ምላሽ የናፈቀው የብሔር ጥያቄ

0
1275

የፊታችን ሰኞ፣ ኅዳር 29 የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ታስቦ/ተከብሮ ይውላል። ዋለልኝ መኮንን የብሔር ጥያቄን በይፋ ካነሳም ግማሽ ምዕተ ዓመታት ማስቆጠሩን መነሻ በማድረግ በቅርቡ በሸራተን ሆቴል ውይይት መደረጉ ይታወሰል፤ ምንም እንኳን ከዛ በፊት አንዳንድ የብሔር እንቅስቃሴዎች በተደራጀ መልኩ ይደረጉ እንደነበር ቢነገርም። እነዚህን ኹለት ሁነቶች መነሻነት በማድረግ የታሪክ መዛግብትን በማገላበጥ እና ይመለከታቸዋል የተባሉ ግለሰቦችን በማነጋገር፣ የብሔር ጥያቄ ዳራ በኢትዮጵያ ምን ይመስላል፤ በአሁኑ ወቅትስ የሚነሱ የብሔር ጥያቄዎች ምንድን ናቸው፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከብሔር ጥያቄ ጋር በማገናኘት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አገሪቷን ለሰላም እጦትና ሕዝቦቿን ለግጭት እየዳረጉ የአገር ህልውናን እየተፈታተኑ መሆናቸውን በማጣቃስ፣ መፍትሔው ምን ሊሆን ይገባል ስትል የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጉዳዩን የሐተታ ዘማለዳ ርዕስ አድርጋዋለች።

መንደርደሪያ
ኅዳር 8/ 1962 በዋለልኝ መኮንን የተዘጋጀች በአምስት ገጽ የተቀነበበች ጽሑፍ መደበኛ በሆነና በተቀናጀ መልኩ የብሔር ጥያቄን ለብዙኀኑ አሰማች። በወቅቱ በተመሳሳይ ከተነሱና መሬት ለአራሹ፣ የአስገባሪ ስርዓት ይፍረስ ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች አንጻራዊ መልስ ያገኙ ቢሆንም፤ የብሔር ጥያቄ ያለመልስ እድሜው ቀጠለ። ያኔ የተነሳው ጥያቄም ዛሬ ድረስ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ ሆኖ ዘለቀ።

የጥያቄው መነሳት በአንድ በኩል ለግጭቶች መበራከት ሰበብ እንደሆነ የሚናገሩ ጥቂቶች አይደሉም። ‹‹ሕዝቡ አንድነትን መርጦና ተቀብሎ በሰላም እየኖረ ነበር፣ ያስቸግር የነበረውም አንዱ ጨቋኝ ሌላው ተጨቋኝ የሆነበት የመደብ ልዩነት እንጂ የብሔር ጉዳይ አይደለም። በዛ ጥያቄ [በዋለልኝ] ምክንያት ግን በብሔሮች መካከል ግጭት ሊፈጠርና ለየብሔሩ ነጻ አውጪ ሊፈጠር ችሏል›› የሚሉ አሉ። በአንጻሩ ደግሞ ጥያቄውን የሚደግፉና ‹‹የመደብ ትግሉ በብሔሮች መካከል ነበር፤ በጭቆናና በግድ ታፍኖ ነው እንጂ ሰው ዝም ያለው ጥያቄው የሕዝብ ነው። ሕዝቡ የብሔር ጥያቄ ነበረው›› የሚሉም ነበሩ።

ያም ሆነ ይህ ለዚህ ጥያቄ ተገቢ መልስ ባለመገኘቱ ወይም ባለመሰጠቱ ምክንያት፤ ዛሬም ድረስ በጉዳዩ ላይ ክርክር፣ ውይይት እንዲሁም ንትርክ ይሰማል፤ የአገሪቱን አቅጣጫ እና መንገድም አስቀይሯል ማለት ይቻላል።

የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንጉሣዊ አስተዳደር፣ የደርጉ ኀይልም ሆነ ሕወሓት መሩ ኢሕአዴግ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሳይሰጡ ቆይተዋል። ጥያቄው አሁንም ቀጥሎ ይመጣል ተብሎ ለሚጠበቀውና ምርጫን ለሚጠብቀው የብልጽግና ፓርቲ ‹‹መደመር›› ፍልስፍና ፈተና ሆኖ መቆየቱ አይቀሬ እንደሆነ ብዙዎች ሲናገሩ ይሰማል።

ጥያቄው ምን ነበር?
ዋለልኝ በአምስት ገጽ ጽሑፉ መጀመሪያ ላይ የጽሑፉ ዓላማ ‹‹ውይይት ማጫር›› የሚል ቃል የሰፈረ ሲሆን፣ ‹‹ጽሑፉ ለልዩ ክብረ በዓል የተዘጋጀ በመሆኑ በጥቅል ብያኔ የተሞላ ነው›› የሚል ሐረግ አክሎበታል። እንዲሁም ‹‹አንባብያን ሐረጋትን ከዓውዳቸው ውጪ እየነጠሉ ከማጋነን አዝማሚያ እንደሚቆጠቡ ተስፋ አደርጋለሁ›› ሲልም ስሜቱን ገልጿል። ይህ በጸሐፊው ጥልቅ ትንታኔ ያልተሰጠውና በ‹‹ጥቅል ብያኔ›› የተሞላ አምስት ገጽ ጽሑፍ የብሔር ጥያቄ እይታዎችን ያሰፋ እንደሆነ ግን ይታመናል።

