የአዲስ አበባና የመቀሌ መንግሥቶቻችን ፉክክር!

0
892

አዲስ አበባ እንዲሁም መቀሌ ላይ የተከናወኑ ስብሰባዎች በየበኩላቸው ኢትዮጵያን ለማዳን ቆመና ሲሉ ተሰምተዋል፤ የአዲስ አበባው ብልጽግና ፓርቲን በማጽደቅ፣ የመቀሌው በአንጻሩ በመቆምና በመተቸት። ይህን ክስተት መነሻ በማድረግ ሐሳባቸውን ያጋሩት ግዛቸው አበበ፤ በኹለቱ ስብሰባዎች መካከል ስላሉ መመሳሰሎችና ልዩነቶች የተለያዩ ነጥቦችን አንስተዋል። እንዲሁም ኹለቱንም እያንዳንዳቸውን በሰላ ምልከታ ተችተዋል። የኹለቱን ስብሰባዎች ጉዞም ለወደፊቱ ምን ሊያመጣ ይችላል የሚለው ላይም ምልከታቸውን አጋርተዋል።

አዲስ አበባ እና መቀሌ ላይ ጩኸት በርክቷል። በኹለቱ ከተሞች ኢትዮጵያን ለማዳን ቆመናል የሚሉ ወገኖች በየፊናቸው ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል። አንዱ ሌላውን አጥፊ አድርጎ በመሳል እያንዳንዳቸው ራሳቸውን የኢትዮጵያ፣ የፌዴራሊዝምና የዴሞክራሲ ጠበቃ አድርጎ ለማሳየት ላይ ታች ሲሉ ይስተዋላል። የመቀሌና የአዲሰ አበባው ቡድኖች እስከ 2010 ድረስ ጌታና ሎሌ ሆነው አገርንና ሕዝብን ችግር ላይ ሲጥሉ የነበሩ ቡድኖች ናቸው። አሁን ደግሞ ኹለቱም ራሳቸውን ለአገርና ለሕዝብ ተቆርቋሪዎች አድርገው ለማሳየት በእጅጉ እየደከሙ ይገኛሉ። አንዳንዴም በሚያሳፍር ደረጃ ወርደው ራሳቸውን ሲክቡና ሌላውን ሲዘረጥጡ እየሰማን እያፈርን ነው።
ኹለቱ ቡድኖች ያለ ስምምነት አገሪቱን ከኹለት ከፍለው እየገዟት መሆኑ አጠራጣሪ አይደለም። የአዲስ አበባው ቡድን በትግራይ ላይ፣ የመቀሌው ቡድን በቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል ላይ ሥልጣን የለውም። የመቀሌው ቡድን የቆየ ልምድና ተሞክሮውን በመጠቀም እጆቹን በስውርና በግልጽ ወደ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል እየሰደደ መሆኑ በገሃድ የሚታይ ሲሆን፣ የአዲስ አበባው ቡድን ግን በትግራይ ውስጥ በሚካሔዱ ጉዳዮች ላይ ያለው ሥልጣን ዜሮ ነው ማለት ይቻላል።

የመቀሌና የአዲስ አበባ ቡድኖች መሪዎች በየከተሞቻቸው እያፏጩና እያጨበጨቡ የሚያሟሙቋቸውን ሰዎች እየሰበሰቡ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ አጋጣሚዎችን በመጠቀም እየተወራረፉ ነው። ውስኪ ጨላጮች፣ ሌቦች፣ አፋኞች፣ ኋላ ቀሮች ወዘተ…. በአደባባይ ከተወራወሯቸው ስድቦች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። በእርግጥ በሕወሐት/ኢሕአዴግ ስርዓት ውስጥ እንደ ጤንነታቸው ሁኔታ ወይም እንደየ እምነታቻው ወይም በሌላ ምክንያት ወተትም ውስኪም የሚጠጡ ሰዎች የሚገኙበት ስርዓት መሆኑ የግድ መሆን ያለበት ጉዳይ ነው።

