፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 55 ኅዳር 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here