በዓቢዩ ብርሌ በተዘጋጀውና ‹‹በሀገር ፍቅር ጉዞ›› በተሰኘው መጽሐፍ ላይ፤ ጸሐፊው በወቅቱ ማለትም ዋለልኝ ጥያቄውን ባነሳበት ጊዜ የነበረውን ሁኔታ እንደሚከተለው አኑሮታል፤ (ገጽ 272) ‹‹የዋለልኝ የብሔር ጥያቄ ጽሑፍ የተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን የኃይለ ሥላሴን መንግሥትና የሕዝቡንም ቀልብ ወዲያው ነው የሳበው። ይህም የሆነበት ዋናው ምክንያት ምናልባትም በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሕሊና የተቀረጸውንና የልብ ትርታ የሚቀሰቅሰውን መሠረታዊ እምነት፣ የአገሪቱን ማንነት ማለትም ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› ወይም ‹‹ብሔራዊ ስሜት›› ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ‹‹በብሔር ጥያቄ›› ሥም ጥርጣሬና ጥያቄ ውስጥ በማስገባቱ ነው። ያም ብቻ አይደለም፤ ለዚህ ድንገተኛና ከባድ ጥያቄ ዋለልኝ ራሱ በድፍረት መልስ ለመስጠት መሞከሩ ነበር፤ ጽሑፉን በተማሪዎች ትግል ሒደት ውስጥ ልዩና ታሪካዊ ሊያደርገውና የኃይለሥላሴን መንግሥትም ሆነ ሕዝብ ሊያስደነግጥ የቻለው›› ይላል።

በወቅቱ ቀርበው ከነበሩ ጥያቄዎች መካከል ይህኛው ጥያቄ በጊዜው የነበረውን ሕዝብ ጠያቂ አድርጎታል። ‹‹ቋንቋና ብሔርተኝነት›› የተሰኘው መጽሐፍ አዘጋጅ ሑሴን አዳል (ዶ/ር) በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ‹‹ከዋለልኝ መኮንን ወቀሳ በስተጀርባ ያለ እውነታ›› በሚል ርዕስ ባስነበቡት ጽሑፍ ተከታዩን ይላሉ፤
‹‹እርግጥ ዋለልኝ መኮንንን ጨምሮ በቀድሞ ተማሪዎች በኩል፣ በብሔር/ብሔረሰብ ጽንሰ ሐሳብ ዙሪያ የጠራ ግንዛቤ አለመያዙ ትልቅ ክፍተት ነበር። ትግሉ በአመዛኙ በተማሪዎች ይመራ ስለነበር ይህ ችግር ማጋጠሙ አያስደንቅም። ተማሪዎቹ “ብሔር”፤ “ብሔረሰብ” የሚባሉትን ኹለት ቃላት ላይና ታች እያፈራረቁ፣ ተመሳሳይ ሁኔታን ለመግለጽ ይጠቀሙ እንደነበር፣ ዋለልኝ መኮንን “ታገል” መጽሔት ላይ ባሰፈረው “የብሔር ትግል በኢትዮጵያ” የሚለው ጽሑፍ ላይ መመልከት ይቻላል።››

ታድያ ግን ተማሪዎቹ ቃላቱን በማፈራረቅ በመጠቀም፣ ጽንሰሐሳቡን ጥርት ባለ ሁኔታ ያልተረዱ ቢሆንም፤ በወቅቱ ትግል የሚጠይቅ የሕዝቦች እኩልነት መጓደል በኢትዮጵያ ነበር ይላሉ፤ ሑሴን። የዋለልኝ ጥያቄ ዋና ፍሬ ነገርም “ኢትዮጵያ የአንድ ብሔር/ብሔረሰብ አገር ብቻ አይደለችም” የሚል ነው ሲሉ ያክላሉ።

ከዋለልኝ የብሔር ጥያቄ በፊት
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በታሪክ ረዳት ፕሮፌሰር ማርሸት ግርማይ፤ ዋለልኝ ባቀረበበት መልኩ በተቀናጀ መንገድ ተጽፎ የሚገኝና የተመዘገበ አይሁን እንጂ፤ እንደ ማኅበረሰብ ሰዎች የራሳቸውን ማኅበርና አደረጃጀት አቋቁመው መብታቸውን ይጠይቁ እንደነበር ታሪክ ያስረዳናል ይላሉ። ይህም በተወሰነ የኢትዮጵያ ክፍል ብቻ ሳይሆን በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል፤ ሰሜኑንም ጨምሮ የሕዝብ ጥያቄዎች ነበሩ ሲሉ ያወሳሉ።

ማርሸት በበኩላቸው ጥያቄው መሠረቱ የኢኮኖሚ ጉዳይ እንደነበር ይጠቅሳሉ። ከዛም በተጓዳኝ በወቅቱ የነበረው የፊውዳል ስርዓት በእኩል ደረጃ ባይሆንም በሁሉም አቅጣጫ ተጽዕኖ ነበረው። ‹‹የመሬት ስሪቱ ወደ ሰሜኑ ክፍል ሲታይ ለመሬት የቀረበ ሲያደርገው በደቡብ የጭሰኛ እና የባላባት ግንኙነት የሻከረ በመሆኑ፤ በወቅቱ ትልቁ ጉዳይ የመሬት ጉዳይ ስለሆነም ጭምር፤ የኢኮኖሚ ጫናው የሚያመጣቸው ተቃውሞዎች ነበሩ›› ብለዋል። እነዛም ሥር እየሰደዱ የኢኮኖሚ ጥያቄዎችም ወደ ፖለቲካ አጀንዳነት እየተቀየሩ መጡ።

‹‹እንጂ በወቅቱ የቋንቋ ወይም የሃይማኖት ተጽእኖ ስለነበር ነው የሚል አመለካከት የለኝም። የታወጀ ነገርም አልነበረም።›› የሚሉት ማርሸት፤ ምናልባት ወደ መሬት ሲወርድ ችግር ሊኖር ይችላል እንጂ በጊዜው በቋንቋና ሃይማኖት ምክንያት የተገፋ አለ ብለው እንደማያምኑ ጠቅሰዋል።