ስርዓቱ ከመላእክት ማኅበር በመጡ ፍጡራን የተሞላ አይደለምና በሐይማኖት መጽሐፍት ላይ የተደነገጉ ሕግጋትን በሚያከብሩ ጻድቃን የተሞላ ሕወሐት/ኢሕአዴግ መኖር ነበረበት ብሎ ድርቅ የሚል ሰው ሊኖር አይገባም። ሕዝብን እያስመረረ የነበረው ነገር ማን ወተት ጠጣ ወይም ማን ውስኪ ተጎነጨ የሚለው ጉዳይ ሳይሆንኅ ስርዓቱ ደም በጠማቸው አረመኔዎች የተሞላ ስርዓት መሆኑ ነው። አሁን ሕዝብን የሚያሳስበው ጉዳይም የእነዚሁ ወገኖች የበላይነት ተመልሶ መምጣቱ፣ የቀድሞ ሥራቸውና ማንነታቸው የተረሳ ይመስል ራሳቸውን መልአክ አስመስለው እየገለጹ ሥልጣንን የመናጠቅ ዓይነት ግብግብ ውስጥ ገብተው መታየታቸው ነው።

በዚሁ ሳምንት አጋማሽ ላይ የመቀሌው ቡድን ከ50 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ከመላ አገሪቱ የተውጣጡ የወጣት ኢ-መደበኛ አደረጃጀት ተወካዮችን ወዘተ….. ሰብስቦ አገርን ከመፈራስ፣ ሕገ-መንግሥትን ከመረገጥ እናድን እያለ ሲሆን፣ የአዲስ አበባው ቡድን ደግሞ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ በሕወሐት የተፈጠሩትንና አባል እና አጋር ብሎ ፈርጆ ሕወሐት ሲጠቀምባቸው የነበሩ ፓርቲዎችን ሰብስቦ አንድ ወጥ የፖለቲካ ፓርቲ ለመሥራት አገርን አበለጽጋለሁ እያለ ነው። የመቀሌው ቡድን ከ2011 ጀምሮ ማካሔድ በጀመረው አገር ዐቀፍና ዓለም ዐቀፍ ስብሰባ ‘ባለ አደራ መንግሥት’ የመመስረት ዝንባሌ እያሳየ መሆኑ ግልጽ ሊሆን ይገባል።

ይህ ካልተሳካ ደግሞ አንድን መንግሥት መንግሥት ነው የሚያስብሉትን የኢኮኖሚ፣ የደኅንነት፣ የምርምር ወዘተ… ተቋማት ያሟላ ‘የትግራይ ዲፋክቶ መንግሥት’ የሚል አማራጭ በጠረጴዛው ላይ አስቀምጧል። በመላ አገሪቱ በተካሔዱ ምርጫዎች በመቀለድና ድራማ በመስራት የሚታወቀው የመቀሌው ቡድን፣ ምርጫ 2012 በውድም ሆነ በግድ፣ በመላ ኢትዮጵያ ካልሆነም በትግራይ ብቻ መካሔዱ የማይቀር መሆኑን በተደጋጋሚ አሳውቋል። የመቀሌው ቡድን በመላ አገሪቱ የተፈጠረው ድፍርስ ሳይጠራና የእሱ ተጽዕኖ የማሳደር አቅም ሳይዳከም ምርጫ እንዲካሔድ በመወትወት ሳይገታ ፌዴራሊስት የሚላቸውን ኀይሎች አሰባስቦ ከፍተኛ የምክር ቤት ወንበሮችን በማግኘት ወደ አዲስ አበባው ሥልጣን ተመልሶ ለመምጣትም ከፍተኛ ሥራዎችን እየሠራ ነው።

መቀሌ ላይ ከሚሰባሰቡት፣ የፖለቲካ ቡድን ከሚባሉት ጥቂት የማይባሉት በሕዝብ ላይ ቀርቶ በገዛ ቤተሰቦቻቸውና በቤተ-ዘመዶቻቸው ላይ እንኳ ተጽዕኖ የማሳደር ኀይልም ሆነ ብቃት የሌላቸው ሲሆኑ፣ አንዳንዶቹ ቡድኖች ግን ሕወሐት በሚፈትለው ሴራ ሕዝባቸውን ከሌላ ሕዝብ ጋር እያጋጩ፣ ሕወሐት ሆነ ብሎ እንዲቆሰቆስ በሚያደርገው እሳት ሕዝባቸውን እያስጠበሱ፣ መልሰው ደግሞ ሕዝባቸው ሕወሐትን እንደ ብቸና አዳኝ፣ ተቆርቋሪና ጠበቃ አድርጎ እንዲያይ በርትተው የሚሠሩ ቅጥረኛ ቡድኖች ናቸው። የመቀሌው ቡድን አካሔድ በዝምታ ቁጭ ብሎ ከታየ አደጋው ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል።

