ኢባትሎአድ በሚል የግንባታ ፕሮጀክት ሥም እየተገነባ ያለው የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታው በወቅቱ ባለመጠናቀቁ ከ295 ሚሊየን ብር በላይ ተጨማሪ ወጪ አስወጣ። በሦስት ዓመት መጠናቀቅ የነበረበት ሕንፃው ለተጨማሪ ዘጠኝ ዓመታት ዘግይቶም ባለመጠናቀቁ በድጋሚ ለስድስት ወራት ተራዝሟል።
ከ12 ዓመት በፊት የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የሕንፃውን ግንባታ ለመጀመር ጨረታ ባወጣበት ወቅት ዲኤምሲ፣ ቬርኔሮና ሚድሮክ ኮንስትራክሽን የመወዳደሪያ መሥፈርቱን አሟልተው ከተወዳደሩ በኋላ ዲኤምሲ ጨረታውን ተጨማሪ እሴት ታክስን ሳይጨምር ከ131 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ዋጋ አሸንፎ ነበር። ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከዲኤምሲ ኮንስትራክሽ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር ጋር የግንባታ ውል መስከረም 4/1999 ተፈራርሟል። የማማከሩን ሥራ ለማሠራትም ከብሔራዊ የአጥኚ ኩባንያ ጋር ተስማምቶ ነበር። በዚህም ዲኤምሲ የግንባታ ቦታውን ጥቅምት 4/1999 ተረክቦ፣ ታኅሣሥ 15/1999 ሥራ ጀምሯል።
ይሁንና ግንባታውን በሦስት ዓመት አጠናቆ ታኅሣሥ 16/2002 ለማስረከብ የተስማማ ቢሆንም በተባለው ቀን ግንባታውን አጠናቆ ማስረከብ ሳይችል ቀርቷል። ለግንባታው መዘግየት የመሬት መቆፈሪያ መሣሪያዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ስድስት ወር መፍጀቱ፣ የሲሚንቶ እጥረትና የባንክ ብድር አለማግኘት በምክንያትነት ተጠቅሰዋል።
የአዲስ ማለዳ የውስጥ ምንጮች ዲኤምሲ ለግንባታ የቀረበለትን 15 ሺሕ ኩንታል ሲሚንቶ ከፕሮጀክቱ ውጭ ለሌላ አገልግሎት መጠቀሙ ለግንባታው መዘግየት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። በዚህና ሌሎች ምክንያቶች አስገንቢው ድርጅት ከዲኤምሲ ጋር የነበረውን የግንባታ ውል ሐምሌ 1/2003 አቋርጧል።
ከዲኤምሲ ጋር ያለው ውል ከተቋረጠ በኃላ ግንባታውን መልሶ ለማስጀመር ተክለብርሃን አምባዬ፣ ገምሹ በየነና የቻይና ኮሙዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን የተወዳደሩ ሲሆን ተክለብርሃን አምባዬ ተጨማሪ እሴት ታክስን ሳይጨምር ከ426 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ የግንባታ ዋጋ አሸንፏል። በዚህም የግንባታ ውሉ ሐምሌ 28/2007 ተፈርሟል። የግንባታውን ቦታ ነሐሴ 9/2007 ተቀብሎ ግንባታውን በ540 ቀናት እዲጠናቀቅ ሥምምነት ላይ ተደርሶ ነበር።
ይሁን እንጂ ተጨማሪ 581 ቀን ጠይቆ የፀደቀለት ሲሆን ግንባታውን ለማጠናቀቅ በጠቅላላ በ1,121 ቀን (ሦስት ዓመት አካባቢ) እንደሚፈጅበት ተስማምቶ ነበር። ይሁንና በውሉ የተያዘው የማስረከበያ ጊዜ መስከረም 20/2011 አልፎም ግንባታው አልተጠናቀቀም። ተቋራጩ ግንባታውን የማጠናቀቂያ ተጨማሪ 193 ቀናት ተፈቅዶለታል። የተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰይፉ አምባዬ ለግንባታው መዘግየት የውጪ ምንዛሬ እጥረትን በምክንያትነት እንዳቀረቡ ከዚህ ቀደም የነበሩ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች አመላካች ናቸው።
የአዲስ ማለዳ ምንጮች ግን ከሕንፃው አጠገብ በሚገኘው የኢትዮጵያ መድን ድርጅትና በሕንፃ ግንባታው ሳይት ላይ የወሰን አለመግባባቶች እንደነበሩ ገልጸዋል።
አዲስ ማለዳ ያልተጠናቀቀው ሕንፃ ሁለተኛና ሦስተኛ ወለል ለድርጅቱ የቢሮ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ተመልክታለች። በ3,200 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ሕንፃው አናቱ ላይ ተሽከርካሪ ሬስቶራንት ያለው ባለ ዐሥራ ስምንት ወለል ሕንፃ ሲሆን ከመሬት በታች ተጨማሪ ሁለት ወለሎች አሉት።
ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011