መምህር ገብረኪዳን ደስታ ጡረታ እስከወጡበት ጊዜ ድረስ በመምህርነት ያገለገሉና ‹‹አጼ ዩሐንስ እና አጼ ቴዎድሮስ በታሪክ መነጽር›› የተሰኘው መጽሐፍ ጨምሮ የተለያዩ ታሪክ ቀመስ ሥራዎችን ለአንባብያን ያደረሱ የ82 ዓመት አዛውንት ናቸው። ከዋለልኝ መኮንን ጋር በትምህርት ቆይታ እንዲሁም በሥራ አጋጣሚ በቅርብ እንደሚተዋወቁ የሚያስታውሱት ገብረኪዳን፣ ‹‹ሐቅን መዋጥ ስለሚያቅተን እንጂ ዋለልኝ አንድ ሰው ነው። በእርሱ ሥም ወጣ እንጂ ጥያቄው የእርሱ ሳይሆን የጠቅላላ ኅብረተሰብ ነው። እኔ ብናገር የምናገረው የማኅበረሰብ ነጸብራቅ እንጂ የራሴ ሊኖረኝ አይችልም›› ሲሉ ያወሳሉ። በዚህም ዋለልኝ ጥያቄውን በመደበኛ መንገድ ሳያነሳው በፊትም በሕዝብ በኩል የተነሳ እንደነበር ይጠቅሳሉ፤ ትግል የአንድ ሰው ብቻ ሊሆን እንደማይችል አጽንኦት በመስጠት።

ዓለማየሁ አረዳ (ዶ/ር) ደግሞ ‹‹ምሁሩ›› በተሰኘ መጽሐፋቸው (2010)፣ የዋለልኝ ጥያቄ ተማሪው አስቀድሞ ስለ ብሔርና በኢትዮጵያ ስለነበረው የብሔሮች ፖለቲካዊ ተዛምዶ የተለየ ግንዛቤ እንዲይዝ አድርጎታል የሚል አመለካከት እንዳላቸው ገልጸዋል። በጊዜው የሆነውንም እንደሚከተለው በመጽሐፋቸው አስፍረውታል፤ (ገጽ 75)

‹‹ያንን ጽሑፍ [የዋለልኝን ጥያቄ] የዚያን እለት ያደመጠው ተማሪ መንፈሱ በተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ሆኖ ከአዳራሹ እንደወጣ እገምታለሁ። …በዩኒቨርሲቲም ሆነ በኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሕይወታችን አብዛኛዎቻችን ማለት ይቻላል ለየግል ነገዳዊ ማንነታችን ብዙም ትኩረት ሳንሰጥ ወይም እንዳንሰጥ ተደርገን ያደግን በመሆናችን፤ ነገዳዊነትን በሆነ መልኩ የሚያንጸባርቁ ተማሪዎችን እንደ ጎጠኛ ቆጥረን ዝቅ አድርገን ስናይ፤ በይበልጥም በትግላችን ሒደት የጋራ አገራዊ መፈክር ይዘን በአንድነት እንጮኽ፣ እንፈክር፣ እንዘምር ወዘተ የነበርን ወጣቶች ከዚያች እለት በኋላ አንዳችን የሌላችንን ነገዳዊ ማንነት ለማወቅ ወደ ጎን መተያየት የጀመርን ያህል ይሰማኛል።››

ሑሴን አዳል በዚሁ ላይ በዝርዝር ጽሑፋቸው እንዳሰፈሩት፤ ዋለልኝ ጥያቄውን ባያነሳ ኖሮ የብሔር ትግል ጥያቄ በኢትዮጵያ አይነሳም ነበር ማለት አይቻልም ይላሉ። ጥያቄው ቢነሳም እንቅስቃሴውን ፊት ሆኖ የሚመራ ብቁ ሰው ኢትዮጵያ የላትም ማለትም ዘበት እንደሆነ ይገልጻሉ። ‹‹ይህ ታሪካዊ አጋጣሚ እንጂ የዕድል ጉዳይ አይደለም። ኅብረተሰብ በቅራኔ ስለመሞላቱና በማያቋርጥ የለውጥ ሒደት ውስጥ ስለመገኘቱ፣ የኅብረተሰብ ቁስ አካልነት ፍልስፍና አስተምህሮ ይገልጻል።›› ሲሉም፤ የዋለልኝ ጥያቄ ቢነሳም ባይነሳም፤ አስቀድሞ ጥያቄው እንደነበር፤ ባይኖር እንኳ መነሳቱ አይቀሬ እንደነበር አመላክተዋል።

ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን ያካፈሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) በዚሁ ላይ በማከል፤ ጥያቄው የእርሱ [የዋለልኝ] ብቻ ሳይሆን በወቅቱ የነበሩ ተማሪዎችም ጥያቄ ነው ይላሉ። እንደውም በኢብሳ ጉተማ የተጻፈው ‹‹ኢትዮጵያዊው ማን ነው?›› የሚል ግጥም መነሻ መሠረት ስለመሆኑም ይጠቅሳሉ። እናም ዋለልኝም በዛ ግጥም ላይ ተመሥርቶ ነው በጣም ግልጽ በሆነ መልኩ ጥያቄውን ያስቀመጠው። ጥያቄውን ለመመለስ ከማፈን ጀምሮ ተከትለው የመጡት መንግሥታት የተለያዩ መንገዶችን ቢሞክሩም፤ መልስ ለመስጠት ቅርብ ሆኖ የተገኘው ፌዴራሊዝም ስለመሆኑም ሲሳይ ገልጸዋል።

ያደረ ሒሳብ
ጥያቄው ከመሠረቱ ከዋለልኝ የመነጨ ይሁን ወይም አስቀድሞ በሕዝብ ሐሳብና ሕሊና ውስጥ ሲመላለስ የነበረ፤ ብቻ እስከዛሬ መልስ ያላገኘ ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ። መልስ ካለማግኘቱ በላይ አስቀድሞ ባይነሳ ይሻል ነበር የሚሉትም የባሰ ግጭት እንዳይፈጠር በመስጋት ነው። ሑሴን አዳል በበኩላቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ የቀድሞ ተማሪዎች ጥንስስ የሆነ የፖለቲካ ሐሳብ ዛሬ አገራችንን ላጋጠማት ወቅታዊ ችግር መነሻ ነው ተብሎ ቢወቀሱ፣ ‹‹አፈራቸውን አራግፈው ከመቃብራቸው አይነሱም›› እናም ከዚህ ይልቅ ማተኮር ይሻላል ያሉት ከወቀሳው ጀርባ ያለውን እውነታ መርምሮ መረዳትና የራስን አቋም ማስተካከል ላይ ነው።