በዚህ ረገድ የመቀሌው ቡድን የቀድሞ ተለጣፊዎቹን ብቻ ሳይሆን ቀድሞ የኢሕአዴግ አባል እና አጋር ብሎ በፈረጃቸው ድርጅቶች ውስጥ ያሉ የቀድሞ አገልጋዮቹን በደካማ ጎናቸው እየገባ ወይም እየደለለ በአሻንጉሊትነት ሊጠቀምባቸው ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑ ከአፈትላኪ ወሬዎች መረዳት ይቻላል። ሕወሐት ስለ ሕዝብ ድምጽ እና ስለ ምርጫ የሚጨነቅ፣ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት የሚያስብ፣ ስለ ሰብዓዊ መብትና ስለ ዴሞክራሲ የሚቆረቆር፣ ስለ ወጣቶች መጻዒ ተስፋ እንቅልፍ አልባ ሆኖ የሚሠራ ድርጅት ነው ብለው በግላቸውም ተጋብዘውም ሆነ ቡድናቸውን ወክለው መቀሌ ላይ የሚሰበሰቡ ወገኖች ከየስብሰባቸው በኋላ ስለ ስብሰባው የሚያነጋግራቸው፣ በሕወሐት ላይ እንዴት እምነት እንዳሳደሩና ከሕወሐት ጋር አብረው ምን ለመሥራት እንደሚያስቡ የሚጠይቃቸው ጋዜጠኛና ሚዲያ አለመኖሩ ሕዝብን ግራ የሚያጋባ ጉዳይ እየሆነ ነው።

የአዲስ አበባው ቡድን ኦሕዴድ/ኦዴፓ፣ ብአዴን/አዴፓ፣ ደኢሕዴን፣ ኢሶሕዴፓ/ሶዴፓ፣ ሐብሊ፣ ጋሕዴን፣ ቤጉሕዴፓ፣ አፍዴፓ…. በየፊናቸው ባካሔዱት ስብሰባ ራሳቸውን አክስመው ብልጽግና ወደ ተባለው ፓርቲ ለመዋሃድ ሙሉ በሙሉ መስማማታቸውን ነግሮናል። አዎ! ሙሉ በሙሉ ተስማምተዋል ተብሏል።
አባል እና አጋር የሚባሉት እነዚህ ድርጅቶች ከሕዝባቸው ይልቅ የፈጣሪያቸው የሕወሐት አገልጋዮች ሆነው የኖሩበት ጊዜ ማክተሙንና ከዚህ በኋላ ሕወሐት እንዳሻው እንደማያሾራቸው (እንደማይዘውራቸው) መስማማታቸውን ሊነግሩን እየሞከሩ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በሌላ ጌታ እግር ስር ወድቀው ሙሉ በሙሉ እየተስማሙ ለሕዝባቸው መቅሰፍቶች ሆነው የሚቀጥሉ ላለመሆናቸው ምንም ዓይነት ማስረጃ ማቅረብ አይችሉም።

እንዲያውም እነዚህ 8 ድርጅቶች በተናጠል ለመፍረስና ወደ ብልጽግና ፓርቲ ለመደመር ሲስማሙ አንድም የተዓቅቦ፣ አንድም የተቃውሞ ድምጽ አለማሰማታቸው የሂደቱን ዴሞክራሲያዊነት አጠያያቂ የሚያደርግ ነው። በብልጽግና ፓርቲ አስማታዊ ኀይል አስተሳሰባቸው ተሰልቦ ወይም አንዳች ኀይል/መንፈስ ነገር ወርዶባቸውና በዚያ መንፈስ/ኀይል ተነድተው ነው እጃቸውን ያወጡት ተብሎ ካልተመካኘ በስተቀር፣ በጤናቸው እያሉ በአንድ ሐሳብ ላይ ተቸክለው ያለ አንዳች ልዩነት ተስማሙ መባሉ ደግ ምልክት አይደለም።

