የአዋሽ ወልዲያ- ሀራ ገበያ የባቡር መስመር ተደጋጋሚ ስርቆት እየተፈጸመበት መሆኑ ተገለጸ

0
170

ማክሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) 82 በመቶ የደረሰው የአዋሽ- ወልዲያ- ሀራ ገበያ የባቡር መስመር የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፕሮጀክት ተደጋጋሚ ስርቆት እየተፈጸመበት መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ ዘርፍ የፕሮጀክቱ የሳይት ሥራ አስኪያጅ ተክለወይኒ ብርሃነ፤ በፕሮጀክቱ እስከ አሁን ከተተከሉ 175 የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሶሶዎች መካከል በ37ቱ ላይ ስርቆት መፈጸሙን ገልጸዋል።

ከመስከረም 2/2016 ጀምሮ በተፈጸመው ስርቆት 6 ሺሕ የሚሆኑ የምሰሶ ብረቶች ተፈተው የተወሰዱ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 262 የሚሆኑት በፖሊስ በኤግዚቢትነት ተይዘው እንደሚገኙም ተናግረዋል።

በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ዱብዱብ በሚባል ቀበሌ በፕሮጀክቱ ላይ የተፈጸመው ስርቆት የግንባታ ሥራውን በተያዘለት ጊዜና በጀት ለማጠናቀቅ እንቅፋት እንደሚሆንም ሥራ አስኪያጁ አመልክተዋል።

ስርቆቱ ከተፈጸመ ጀምሮ ችግሩ በስፋት በሚስተዋልበት አካባቢ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የቁጥጥርና የጥበቃ ሥራ በመጀመሩ የስርቆት ወንጀሉ የመቀነስ አዝማሚያ ማሳየቱንም ተናግረዋል፡፡

ከአንድ ምሶሶ ከ150 እስከ 200 የሚጠጉ ብረቶች ተፈተው እንደተወሰዱ የተጠቆመም ሲሆን፤ ተሰርቀው የተወሰዱትን ብረቶች ለመተካት 12 ነጥብ 5 ማሊዮን ብር እንደሚጠይቅ ተነግሯል።

እስከ አሁን ከስርቆት ወንጀሉ ጋር በተገናኘ ሰባት ሰዎች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ እና ከዚህ ውስጥ አራቱ ከንብረቱ ጋር እጅ ከፈንጅ የተያዙ መሆናቸውን፤ የአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here