ዓለማየሁ በዛው ‹‹ምሁሩ›› በተሰኘ መጽሐፋቸው ካሰፈሩት ተጨማሪ እንጥቀስ፤ ይልቁንም የዋለልኝ አምስት ገጽ ጽሑፍ ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመመሥረት ከሚታገሉ ኀይሎች ይልቅ የመገንጠል ሐሳብ ላላቸውና የብሔር ነጻ አውጪ ነን ለሚሉ ኀይሎች ንድፈ ሐሳባዊ ድጋፍ የሚሰጥ ሆኖ መገኘቱ ግልጽ ነው›› ሲሉ ያትታሉ። ታድያ ለያኔው ተማሪ ይህ ጉዳይ መነሳቱ እንደ ዛሬ የተለመደ እንዳልነበረም በቀጠለው የመጽሐፉ ገጽ እንዲህ ሲሉ እይታቸውን ገልጸዋል፤
‹‹ለያኔው ትውልድ ኢትዮጵያ በዚህ መልክ አልነበረም የተሰጠችው። የነገድም ሆነ የብሔር ማንነትን በቋንቋም ሆነ በሌላ መንገድ መግለጽ እንደ ጎሰኛና ጠባብ አስተሳሰብ ይታይ ነበርና የዋለልኝ ጽሑፍ እዚህ ዓይነቱ ነባር አስተሳሰብ ላይ የተጣለ ፈንጂ ነበር››
በዚህ መካከል የተማሪዎች አመጽ በርትቶ ደርግ ወደ ሥልጣን መጣ። ዋለልኝም ኅዳር 29/1965 ተገደለ። ነገር ግን ትግሉና ጥያቄው በዛ አላበቃም። ሑሴን እንደጠቀሱት፤ በንጉሡ ዙፋን የተተካው ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ፣ የብሔር ትግልን በአዋጅ ዘጋው። ምናልባትም በወቅቱ ምላሽ መስጠት ቢቻል ኖሮ ጥያቄው በአጨቃጫቂነት እስከዛሬ ላይቀጥል እንደሚችል ብዙዎች የሚናገሩትም ይህን መነሻ በማድረግ ነው።

ታድያ ደርግን በመቃወም ይደረግ የነበረው ትግል ሕዝብን ነጻ ከማውጣት ተፋትቶ የተማሪዎች የትግል እንቅስቃሴም ቀርቶ አውዱ ብሔር ሆነ፤ ጥቂት የማይባሉ የብሔሮች ‹ነጻ አውጪ›ዎችም ተወለዱ። በንጉሡ ዘመን የተነሳው ጥያቄ ሲወርድ ሲዋረድ ወደ ደርግ ደርሶ ምላሹ ባለመገኘቱ ወደ ጫካ፤ ወደ ሌላ ዓይነት ትግል ተገባ።

ሑሴን እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል፤ ‹‹ለኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች ነጻ መውጣት በጋራ እንታገል በሚለው ምትክ፣ “ለብሔሬ” ልታገል የሚል ጠባብ አስተሳሰብ መሬት ያዘ።… ይህ ዝቅጠት በአገራችን የነበረውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ዕድገት ጅማሮ ወደ ኋላ መለሰው።››

ዋለልኝ በጽሑፉ መግቢያ ላይ ‹‹አንባብያን ሐረጋትን ከዓውዳቸው ውጪ እየነጠሉ ከማጋነን አዝማሚያ እንዲቆጠቡ ተስፋ አደርጋለሁ›› ቢልም ተስፋውም እውን የሆነ አይመስልም ወይም የፈራው አንዳች ነገር የደረሰ ይመስላል። ሑሴን እንደሚሉት፣ ‹‹የብሔረሰብ ፓርቲ ያቋቋሙት ተማሪዎችና ልኂቃን በነበረባቸው የአቅም ውስንነት የተነሳ ያልጠራውን የብሔር/ብሔረሰብ ጽንሰ ሐሳብ እንደመሰላቸው በመተርጎም፣ “የአማራ ገዥ መደብ” ሲባል የነበረውን “ጨቋኝ የአማራ ብሔር” በሚል በመተካት፣ ትግሉን በአማራ ሕዝብ፤ የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት እና የአማርኛ ቋንቋ ላይ እንዲያነጣጥር በማድረግ፤ የኤርትራ ጥያቄም “በጨቋኙ የአማራ ብሔር” ተጽዕኖ ምክንያት የመጣ፣ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው ብለው ተነሱ›› ይላሉ።

የጎንደር ዩኒቨርስቲው ማርሸት በበኩላቸው ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን ሲያካፍሉ፤ ጥያቄው በተነሳ ጊዜ የምሥራቁ ፖለቲካ፣ የእነ ካርል እና የእነ ሌኒን መዛግብት ምንጭ ነበሩ። በወቅቱ እነዚህን መዛግብት መጥቀስም ሆነ ስለእነዚህ ማወቅ የአዋቂነት ልክ ተደርጎ መቆጠሩ ላይ፤ ጥያቄው የተነሳበት አቅጣጫ ከኢትዮጵያ እውነታ ጋር አብሮ ሊሔድ የማይችል መሆኑን ያነሳሉ። በዚህ ላይ ጥልቅ ትንታኔ ሳይሰጥ ጥያቄውን የተቀበሉትና ‹የተረከቡት› ጥያቄውን ከማጠናከር በዘለለ ከሌላ አንጻር ለማየትና ለመመርመር ጊዜ የሰጡ አልነበሩም።

ልክ እንደ ሑሴን ሁሉ ማርሸት ደርግ ጥያቄውን ለማፈን መሞከሩ፣ እየባሰ ከሔደው ድህነትና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ጋር፤ ሐሳቡን ተረክበው ጥያቄውን ያነሱት ሰዎች ወደ ጫፍ/ጽንፍ እንዲወስዱ አድርጓቸዋል ይላሉ። እንደውም በጊዜው መልስ ያላገኘው የብሔር ጥያቄ ሳይሆን የኢኮኖሚ ጥያቄ እንደነበር ይጠቅሳሉ። ‹‹የሕዝቡ የኢኮኖሚ ጥያቄ ባለመመለሱ የብሔር ጥያቄውን እያጠነከረ ሔደ ብዬ አምናለሁ። በሕወሓት የሚመራው ደርግን የጣለው ኃይል ወደፊት ሲመጣም ጥያቄዎቹ ዋልታ ረገጡ እንጂ አልተመለሱም›› ብለዋል።