ቀድሞውንም ቢሆን እነዚህ ድርጅቶች ለሕወሐት-በሕወሐት የተፈጠሩ፣ በውስጣቸው የሚሰገስጓቸው ግለሰቦችም ሕወሐትን በማገልገል የየግል ጥቅማቸውን እያሳደዱ ለመኖር ቆርጠው የተነሱ ናቸው። እናም የአሁኑን ውሳኔ ሲወስኑ ግለሰቦቹ የየግል መጻዒ መልካም ዕድላቸውን መወሰናቸው ነው ወይስ እንወክለዋለን ለሚሉት ሕዝብ አንዳች ፋይዳ ያለው ሥራ ለመሥራት ቆራጥነታቸውን ማሳየታቸው ብሎ መጠየቅ በጣም ተገቢ ጉዳይ ነው።

በነዚህ ድርጅቶች ወስጥ በተለይም በከፍተኛ የአመራር ቦታዎች ላይ ከተኮፈሱት ግለሰቦች በጣም ብዙዎቹ ከታዳጊነት እስከ ጎልማሳነት ወይም ከጎረምሳነት እስከ ሽምግልና የሚዘረጋ ዕድሜአቸውን በእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ የቆዩ ናቸው፣ አንዳንዶቹም ከእነዚህ አባልና አጋር ድርጅቶቹ ምሥረታ ጀምሮ የቆዩና የፖለቲካ ዕድሜአቸው ከድርጅቱ ዕድሜ ጋር እኩል የሆነ ነው። ወሎ፣ አዲስ አበባ ወዘተ… ከሚገኙ ሕወሐት ሠራሽ አንደኛና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅን በመሳሰሉ ሌሎች የአገር ቤትና የውጭ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አማካኝነትም እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ያላቸው ለመሆን በቅተዋል።

ከእነዚህ ሰዎች በጣም ብዙዎቹ ለሌላ ሥራ ቦታ የማይመጥኑ፣ በፖለቲካ ባለሥልጣንነት ተቀምጠው ለማገልገል ብቻ እንደተሠሩ ሮቦቶች ዓይነት ናቸው፤ ጥርስ የነቀሉበት የኢሕአዴግ አባል/አጋር ፓርቲ ሞቶ ቀብሩ ሲደርስ ራሳቸውን መሄጃ ያጡ ፍጡራን አድርገው ማየታቸው የግድ ነው። ታዲያ ይህ ይሆን ተደጋጋሚውን “ሙሉ-በሙሉ ተስማሙ” የሚለውን ዜና ያስከተለው? የሶዴፓውን አቶ ሙስጠፌን የመሳሰሉ በለውጡ ማግስት ወደ ፖለቲካ ድርጅቶቹ የገቡ ሰዎች የሚመሩት ቡድን በምን ሂሳብ ነው ሙሉ በሙሉ የሚለውን ጨዋታ የተቀላቀለው የሚለው ጥያቄም መልስ የሚያሻው ይመስላል።

ከአባል ወይም ከአጋር ድርጅቶቹ አንዱ ከነ ጭራሹ ወደ ብልጽግና ፓርቲ ላለመግባት በአብላጫ ድምጽ ሊወስን ይችላል ብሎ መገመት አዳጋች ቢሆንም፣ ጥቂት ወይም ብዙ ድምጸ-ተዓቅቦ ወይም ጥቂትም ሆነ ብዙ የተቃውሞ ድምጽ ቢኖር ምን ችግር ወይም ምን ለውጥ ስለሚያስከትል ነው ስምንቱ ፓርቲዎች በሙሉ ድምጽ ውህደቱን ያጸደቁት?

