280 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለመግዛት የወጣው ጨረታ ተከፈተ

0
357

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ በማሰብ በአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሚገዛው እና በተደጋጋሚ ሲራዘም የነበረው የ 200 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ እና ለሴፍቲ ኔት ፕሮጀክቶች የሚውል 80 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዢ ጨረታ ኅዳር 16/2012 በመንግሥት ንብረት ግዢ እና ማስወገድ አገልግሎት ተከፈተ።

በኹለቱም ጨረታዎች ላይ 13 የአገር ውስጥ እና የውጪ አገራት አቅራቢዎች የጨረታ ሰንድ በመግዛት የተሳተፉ ሲሆን፣ ተጫራቾች ያቀረቡትን መነሻ ዋጋ እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን በማጥናት አቅራቢ ድርጅቶች እንደሚለዩ ተገልጿል።

የጨረታዎቹ መክፈቻ ጊዜም ተጫራቾች ባቀረቧቸው ከማጓጓዣ ጋር በተያያዙ የማብራሪያ ጥያቄች ለሦስት ጊዜያት ሲሸጋገር መቆየቱ በጨረታው መክፈቻ ላይ ተገልጿል።

በተጨማሪም የመንግሥት ግዢ እና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ከ 240 ሺሕ ኪሎ ግራም በላይ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶችን በመሸጥ ከ 5 ሚሊዮን ብር ማግኘቱን አስታውቋል።

ብረታ ብረቶቹ ከአዲስ አባባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን እና የቤተ መንግሥት አስተዳደር ከተለያዩ ግንባታዎች ላይ በተረፈ ምርትነት የተወገዱ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን፣ ሕጋዊ ጨረታ በማውጣት ለገበያ መቅረባቸውን አገልግሎቱ ገልጿል።

ከዚህ ቀደም የብረታ ብረት እና መሰል የግንባታ ግብዓቶች ትኩረት እንደማይደረግባቸው እና ለስርቆት ሲዳረጉ እንደቆዩ የተገለጸ ሲሆን፣ አገልግሎቱ ከተቋማት ጋር በመሆን በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ከሚደረጉ ግንባታዎች የሚገኙ ተረፈ ምርቶችን በሕጋዊ ጨረታ ለገበያ በማቅረብ ገቢ የሚያስገኙበትን መንገድ እያመቻቸ እንደሆነ ተገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 56 ኅዳር 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here