ችግሩ- ከጥያቄው ወይስ ከ‹‹መልሱ››?
አሁንም የሑሴንን ሐሳብ እናንሳ፤ እርሳቸው እንደውም ቀጥሎ የተነሳው የብሔር ጉዳይ ‹‹የማይረባው የፖለቲካ ንድፈ-ሐሳብ› ሲሉት፤ ከቀድሞ ተማሪዎች የብሔር ትግል ንድፈሐሳብ ጋር በዓይነቱ ፈጽሞ ይቃረናል ባይ ናቸው። የተማሪዎቹ ጥያቄና የብሔር ትግል የነበረው፤ ‹‹በየጠቅላይ ግዛቱ የሚኖሩት ብሔረሰቦች ሕዝቦች መብት ስለመከበር፤ በቋንቋቸው እንዲማሩ፤ እንዲዳኙ ስለማድረግና አስተዳዳሪዎቻቸውን እንዲመርጡ፤ እኩልነት በሰፈነበት ምኅዳር ተከባብረው በአንድነት እንዲኖሩ ስለማስቻል›› ነው።

ዓላማውም ‹‹በየጠቅላይ ግዛቱ የነበረው ታህታይ ኅብረ ብሔራዊነት፣ የሁሉም ብሔረሰቦች ሕዝቦች እኩልነት በሰፈነበት ምኅዳር ወደ እውነተኛ ላዕላይ ኅብረ ብሔራዊነት (ኢትዮጵያዊነት) የሚረማመድበት አስቻይ ሁኔታ መፍጠር እንጂ ማኅበረሰቦች ከያሉበት ዘውግ ተነጣጥለው፣ በቋንቋ ግድግዳ አጥር ለየብቻቸው ተኮልኩለው እንዲኖሩ ስለማድረግ፤ በዳር ድንበር ተለያይተው በጉርብትና እየተናቆሩ የሚኖሩ ብሔረሰቦች ሕዝቦችን ስለማየትና ኢትዮጵያን ቀስ በቀስ አዳክሞ ስለመበታተን አልነበረም›› ሲሉ ጠቅሰዋል።

እንደውም በዚህ ምክንያት የቀድሞ ተማሪዎች ትግል መስመሩ እንደተቀየረና የብሔር ትግል እንደከሸፈም ነው የገለጹት። ይህም ችግሩ ያለው ከጥያቄው ሳይሆን ታግለው ወደ ሥልጣን የመጡት ጥያቄውን ራሳቸው በፈለጉት አንጻር ሊመለከቱትና ሊተረጉሙት በመቻላቸው ነው።

መምህር ገብረኪዳን መከፋፈልና ግጭትን ያመጡት አሁንም ሐቅን መዋጥ የሚያቅታቸው ሰዎች ናቸው ባይ ናቸው። ይህም ከመከፋፈል አልፎ እርስ በእርስ ጦርነት ሊያስነሳ እንደሚችል ጠቅሰዋል። ከቀደመው ይልቅ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተሠራውንና የሆነውንም አብዝተው ሲኮንኑ፤ አካሔዱም የብሔር ጥያቄን የሚያፍን ነው ከሚል ስጋት፤ ‹‹ለጥፋት ካልሆነ በቀር ከእንግዲህ ወዲህ አንድ አገር አንድ ሕዝብ አንድ ቋንቋ የሚለው አይሠራም›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን አካፍለዋል። እንደውም በ2010 የመጣውን ለውጥ ጠቅሰው፤ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እስኪመጡ ችግር አልነበረም›› ሲሉ ያክላሉ። ከዚህ በተጓዳኝ ለሚታዩ ግጭቶች መንስኤው ጥያቄው ሳይሆን ሥልጣን ፈላጊ ሰዎች ናቸው ብለዋል።

የሕግ መምህሩ ሲሳይ በበኩላቸው፤ ለግጭት መንስኤ የሆነው ወይም ችግሩ ከጥያቄው ነው አላሉም። ‹‹ጥያቄው ችግር የለበትም፤ በጊዜው የነበረውን የአገር ሁኔታና ግንኙነት ግምት ውስጥ ያስገባ ነው። ሁሉ ሥልጣን በንጉሡ እጅ የነበረበት ጊዜ ነው›› ሲሉ ያስታውሳሉ። ጥያቄው ግን እስከ አሁን ተገቢውን ምላሽ ሳያገኝ ስለመቅረቱ አያይዘው ጠቅሰዋል። ችግር ያለውም ከዚሁ መልስ ለመስጠት ከተደረገና ከሚደረግ ሙከራ ሲሆን፤ የባለሥልጣናት ከሕዝቡ ፍላጎት የተለየ ዓላማና ግብ ታክሎበት ፈታኝ አድርጎታል።

መልሱን ከፌደራሊዝም ጓዳ
ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በግልጽ መልስ ያልሰጡትና ደርግ በመሣሪያ ዝም ሊያሰኝ የሞከረውን ጥያቄ ኢሕአዴግ በፌዴራሊዝም አቅጣጫ መሪነት ሊመልሰው ሙከራ አድርጓል። ሲሳይ እንደሚሉት ፌዴራሊዝም ለጥያቄው መልስ ለመስጠት የተሻለ ተመራጭ መንገድ ነበር። ሕገ መንግሥቱም ቢሆን በ1987 ሲጸድቅ በተወሰነ መልኩ እኩልነትን ያረጋገጠ ነበር፣ ክልሎችም ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ከማድረግ አንጻር። ‹‹አተገባር ላይ ግን ችግሮች አሉ›› ብለዋል ሲሳይ።