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹መደመር›› የተባለ መጽሐፋቸውን ሲያስመርቁና በብልጽግና ፓርቲ የስምምነት ፊርማ ስነ-ስርዓት ላይ ያደረጉት ንግግር የአሸማቃቂነት ባህሪ ነበረው ማለት ይቻላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብልጽግና ፓርቲን የሚቃወሙ ወገኖች ሌቦች ናቸው ሲሉ ወርፈዋል። በፓርቲው ሰነድ ላይ ሌብነትን የሚኮንን ሐሳብ ስለሰፈረ፣ መስረቅ ስለማይቻል ወደ ብልጽግና ፓርቲ አንገባም ብለው ያመጹ ወገኖች እንዲኖሩ አድርጓል ሲሉ በግልጽ ነቆራቸውን አሰምተዋል። በዘረፉት ገንዘብ በአገር ቤትና በውጭ ሕንጻዎችን የገነቡ፣ ለምንም ደንታ ቢስ ሆነው የሚበሉና የሚጠጡ ወዘተ… የሚሉና የመሳሰሉ አሸማቃቂ ነቆራዎችን ከአንድ መሪ በማይጠበቅ ሁኔታ አስተጋብተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጨባጭ መረጃና ማስረጃ ካላቸው የተዘረፈ የአገር ሃብትን ለማስመለስ መሥራት ሲገባቸው፣ ዘራፊዎች የሚሏቸው ሰዎች በባለ ኮከብ ሆቴሎች ውስጥ እየተመገቡና እየተኙ በመቀናጣት ላይ መሆናቸውን መናገራቸው የእርሳቸውንና የጠቅላላ መንግሥታቸውን ደካማነትና ዓቅመ ቢስነት በተዘዋዋሪ ማሳወቃቸው መሆኑን ሊረዱት በተገባ ነበረ። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር እያፏጩና እየጮኹ ከመቀመጫቸው እየተነሱ የቧረቁ ግለሰቦችም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ደካማነት ጮቤ እየረገጡ መሆኑን ሊያውቁት ይገባል። እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው። ‘…ይህን መሰሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ የሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ነቆራ፣ ማስፈራሪያና ማሸማቀቂያ ወደ ብልጽግና ፓርቲ ለመዋሃድ ሲባል በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ ሚና አልነበረውምን?..’

ቆየት ባለው ጊዜ፣ በሕወሐትም ሆነ በኢሕአዴግ ስብሰባዎች ላይ፣ የሐሳብ ልዩነት ሲነሳና ክርክር ሲበዛ በየሰኮንዱ የአቶ መለስን አዝማሚያ እያዩ ሐሳብ መስጠት፣ የተለየ ሐሳብን በሆድ መቅበርና በመጨረሻም አቶ መለስን ተከትሎ ድምጽ መስጠት የተለመደ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ማዕከላዊነትን መጠበቂያ ዘዴ ነበረ። ይህን አሠራር በመጣስ የተቃውሞ ድምጽ መስጠት ቀርቶ ድምጸ-ተዓቅቦ ማድረግ በጣም አስፈሪ ነገር ይሆናል።

በአንድ ወቅት አንድ የውጭ ጋዜጠኛ አቶ መለስን በኢትዮጵያው ፓርላማ ኢሕአዴጋውኑና አጋሮቹ ለምን በአንድ ላይ አጃቸውን እያወጡ ድምጽ እንደሚሰጡ ማብራሪያ ጠይቋቸው ነበረ። አቶ መለስ ይህ የሚሆነው ድርጅታቸው ተነጋግሮና ተመካክሮ ወደ ስብሰባዎች የመግባት ባህል ስላለው ልዩነት እንዳይኖር ስለሚደርግ ነው የሚል መልስ ነበር የሰጡት። ነገር ግን የምክር ቤቱ አባላት ቀደም ብለው ተሰባስበው የመመካከርና የመነጋገር ልምድ እንደሌላቸው፣ በዚያው በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ የአቶ መለስን ገጽታ በማየትና በየጉዳዩ ላይ አቶ መለስ ሐሳብ ሲሰነዝሩና መልስ ሲሰጡ ጥቅም ላይ የዋለውን የድምጻቸውን ኀይልና ቃና በንቃት በመከታተል ብቻ እጅ የሚመዠረጥበት አሰራር ሰፍኖ መኖሩ ግልጽ ነበረ። ወደ ብልጽግና ፓርቲ የሚደረገው ጉዞስ የዚህ ዓይነት አንዱን አይቶ በመንጋ የመግተልተል አካሔድን እያሳየን ይሆን?

