በፋኖ ታጣቂዎች እና በታጠቁ ነዋሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ከ18 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

0
297

ረቡዕ ጥቅምት 28 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል ኦሮሞ ልዩ ዞን በአርጡማ ፋርሲ ወረዳ በፋኖ ታጣቂዎች እና በታጠቁ ነዋሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ከ18 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል።

ጥቅምት 25/2016 በአከባቢው ቀኑን ሙሉ በተካሄደ ውጊያ ከ30 በላይ የሚሆኑ ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ 10 የሚሆኑት ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰባቸው ለተጨማሪ የሕክምና እርዳታ ወደ ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል መወሰዳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ነግረውኛል ሲል አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል።

ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ ታጣቂዎቹ የመጡት ከአጎራባቹ የሰሜን ሽዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ ማጀቴ ከተማ መሆኑን ማስታወቃቸውንም ዘገባው አመላክቷል።

“በአርጡማ ፉርሲ ወረዳ በሚገኙ ሦስት መንደሮች ላይ እሁድ ዕለት ቀኑን ሙሉ ከፍተኛ ውጊያ ነበር፣ ይህ ውጊያ ከመደረጉ ከሦስት ቀን በፊት ጥቅምት 22 የፋኖ ታጣቂዎች ወደ ወረዳችን በመግባት አንድ ሽማግሌ ገድለው ሄዱ፤ ከዚያም እሁድ ዕለት በድጋሚ መጥተው ጥቃት አደረሱ፤ ከዚያም ነዋሪው አጸፋዊ እርምጃ በመውሰድ ውጊያው ተጀመረ፤ 18 ሰዎች ሞተዋል፡፡” ሲሉ ነዋሪው ኹኔታውን ገልጸዋል።

ከተገደሉት ነዋሪዎች መካከል ያልታጠቁ እና ሽማግሌ መሞታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የመንግሥት የጸጥታ ሀይሎች የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ ወታደሮች ጨምሮ ጣልቃ በመግባት ኹኔታውን ለመቆጣጠር ያደረጉት ጥረት ወደ ምሽት ላይ ተሳክቶላቸው አካባቢውን እንዳረጋጉት ነዋሪው አስታውቀዋል።

በወረዳው ከሚገኙ መንደሮች መካከል በሆነችው ቾኮርሶ መንደር ነዋሪ መሆናቸውን የገለጹትና ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሌላ ነዋሪ በእሁዱ ግጭት 18 ሰዎች መሞታቸውን ያረጋገጡ ሲሆን፤ ቁጥራቸው ያልታወቀ የሚሊሻ አባላት መገደላቸውን ገልጸዋል።

ነዋሪው፤ ታጣቂዎቹ ባለፉት ግዜያት ከአስር ግዜ በላይ ጥቃት መሰንዘራቸውንም አስታውሰዋል።

ከኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን አርቱማ ፈርሲ ወረዳ በሚዋሰነው በኤፍራታ እና ግድም ወረዳ በማጀቴ ከተማ ዙሪያ ባለፉት ግዜያት በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ሀይሎች መካከል ከፍተኛ ጦርነት ሲካሄድ መክረሙም ተገልጿል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here