እርሳቸው እንደሚሉት አንደኛው ችግር ዋለልኝ መጀመሪያ ካስቀመጠው መርሆ ወጣ ባለ መልኩ ጉዳዩን አክራሪ የብሔር ፖለቲከኞች ከሚገባው በላይ ለጥጠው ሥራ ላይ እንዲውል ማድረጋቸው ነው። ያም ብቻ ሳይሆን ሕገ መንግሥቱ ሁሉን የኅብረተሰብ ክፍል ያሳተፈና ሁሉም አስተያየት ለመስጠት የተካተተበት አልነበረም። ከረቂቁ ጀምሮ ያሳትፍ የነበረው ብሔር ተኮር ፓርቲዎችን እንጂ ለአብሮነት የሚሠሩ የአንድነት አገራዊ ፓርቲዎችን አልነበረም።

‹‹በኋላም በተግባር የታየው አሸናፊዎች ያጸደቁት ሕገ መንግሥትና በአሸናፊ ፍላጎት የተቀረጸ የፌዴራል ሥርዓት ነው ተግባር ላይ የዋለው። በተለይ በትህነግ/ሕወሓት ፍላጎትና ስሜት ነው ሁሉም የተቃኘው›› ይላሉ ሲሳይ። ትህነግ/ሕወሓት አሁን ላይ እያሳየ ያለውን አቋም የሚጠቅሱት የሕግ መምህሩ፤ አሁን እያታየ እንዳለው የትግራይን ሪፐብሊክ /ነጻ የትግራይ መንግሥት የመመሥረት ፍላጎት ነበራቸው።

ስለዚህም እያንዳንዱም እንቅስቃሴ ጥያቄውን ከመመለስ ይልቅ ፍላጎታቸውን ለመሙላት የተደረገ ሲሆን፣ በዛ መልክም ብሔሮች ወይም በክልል የተደራጁ የአገሪቱ ክፍሎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በማንኛውም ጊዜ ነጻ አገር ሊሆኑ እንዲችሉ በሕገ መንግሥቱ እድል አስቀምጠዋል። ይህም ለአብሮነት ዋጋ እንዳይሰጥ ከማድረጉ በላይ ሕገ መንግሥቱ ለክልሎች አደረጃጀት የተለያዩ መስፈርቶችን ቢያስቀምጥም በግልጽ የሚታየው አደረጃጀት ያተኮረው ቋንቋ ላይ ነው።

እዚህ ላይ በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር) ‹‹ጠርዝ ላይ›› በተሰኘ መጽሐፋቸው ያነሱትን ነጥብ እናስገባ። በመጽሐፉ (ገጽ 75) የኢሕአዴግ መንግሥት የፖለቲካ አስተሳሰብ አስኳል ስላደረገው ቋንቋና ጎሳዊ ማንነት ነው ሲል ይጠቅሳል። ‹‹ከዚህ አስተሳሰብ የመነጨው በ1984 የተዘጋጀው የትምህርት ሥልጠና ፖሊሲ፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ሕዝቦች በቋንቋቸው እንዲጠቀሙ፣ ባህላቸውን ያለመሸማቀቅ እንዲያደርጉ፣ ሕጻናት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ ይደነግጋል። ይሁን እንጂ ለዝርዝር ተግባራዊነቱ የተቀመጠ ዝርዝር የቋንቋ ፖሊሲና የቋንቋዎች አቋም እቅድ የለም። በዚህም የተነሳ የቋንቋ ጉዳይ በዘመነ ቀዳማዊ ኢሕአዴግ የመብት ማስጠበቂያ ብቻ ሳይሆን የግጭትና የውዝግብ ምንጭም ሆኖ ቆይቷል›› ይላል።

ቀጥሎ በሚገኙ የመጽሐፉ ገጾችም፤ በርካታ ቋንቋዎች በሚነገርባቸው አካባቢ ምርጫው ለፖለቲካ ውሳኔ መጋለጡን ይገልጻሉ። ይህን ተከትሎ የትምህርትና የቋንቋ ፖሊሲ አነዳደፍም ሆነ አተገባበር ያለፈው መንግሥት የቋንቋ ትግበራ ላይ ያለ ጥላቻ ነጸብራቅ ያረፈበት ነው፤ እንደ በድሉ ገለጻ።

ወደቀደመ ነገራችን ስንመለስ፤ ከላይ በተጠቀሰው የቋንቋ ጉዳይም ሆነ በሌሎች ነጥቦች ላይ ‹‹ብሔርተኞች በሚፈልጉት መልኩ አገሪቱን መሩ። አሁን ለግጭት መንስኤ የሆነውና ብሔር ተኮር አንባገነንነት የመጣው፤ እድገቱ የተወሰነ አካባቢ እንዲያዘነብል በመደረጉም ነው። ጥያቄው ትክክለኛ ቢሆንም የተመለሰበት አግባብ ነው ችግሩ›› ሲሉ ሲሳይ ችግር ያለው ከጥያቄ ሳይሆን ከመልስ አሰጣጡ ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መምህር ገብረኪዳን ደግሞ ምንም እንኳ የለውጡን ኃይል [የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን] አካሔድ ቢተቹና ቢቃወሙም፤ አስቀድሞም ለብሔር ጥያቄ መልስ በተሰጠበት መንገድ ላይ ያነሷቸው ነጥቦች አሉ። በዚህም ‹‹ፌዴራሊዝም ያላሟላው ነገር አለ፤ ለምሳሌ የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ ቀድሞ መመለስ ነበረበት፤ ፌዴራሊዝም በትክክል አልተተገበረም›› ይላሉ።

ያም ብቻ አይደለም ብሔሮች በክልል መልክ ሲደራጁ ራሳቸውን በራቸው እንዲያስተዳድሩ በሕገ መንግሥቱም ሆነ በፌዴራሊዝም ሥርዓት ሥልጣን ያላቸው ቢሆንም፤ ይህ በትክክል ተፈጻሚ አለመሆኑን ያነሳሉ። እንዲህም ጠቅሰዋል፤ ‹‹ኢሕአዴግ የራሱን ተላላኪ በየክልሉ ከመመደብ፤ በትክክለኛ ሕዝብን የሚወክልና ሕዝቡም የሚቀበለውን ሰው መሾም ነበረበት። ወደ ማዕከላዊነት እየተጠጋ ነበር፤ ያ ትክክል አይደለም።››