ፓርቲዎቹን አባልና አጋር ብሎ ከፋፍሎ ድራማ መሥራቱ ቀድሞውንም ቢሆን ምንም ዓይነት ምክንያታዊነት ያልነበረውና ሁሉንም ክልሎች ወክሎ የሚቆም፣ በሁሉም ክልሎች የሚንቀሳቀስና የተሻሉ አመራሮችን ከሁሉም ብሔረሰቦች አውጣጥቶ አገርን ማስተዳደር የሚችል ፓርቲ ማዋቀሩ ተቀባይነት ያለውና ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም፣ የሕወሐት/ኢሕአዴግ ዘመን ሹማምንት እርስ በእርስ እየተስማሙ በገዥነት የሚቀጥሉበትን መንገድ በማመቻቸት ላይ ያሉ በሚመስል አካሔድ ብልጽግና የተባለው ፓርቲ መዋቀሩ ግን ከተስፋ ይልቅ ጥርጣሬን የሚያጭር ነው።

ይህ ሙሉ በሙሉ ተስማምቶ የመጓዝ ነገር 2007 የሆነውን ነገር የሚያስታውስ ነው። የኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች የሙሉ በሙሉ ድምጽ ማሸነፍ ጨዋታ እመርታዊ ዕድገት አሳይቶ ጣራ የነካው በምርጫ 2007 ነው ማለት ይቻላል። እነዚህ ስምንት ቡድኖች፣ አሁን ራሱን ባገለለው ሕወሐት እየተመሩ በምርጫ 2007 ሙሉ በሙሉ ተስማተው የክልልና የፌዴራል ምክር ቤት ወንበሮችን በሙሉ የዘረፉ መሆኑ አይረሳምና፣ በምርጫ 2012 ወይም በቀጣዩ ምርጫ እነዚህ ቡድኖች በብልጽግና ፓርቲ ስም ምን ይሠሩ ይሆን ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። የ2007ቱ ሕሊና ቢስነት ከ2008 ጀምሮ የታየውን መጠነ ሰፊ ሕዝባዊ ተቃውሞ መቀስቀሱም የሚዘነጋ አይደለም።

ሕወሐት በአባል ይሁን በአጋር ፓርቲዎቹ ላይ የበላይነቱን ለማስቀጠልና እነሱን እንደ መሣሪያ እየተጠቀመ ሁለ-ገብ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ‘…ለኢሕአዴግ/ሕወሐት ታማኝ ይሁኑ እንጅ ለዘበኝነት የማይመጥኑትንም ቢሆን ሚኒስትር አደርጋለሁ’ በሚለው መፈክሩ የሾማቸው ሰዎች አሁንም በፌዴራልና በየክልሉ በሥልጣን ላይ ያሉ መሆኑ፣ እነሱው የቀድሞ ቡድናቸውን አፍርሰው የብልጽግና ፓርቲ አዋቃሪና መሪ መሆናቸው ወዘተ…. ሲታሰብ ቀጣዩ ጊዜ የብልጽግና ዘመን መሆኑን በጥርጣሬ እንዲታይ የሚደርግ ነው።

አሁን እንኳ በመላ አገሪቱ በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች መንግሥት የለም በሚያስብል ደረጃ ችግሮች በመከሰት ላይ ያሉት በአብዛኛው በአመራር ብቃት ችግር መሆኑ የታወቀ ነው። ከዚህ ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ዓመት በእግር ኳስ ሜዳዎች ችግሮች ሲበራከቱ ስፖርቱን አቆመዋለሁ ብለው መዛታቸውና በዚህ ዓመት ዩንቨርሲቲዎች ሲበጠበጡ ትምህርቱን አቆመዋለሁ ብለው ማስፈራራታቸው በፌዴራል ደረጃም ቢሆን፣ ተስፋ የሚጣልበት አመራር መኖሩን አጠራጣሪ የሚያደርግ ነው። ታዲያ ብልጽግና ፓርቲ በእነዚሁ ሰዎች እየተመራ፣ አገሪቱም በነዚሁ ሰዎች እየተመራች ሰላማዊና የበለጸገች መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

ግዛቸው አበበ መምህር ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው gizachewabe@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here