5 ሚሊዮን ገበሬዎችን የሚያሳትፍ መርሐ ግብር ተግባራዊ ሊሆን ነው

0
600

በአነስተኛ የእርሻ መሬት ላይ የሚያርሱ ገበሬዎችን የሚያሳትፍ እና ምርቶቻቸውን በዘመናዊ መንገድ ማምረት እንዲችሉ የሚያደርግ የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር በቀጣይ አምስት ዓመታት ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገለፀ።

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ እንደገለጸው፤ የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር በግብርና ዘርፍ ገበያ መር በሆነ ኩታ ገጠም ዘዴ መልክዓ ምድራዊ ይዞታን መሰረት በማድረግ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችን በማዘመን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።

ከ2012 እስከ 2016 ባሉት አምስት ዓመታት ውስጥ የሚተገበረው ይህ የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር፣ በአራት ክልሎች ማለትም አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ እና ትግራይ በተመረጡ ሦስት መቶ ወረዳዎች የሚከናወን ነው። በዚህም ዐስር ምርቶች ትኩረት የተደረገባቸው ሲሆን፣ አምስቱ እህሎች ስንዴ፣ በቆሎ፣ የቢራ ገብስ፣ ሰሊጥና ጤፍ፤ የተቀሩት አምስት ደግሞ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት የሆኑት አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ማንጎ፣ ሽንኩት እና ቲማቲም መሆናቸውን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ በላከው መረጃ አሳውቋል።

በመርሃ ግብሩ ገበሬው ምርቱን በአግሮ-ፕሮሰሲንግ ፓርኮች ወደ ገበያ ትስስር ለማቅረብ የታሰበበት ነው። በአራቱ ክልሎችም የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በግንባታ ላይ ይገኛሉ ተብሏል።

የፓርኮቹ ግንባታ የተቀናጀ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ በአማራ ክልል ቡሬ፤ በትግራይ ባዕከር፤ በደቡብ ይርጋለም እና ኦሮሚያ ቡልቡላ አካባቢዎች እየተካሔዱ እንደሆነ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ለግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር መርሃ ግብሩ የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ የዴንማርክ ልማት ኮርፖሬሽን፤ የኔዘርላንድ ልማት ኮርፖሬሽን እና በአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ የሚደረግለት ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት መርሃ ግብሩን በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ተቆጣጣሪነትና በግብርና ሚኒስቴር መሪነት በቀጣይ አምስት ዓመታት ተግባራዊ እንደሚያደርገው ይጠበቃል።

ቅጽ 2 ቁጥር 56 ኅዳር 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here