አዳዲሶቹ ጥያቄዎች
በነዋለልኝ ዘመን የጎሳና የብሔር ነገር ሲነሳ ለጆሮ የሚያስደነግጥና የሚያስኮንን፣ አንድነትና አንድ አገርን የሚፈትን ተደርጎ የሚቆጠርና የተፈራ ጉዳይ ነበር። ለዛ ነው ዋለልኝም ‹አይነኬ ጉዳይ አነሳ› ተብሎ ትኩርት ሊስብ የቻለው። ያ ትውልድ ምናልባት በሰላም ለመኖር የወሰደው አማራጭ ዝም ማለትን ሳይሆን አልቀረም፤ ወይም ዛሬ ላይ የሚታየው አስከፊ የሚባል ክስተት በታሪክ መዝገብ ላይ እንዳይሰፍር ከመስጋት በመነጨም ሊሆን ይችላል። ታድያ ዛሬ ላይ የብሔር፣ የጎሳና የጎጥ ጉዳዮች በድፍረትና በግልጽ አንዳንዴም በኩራት የሚነሱ ነጥቦች ሆነዋል። በብሔር ምክንያት እርስ በእርስ ግጭት፣ መገዳደልና ‹ውጡልን!› መባባልም እንግድነቱን ጨርሶ ቤተኛ ሆኗል።

ሲሳይ እንዳነሱት፤ አስቀድሞ ጥያቄው በዋለልኝና በጊዜው በነበሩ ተማሪዎች መነሳቱ ከነበረው ንቃተ ሕሊና አንጻር መነሳት አልነበረበትም የሚሉ አሉ። ጥያቄው ስሜታዊነት ይንጸባረቅበት፣ ድፍረት የተመላ እና ከጊዜው የቀደመ ጥያቄ ከመሆኑ ግን ችግር ኖሮበት እንዳልሆነ አስምረው ይጠቅሳሉ።

ሕወሓት/ኢሕአዴግ በ1983 በትጥቅ ትግል ሲያሸንፍ ከፊሉን ጥያቄ ለመመለስና በሕገ መንግሥት እውቅና ለመስጠት ተሞክልሯልም ይላሉ። ነገር ግን ነባሩ ጥያቄ በዛ መንገድ ሲመለስ አዳዲስ ጥያቄዎች መጥተዋል። ይልቁንም ቀደም ሲል የባህልም ሆነ የቋንቋ ተጽእኖ ያልነበረባቸው አሁን ተጽእኖ ውስጥ ወድቀዋል። ለምሳሌ ያነሱት አማራውን ነው። ‹‹አማራው ያኔ ብዙም ችግር አልነበረበትም፤ እንደ ሕዝብም ጨቋኝ ባይሆንም ስርዓቱ አማርኛ ቋንቋና ባህል እየተጠቀመ ሌሎች ላይ ጫና ያሳርፍ ነበር፤ አሁን በተቃራኒው አማራው ላይ ጫናዎች አሉ›› ይላሉ።

አንዱ ነባር አንዱ መጤ ወይም ኹለተኛ ዜጋ፣ አንዱ የቤት ልጅና ሌላው የእንጀራ ልጅ ተደርጎ የሚታይበት ሁኔታ በዜጎች መካከል እየተፈጠረ አዲስ ጥያቄም እየተወለደ ነው። ስሜታዊ ከመሆን በላይ የተሳሳተ ትርክት ማቅረብና ታሪክን የማዛበት፣ ፖለቲካውን ማጣመም ሁኔታዎች ታይተዋል። ክልሎች በውስጣቸው ያሉ ከእነርሱ የተለየ ብሔር ተወላጆችን አለማክበር፣ እውቅና አለመስጠትና ‹መጤ› መባባልን ፌዴራል መንግሥቱ ዝም ብሎ ሲታዘብ ስለመቆየቱም ሲሳይ ጠቁመዋል።
ኢሕአዴግን ሲመራ የቆየው ሕወሓት የዚህ ሐሳብ ተጋሪ ሆኖ በመገኘቱ ለዚህ መፍትሔ ሳይሰጠው ቀርቷል፤ አዳዲስ ጥያቄዎች እንዲወለዱም ሆኗል። ‹‹የትሕነግ የበላይነት ያለበት ፌዴራል መንግሥት ስለሆነ አንደኛ አማራን አንገት ማስደፋትና ጨቋኝ አድርጎ የመተርጎም፣ አማራ ላይ ጫና መፍጠር እና ሌሎች ብሔረሰቦች አማራ ላይ ጥላቻ እንዲኖራቸውና አማራን በጠላትነት እንዲፈርጁ አድርጎ የመቃኘት ነገር ስለነበር፤ መሠረታዊው ችግር የቂም በቀለ ፖለቲካ ማራመድ ነው ብዬ ነው የማስበው›› ብለዋል፤ ሲሳይ።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲው ማርሸት በበኩላቸው፤ በትኩረት መታየት አለበት ከሚሉት የኢኮኖሚ አቅም አንጻር አሁን ላይ መሻሻሎች ስለመኖራቸው ጠቅሰዋል። ነገር ግን ደግሞ በክልሎች መካከል እኩል በሆነ ደረጃ ይህ መሻሻል እንደማይታይ ነው የጠቀሱት። እኩል ተጠቃሚ መሆን ባለመቻል ምክንያትም ‹‹የእኔና የእገሌ ብሔር›› የሚለውን ካለፉት ዓመታት ይልቅ አጠናክሮታል›› ባይ ናቸው። እናም በቀደመው ጊዜ ድህነት ለጥያቄው መነሻ ነው ሲሉ አሁን ደግሞ የኢኮኖሚ ልዩነት የብሔር ጥያቄውን እያጋጋለና አዳዲስ ጥያቄ እየወለደ ይገኛል።

የመፍትሔ ያለህ!
ለብሔር ጥያቄ መልስ በመስጠት ግጭትንና መከፋፈልን ለማስቆምና አንድነትን ለማጠናከር አሁን ላይ የብልጽግና ፓርቲ የ‹መደመር› ፍልስፍና ላይ ተስፋቸውን የጣሉ ጥቂት አይደሉም። ኢሕአዴግ የአንድ ወጣት እድሜን ባስቆጠረበት ዘመን ያልሰጠውን መፍትሔ በወጣትነቱ ማብቂያ በውሕደት መልሱን ሊሰጥ ይችላል የሚል መላምት የሚሰጡም ብዙዎች ናቸው።

ሲሳይ እንደሚሉት፤ መደመር እንደ አንድ የመፍትሔ አቅጣጫ ሊወሰድ ይችላል ወይ የሚለው አከራካሪ ሆኖ፤ በመደመርና በአብሮነት በመነጋገር ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል ይጠቅሳሉ። ለመነጋር ግን መጀመሪያ መግባባትና ቅራኔዎችን መፍታት አስፈላጊ ስለመሆኑም አጽንዖት ይሰጣሉ።

ቃል በቃል ሲሳይ ያቀረቡት የመፍትሔ ሐሳብ እንዲህ ይላል፤ ‹‹ትልቁ መፍትሔ ብዬ የማምነው፤ ሕገ መንግሥት ራሱ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ ችግሩን በሚፈታ መልኩ ማሻሻል ይጠይቃል። ይህም ሁሉም ዜጎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን የሚሳተፉበትና የእኛ ነው የሚሉት እንዲሆነ የማድረግ ጉዳይ ነው። የክልል አደረጃጀትን እንደገና መፈተሸ፣ ማስተካከልና የተመጣጠኑና ኅብረ ብሔራዊ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል›› ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ተመሳሳይ ቋንቋ የሚናገሩ በርካታ ክልሎች ያሉባቸውን አገራት በመጥቀስ፤ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎችም የተለያየ ክልል እንዲኖር ማድረግንም እንደ አማራጭ አቅርበዋል። ‹‹አንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች በአንድ ክልል መታጨቅ የለባቸውም። የተመጣጠኑ ክልሎች እንዲሆኑ በዚህ መልክ መቃኘት አለበት›› ሲሉም አክለዋል። በተጨማሪም እንደ ሐረሪ እና ድሬዳዋ ዓይነት አካባቢዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው አሁን ባለበት መልክ መታጠሩ ቀርቶም መስፋት አለባቸው የሚል ሐሳብ ሰጥተዋል።

የክልሎችም ቁጥር መጨመር እስካስፈለገ ድረስ ጥያቄዎችን በማስተናገድ፤ ጥያቄና ችግር የሌለባቸው ባሉበት እንዲቀጥሉ ሲሉም ሐሳባቸውን አጋርተዋል።
ሑሴን ሰፋ ባለ ጽሑፋቸው እንዳስቀመጡት፣ ትውልዱ ካለፈው ነገር በመማር ማስተዋል እንደሚኖርበት ነው። ‹‹የብሔር ትግሉ ታሪክና ውጤት ለወጣቱ ትውልድ ሊሰጥ የሚችለውን ትምህርት ከትውልዱ ቀጣይ ኃላፊነት ጋር አያይዞ መመልከት ያስፈልጋል።… አገራችን አሁንም በጂኦፖለቲካ መዘዝ ራዳር ክልል ውስጥ መሆኗን፤ ዛሬም ለግል ጥቅም የሚራወጡ የውስጥ ቦርቧሪና የውጭ ደመኛ ጠላቶች አለመገላገሏን መገንዘብ አለበት። ከዚህ አሳሳቢና አጣብቂኝ ከሆነ ችግር በመነሳት ለአገር ጥቅም ዘብ የሚቆም የብልህ፤ አስተዋይና አገር ወዳድ ወጣት ትውልድ ዋስትና የሚያስፈልጋት መሆኑን ማንም ሳያስተምረው በራሱ ጥረት አውቋል። ድኅረ ዋለልኝ የብሔረሰብ ትግል የተመራበት ስልት በኋላ ቀር አመለካከት የታጀለ ነበር›› ብለዋል።

ማርሸት በበኩላቸው ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት የፖለቲካ ሁኔታ ለመተንበይ በጣም አስቸጋሪ ነው ሲሉ ‹‹በየቀኑ አዳዲስ መልክ ይዞ እየመጣ ያለ ፖለቲካ ነው። አሁን ያለው ነገር ግን በሦስት የተጠቃለለ ይመስለኛል›› በማለት ለወደፊቱ የሚታያቸውን ገልጸዋል። ይህም ከፖለቲካው አሰላለፍና ከምርጫ ጋር የተገናኘ ሲሆን አንደኛው ‹ብልጽግና ፓርቲ› ኹለቱን ማለትም የብሔር ተኮር ጽንፍ ላይ ያለውን ኀይል እና የአንድነት ኀይሉን አስታርቆ ለመሔድ የሚሞክር ሆኖ ሲወጣ፤ የክልል ፖለቲካን በጽንፍ የሚያቀነቅኑ የፌዴራሊስት ኀይሎች በሌላ ወገን፤ በሦስተኛ ደረጃ እንደ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ያለው ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ላይ ብቻ እያቀነቀነ ያለ ብሔራዊ ፓርቲ በመሆን ሰፋ ያለ ምርጫ ለሕዝብ ቀርቧል ይላሉ።

ያም ሆነ ይህ፤ በሁሉም መንገድ አሁንም ለብሔር ጥያቄ መልስ ፍለጋው አላበቃም። ዋለልኝ ጥያቄውን ሲያነሳ መልስ ይገኝበታል ብሎ ያሰበው የመፍትሔ ሐሳብ በጽሑፉ ሰፍሮ እንደሚታየው፤ አብዮታዊ የትጥቅ ትግልን ነው። ይህ ምናልባት በዛን ወቅት ቀድሞ ወደ ሐሳብ ሊመጣ የሚችል አማራጭ ይሆናል። ዴሞክራሲን ተስፋ አድርጋ በምትጠብቅ የአሁኗ ኢትዮጵያ ግን አሁንም ከፌዴራሊዝሙ እንዲሁም ከሕዝብና ከአመራሩም ጭምር ለጥያቄው መልስ ፍለጋዋን ትቀጥላለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here